ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት የደረሱባቸው የመግባቢያ ነጥቦች ይፋ ሆኑ

አሜሪካ እና ኢራን ከሦስት ወራት በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ። በመካከለኛው ምሥራቅ ብሎማ በመላው ዓለም ከባድ ቀውስን አስከትሎ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ለወራት ሲደረግ የነበረው ድርድረ አርብ ዕለት ስዊትዘርላንድ ውስጥ በሚካሄድ የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ይቋጫል ተብሏል። አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ እንዲቆም በደረሱት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ጦርነቱ እንደሚቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደሚከፈት ተዘግቧል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም ተባለ

    ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም እንደማይጠበቅባቸው የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ገለጹ።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከሲኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ለረዥም ጊዜ ከክፍያ ነጻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።

    ጦርነቱ መነሳቱን ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚያልፉ መርከቦች የክፍያ ሥርዓት ዘርግታ ቆይታለች።

    አሁን ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው ስምምነት አማካኝነት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለ ክፍያ ማለፍ ጊዜያዊ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ጄዲ ቫንስ፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ከኢራን ጋር መወያየት እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

    ክፍያውን ማስቀረት “በቴክኒክ ድርድሩ ወቅት የምናነሳው ጉዳይ ይሆናል። አብረን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የምንወያይባቸው በጣም ጠቃሚ ነጥቦች ይኖራሉ” ብለዋል።

  2. የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት በቀጣይ ቀናት እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ማክሮን ገለጹ

    ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

    የፎቶው ባለመብት, YOAN VALAT/EPA/Shutterstock

    ከሁለት ወይም ከሦስት ቀናት በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ጥምር እንቅስቃሴ እንደሚጀመር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።

    ዛሬ በፈረንሳይ እየተካሄደ ባለው የቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሆርሙዝ ወሽመጥን ነጻ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ “በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ” ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

    የሁለቱ አገራት ጥምር እንቅስቃሴ ወደ አካባቢው ተዋጊ አውሮፕላን እና ፈንጂ አምካኝ ባለሙያዎችን መላክን እንደሚያካትት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

    “በቀጣናው ተዋጊ አውሮፕላን ጫኙ መርከብ ቻርለስ ደ ጎል አለን። የድጋፍ ቁሳቁስ ጭኗል። ስምምነቱ በተረጋገጠ በሁለት ወይም ሦስት ቀናት ሊሰማራ ይችላል” ብለዋል።

    ስምሪቱ የሚከናወነው ከአሜሪካ እና “በትይዩ ደግሞ ከኢራናውያን ጋር” መሆኑን ማክሮን ጠቅሰዋል። በዚህም የሆርሙዝ ወሽመጥ “በሰላም ተከፍቶ መዝለቁን” ማረጋገጥ እንደሚቻል አክለዋል።

  3. የኒውክሌር መርሃ ግብር እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውይይት ይደረግባቸዋል- የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለማረጋገጥ እና የፊታችን አርብ በስዊትዘርላንድ ስለሚደረገው ይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓት ለብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ቴህራን አሜሪካ ላይ ስላላት የአመኔታ ችግር በድጋሚ ገልፀው፤ አገራቸው የአሜሪካን ቃል ኪዳኖች አፈፃፀም “እንደምትከታተል” ጠቅሰዋል።

    እስራኤል ቤይሩትን ማጥቃቷን ተከትሎ ቴህራን መዛቷ “የስምምነቱን ይዘት እንዲፋጠን ያገዘ እና አንዳንድ ጉዳዮችን የፈታ” እንደነበር ጠቁመዋል።

    ምክትል ሚኒስትሩ ኢራን ድርድሩ በ60 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላት ተናግረዋል። በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ከአገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ድርድር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

    በዚህ 60 ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ ጉዳት የደረሰበትን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ዳግም ለመገንባት የሚያስችሉ ጉዳዮችም የድርድሩ አካል ናቸው ብለዋል።

