የየመን የባሕር ዳርቻዎችን በመቆጣጠር በቀይ ባሕር ላይ ስጋት የደቀኑት ሁቲዎች እና የኢራን ጥሪ
የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ወደ ቀይ ባሕር በሚስገባው ወሳኙ የባብ ኤል መንደብ መተላላፊያ አቅራቢያ የሚገኙ ወደቦችን እየተቆጣጠሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ኢራን ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቀረበች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገሪቱ አጋር የሆኑት ሁቲ ታጣቂዎች በየመን ውስጥ እያካሄዱት ባለው ጦርነት እየታየ ያለውን ለውጥ በመጥቀስ ባወጣው መግለጫ የመን ላይ የተጣለው ወታደራዊ ከበባ እንዲነሳ እና ድርድር እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።
በኢራን መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኢርና በኩል ይፋ የተደረገው መግለጫ፣ “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ፣ የሙስሊሙን ሕዝብ ጥቅም መጠበቅ አስፈላጊነትን እያሳሰበች፣...በአሜሪካ ድጋፍ እየተስፋፋ ያለውን የጽዮናዊው ሥርዓት ጥቃት እና መስፋፋት በምትጋፈጥበት ወቅት፣ የየመን ችግር በከበባ እና በወታደራዊ ጥቃት ሊፈታ እንደማይችል ታሳስባለች” ብሏል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮም የየመን ኃይሎች “በተስማሙበት የሰላም ፍኖተ ካርታ መሠረት ውይይቱ በአስቸኳይ እንዲቀጥል እና ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች መተግበራቸው” አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ፣ ኢራንም “ማንኛውንም ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ ናት” ብሏል።
ይህ የኢራን መግለጫ የወጣው፣ ሁቲዎች በየመን የሚገኘውን የሞካ ወደብን ጨምሮ አንዳንድ የአገሪቱን አካባቢው በመቆጣጠር እየገሰገሱ እና በሳዑዲ አረቢያ የሚደገፉት የየመን መንግሥት ኃይሎች እያፈገፈጉ መሆናቸው እየተዘገበ ባለበት ጊዜ ነው።
ትናንት ሐሙስ ጳጉሜ 5 በሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ የሚያገኙት የየመን ኃይሎች እና አጋሮቻቸው ዱባብ ከተባለችው ሌላ ወደብ መውጣታቸውም ተዘግቧል።
የሞካ ወደብ በሁቲዎች እጅ መውደቁ፣ በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የነዳጅ እና የሸቀጦች ዋነኛ መተላለፊያ በሆነው የቀይ ባሕር መስመር ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ያጠናክራል።
ይህ ወደብ ቀይ ባሕርን ከሕንድ ውቅያኖስ በሚያገናኘው የባብ ኤል መንደብ ባሕር ወሽመጥ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ለባሕር ላይ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።
በተጨማሪም የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ሐሙስ ዕለት አንድ ወታደራዊ ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሁቲዎች “ሮኬቶች እና ታጣቂዎችን በጫኑ ጀልባዎች በመጠቀም በፈጸሙት ወረራ” በደቡባዊ ቀይ ባሕር የሚገኘውን ዛቅር የተባለውን ደሴት ተቆጣጥረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁቲ ታጣቂዎች እንደ ዋነኛ ጠላት የሚመለከቷት የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሳል ቢን ፋርሃን ከኢራኑ አቻቸው አባስ አራግቺ ጋር በየመን ስላለው ሁኔታ በስልክ ተወያይተዋል።
ሳዑዲ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለውን የየመን መንግሥት እና ሌሎች ፀረ ሁቲ ታጣቂዎችን የምትደግፍ ሲሆን፣ ኢራን ደግሞ የሁቲዎች አጋር መሆኗ ይታወቃል።