  4. ኢራን፤ እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም አለበት” አለች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራጋቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/ Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራጋቺ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ዛሬ ሰኞ ማለዳ ከቱርክ፣ ከኢራቅ እና ከግብፅ አቻዎቸው ጋር በስልክ መወያየታቸውን በቴሌግራም ገጻቸው ላይ አስታወቁ።

    አራግቺ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ጋር እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመው ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መቆም እንዳለበት” መወያየታቸውን አስፍረዋል።

    አራግቺ አክለውም ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የአሜሪካ ኃላፊነት እንደሆነም ገልጸዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ አገራቸው ጦሯን የደኅንነት ቀጣና ብላ ከከለለችው ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ሶሪያ እንደማታስወጣ አስታውቀዋል።

    ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነም አገራቸው “ሙሉ ኃይሏን ተጠቅማ” ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።

    ካትዝ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የደኅንነት ቀጣና ከአካባቢው ነዋሪዎች እና “ከሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች፣ በመንደሩ ከሚገኙ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቤቶች” ነጻ እንደሚሆን በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

  5. የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ያለ ጊዜ ገደብ ለመቆየት እንደሚያስብ ሚኒስትሩ ገለጹ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሊባኖስ ያለምንም የጊዜ ገደብ የመቆየት ሃሳብ እንዳለው ሚኒስትሩ እዝራኤል ካትዝ አስታወቁ።

    ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት አሜሪካ እና ኢራን አደራዳሪዋ ፓኪስታን ባቀረበችው የመግባቢያ ሰነድ ላይ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው።

    ሁለቱ አገራት“የትኛውንም ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ በሊባኖስ ጨምሮ” ለማቆም ተስማምተዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በሂብሩ በጻፉት መግለጫ ጦራቸው ከሊባኖስ ይውጣ የሚለውን “ግልጽ በሆነ እና በሚጠበቁ ጫናዎች የተነሳ” ይቃወማል ብለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ ከቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ጦሩ በሊባኖስ፣ በሶሪያ እና ጋዛ “የደህንነት ቀጣናዎች ያለ ጊዜ ገደብ” እንደሚቆይ መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

    አክለውም “ሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች”፤ “የእስራኤልን ድንበሮች ለመከላከል” ይወድማሉ እንዲሁም ይህንን አቋሟን ለአሜሪካ ማሳወቋን ገልጸዋል።

    “ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት ከፈጸመች ሙሉ ኃይላችንን ተጠቅመን ጥቃት እንፈጽማለን። ያለንንም የመከላከያ የበላይነት እናሳያለን።”

  6. ሊባኖስ ከአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ስምምነት በኋላ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ለመመለስ እንዳይቸኩሉ አስጠነቀቀች

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ከስምምነት መደረሱን የሰሙ የደቡብ ሊባኖስ፣ ሲዶን ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ከስምምነት መደረሱን የሰሙ የደቡብ ሊባኖስ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል

    የደቡብ ሊባኖስ ባለሥልጣናት በሦስት ወሩ የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ውጊያ የተፈናቀሉ ሰዎች ሰኞ ዕለት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለመመለስ እንዳይጣደፉ አስጠነቀቁ።

    ባለሥልጣናቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት እስራኤል ጦሯን ከደቡባዊ ሊባኖስ እንደማታስወጣ በመናገሯ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን በማስወንጨፉ በደቡባዊ ሊባኖስ ከፍተኛ አየር ድብደባ አካሄዳለች።

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት 3,700 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ 1.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራንን የምታሸማግለው ፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ አገራቱ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት “ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች በቋሚነት እና አሁኑኑ እንዲቆሙ” መግባባታቸውን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በተቆጣጠሯቸው የደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎች እንዳይመለሱ ማስጠንቀቃቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ አገራቸው ጦሯን የደህንነት ቀጣና ብላ ከከለለችው ደቡባዊ ሊባኖስ፣ ጋዛ እና ሶሪያ እንደማታስወጣ ገልጸው፣ ኢራን በሊባኖስ ባለው ሁኔታ የተነሳ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

    ካትዝ በደቡባዊ ሊባኖስ ያለው የደህንነት ቀጣና ከአካባቢው ነዋሪዎች እና “ሁሉም የሽብር መሠረተ ልማቶች፣ በመንደሩ የሚገኙ [ከሄዝቦላህ ጋር] ግንኙነት ያላቸው ቤቶች” ነጻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

  7. ‘በዚህ ስምምነት እኛ አጋሮች አይደለንም፤ እኛን አይገዛም’- የእስራኤል ሚኒስትር

    እስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ኢትማር ቤን-ጋቪር

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, ቤን-ጋቪር እስራኤል ነፃ አገር እና በአሜሪካ ተገዢ እንዳልሆነች ተናግረዋል

    እሁድ ምሽት በፓኪስታን ይፋ በተደረገው የአሜሪካ እና የኢራን የስምምነት ማዕቀፍ ላይ እስራኤል ይፋዊ አስተያየት እስካሁን አልሰጠችም።

    ዛሬ ሰኞ ጠዋት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል ብሔራዊ የደኅንነት ሚኒስትር ኢትማር ቤን-ጋቪር ግን አስተያየት ሰጥተዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገውን ስምምነት በመተቸት “ደኅንነታችን በማያስጠብቀው በዚህ ስምምነት እኛ አጋሮች አይደለንም። እናም በየትኛውም መንገድ እኛን እይገዛም” ብለዋል።

    እስራኤል “ሄዝቦላህን ከመበታተን ያነሰ ነገር መቀበል የለባትም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ላይ የሚደረገው እርምጃ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

    “እያንዳንዱ ከእስራኤል ወደ ሊባኖስ የሚጓዝ ድሮን፣ ሰው አልባ በራሪ ወይም ሚሳዔል በዳሂያ ጥቃት ይፈጽማል” ሲሉም አክለዋል።

    ቤን-ጋቪር የራሳቸውን መንግሥት በተደጋጋሚ የሚተቹ ሲሆን፤ በዩናይትድ ኪንግደም እና በሌሎች አገራት “በፍልስጤም ማኅበረሰብ ላይ ተደጋጋሚ የግጭት ቅስቀሳ” በማድረግ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

  8. የአሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ይፋ ከሆነ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ

    ነዳጅ የሚቀዳ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    አሜሪካ እና ኢራንን የምታሸማግለው ፓኪስታን ሁለቱ አገራት በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ መስምምታቸውን ይፋ ካደረገች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ።

    ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ በኋላ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም ይከፈታል ብለዋል።

    ሰኞ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ4.3 በመቶ ቀንሶ በበርሜል 83.55 ዶላር ተሸጧል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት አርብ ሰኔ 12 2018 ዓ.ም. በስዊትዘርላንድ ይፈረማል ብለዋል።

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከአሜሪካ ጋር ድርድር ሲደረግበት የቆየው ሰነድ ላይ መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ነዳጁ መፍሰስ ይጀምር” ሲሉ ጽፈዋል።

    የኢነርጂ ግብይት ተንታኝ የሆኑት ቫንዳና ሃሪ ግን የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ይፋ ባለመሆናቸው “በገበያው ላይ አለመረጋጋር እና እርግጠኝነት ማጣትን ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።

    አክለውም በዚህ ሳምንት በነዳጅ ገበያው ላይ መዋዠቅን እና እርግጠኛ አለመሆንን ልናይ እንችላለን ብለዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ የተዘጋው አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ የካቲት 21 2018 ኣ.ም. ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።

    ከጥቃቱ በኋላ ቴህራን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በሚያልፍበት ሆርሙዝ በኩል በሚቀዝፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ዝታለች።

    ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ከግጭቱ በፊት ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በበርሜል 70 ዶላር ይሸጥ ነበር።

    ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በጥቂት ቀናት ይህ ዋጋ ወደ 120 ዶላር ከፍ ብሎ ነበር።

  9. የተባበሩት መንግሥታት እና የተለያዩ አገራት በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አደነቁ

    ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ ቃል አቀባይ “ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን የሰላም ስምምነቱ ላይ መድረሳቸውን ይፋ በማድረጋቸው” ደስተኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ አክለውም “ይህ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ እርምጃ” መሆኑን ገልጸዋል።

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱን ካደነቁ የዓለም መሪዎች መካከል ናቸው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጃፓን “በሆርሙዝ ወሽመጥ ነጻ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ በተግባር እንደሚረጋገጥ በብርቱ ተስፋ ታደርጋለች” ካሉ በኋላ “በኢራን የኒውክሌር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ስምምነት በቅርቡ ይደረሳል” ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒሲትር አንቶኒ አልባኔዝ ስምምነቱ “ቋሚ እና ዘላቂ ሰላም” ያመራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድም ይህንን ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ መልሶ መክፈት በኢነርጂ ዋጋ እና ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ይቃለላል” ብለዋል።

    የኒው ዚላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊንስተን ፒተርስ “ወሳኝ እና ገንቢ ስምምነት” እንዲሁም “ውጥረትን ለመቀነስ እንዲሁም መረካካትን ለዓለም ምጣኔ ሀብት ደኅንነት ወሳኝ በሆነው ቀጣናው ለማምጣት” ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን ከስምምነቱ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ አሜሪካን እና ኢራንም እንዲሁ በድርድሩ ውስጥ የተሳተፉትን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    “ይህ ቀጣናዊ መረጋጋት ለማምጣት እና ዓለም ምጣኔ ሀብትን ለማረጋጋት ጥሩ ዕድል ነው” ብለዋል።

    ስምምነቱ በፍጥነት እና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ አንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት አገራቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ያለገደብ” እንዲከፈት ጠይቀዋል።

  10. አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት የደረሱባቸው የመግባቢያ ነጥቦች ይፋ ሆኑ

    የአሜሪካ እና ኢራን ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል ጦርነቱን ለማስቆም ስምምነት በተደረሰበት የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦችን ይፋ አድረገዋል።

    የመገናኛ ብዙኃኑ ባቀረቧቸው ዝርዝሮች ውስጥ የተካተቱት ነጥቦች በሁለቱም ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠባቸውም።

    ሜህር የዜና ወኪል ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል

    • በሁሉም ግንባሮች ሊባኖስን ጨምሮ በቋሚነት ተኩስ ይቆማል
    • አሜሪካ በኢራን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም
    • በ30 ቀናት ውስጥ የአሜሪካ የባሕር ዕገዳ ይነሳል
    • የአሜሪካ ጦር ከኢራን ለቅቆ ይወጣል
    • የሆርሙዝ ወሽመጥ “በኢራናውያን ቁጥጥር” በ30 ቀናት ውስጥ ዳግም ይከፈታል
    • አሜሪካ እና አጋሮቿ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ያቀርባሉ
    • በኢራን የነዳጅ ዘይት እና ኢነርጂ ምርቶች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳት
    • ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ላለማምረት ዳግም ታረጋግጣለች
    • አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጦር አትጨምርም እና አዲስ ማዕቀብም አትጥልም

    ሜህር አክሎም የስምምነቱ መጨረሻ የኢራን እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ግማሽ ሃብቷ እስኪለቀቅ፣ የኢራን ነዳጅ ዘይት ላይ የተጣለው ማዕቀብ እና የባሕር ላይ ዕገዳው እስኪነሳ ድረስ የመጨረሻው ድርድር አይጀመርም ሲል ዘግቧል።

    እንዲሁም የመጨረሻው ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚጸድቅ ዘግቧል።

  11. 15 ሰዓት የፈጀ ንግግር ወደ ስምምነት አድርሷል

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኳታር አሸማጋዮች ትናንት በቴህራን ተገኝተው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ከስምምነት እንዲደረስ በረቂቅ የመግባቢያ ሰነዱ ላይ “ከ14 እስከ 15 ሰዓታት ያህል የረዘመ ንግግር” ማድረጋቸውን ገለጹ።

    ካዘም ጋህሪባባዲ ለኢራን መገናኛ ብዙኃን ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት “ይህ ድርድር ረዥም ጊዜ የወሰደ ነው” ብለዋል።

    “የኳታር የልዑካን ቡድን ኢራን እና በዩናይትድ ስቴትስ ኢዝላማባድ ባቀረበችው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ዙሪያ ውይይቶታቸውን እንዲቋጩ ለማስቻል ትናንት ቴህራን ነበሩ” ብለዋል።

    “ወደ 14 እና 15 ሰዓት የፈጀ ረዥም ንግግር ተካሄዷል። በዚህ ጊዜ የእስላማዊ ሪፐብሊክ ሰነዱ ላይ የመጨረሻውን ማሻሻያ አቅርባለች። እነዚያ ማሻሻያዎች ተቀባይነት አግኝተዋል። እንዲሁም ኢዝላማባድ ያቀረበችው የመግባቢያ ሰነድ ጸድቋል”

    ምክትል ሚኒስትሩ የኢራን ዋና ፍላጎት የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ ቢሆንም ”በርካታ የምታነሳቸው ጉዳዮች ስላሏት” የስምምነቱ የመጨረሻው ክፍል ላይ በ60 ቀናት ውስጥ ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

  12. ስምምነቱ “መካከለኛው ምሥራቅን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት በመሠረታዊነት የሚለውጥ ነው”-ቫንስ

    ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ለፎክስ ኒውስ ስምምነቱ “በመሠረታዊነት መካከለኛው ምሥራቅን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት የሚለውጥ ነው” ሲሉ ተናገሩ።

    “ይህ የዓለማችን ቀጣና በእኔ የእድሜ ዘመን በሙሉ ከዚያም ለረዘመ ጊዜ የአለመረጋጋት ምንጭ ነበር” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃኑ ገልጸዋል።

    ቫንስ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራንን ስጋትነት ማስወገድ ችለዋል” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።

    አክለውም አሁን “የመካከለኛው ምሥራቅ ብልጽግና እና ስኬት አዲስ ዘመንን መገንባት ይቻላል” ብለዋል።

    “እውነቱን ለመናገር ከቀጣናው ለአሜሪካ ሕዝብ በርካታ ሃብት ማመንጨት እንችላለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

  13. አሜሪካ እና ኢራን በሁሉም ግንባሮች፣ ሊባኖስን ጨምሮ ጦርነቱን ለማቆም ተስማሙ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ከሦስት ወር በላይ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዚዳንቱ “ከእስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር እያደረግን የነበረው ስምምነት አሁን ተሟልቷል” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸወ ላይ አስታውቀዋል።

    ትራምፕ ስምምነቱን ተከትሎ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ዘግቶት የነበረውን የኢራን ወደብ እንዲከፍት ያዘዙ ሲሆን መርከቦችም ያለምንም ክፍያ በወሽመጡ መጓዝ እንዲጀምሩ ተናግረዋል።

    “የዓለም መርከቦች አሁን ሞተራችሁን አንቀሳቅሱ። ነዳጅ መፍሰሱን ይቀጥል።”

    ሁለቱን አገር ስታደራድር የነበረቸው ፓኪስታን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ሼህባዝ ሻሪፍ በኩል ባወጣችው መግለጫ ደግሞ “በተከታታይ ከተደረገ ንግግር በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መካከል ስምምነት ላይ መደረሱን ስናሳውቅ በደስታ ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሁለቱም ወገኖች አሁኑኑ በሁሉም ግንባሮች፣ ሊባኖስን ጨምሮ ቋሚ የሆነ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማቋረጥ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

    “የፊርማ ሥነ ስርዓቱ አርብ ሰኔ 12 በስዊዘርላንድ ይካሄዳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለማቆም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን ለመፈለግ ላሳዩት ቁርጠኝነት እናመሰግናለን።"

    ለድርድሩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ያሏቸውን ኳታርን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ እንዲሁም ቱርክን ጨምረው አመስግነዋል።

    “ከስምምነት ላይ በመደረሱ በዚህ ሳምንት ተከታታይ የሆኑ ስብሰባዎችን እናዘጋጃለን። ይህ የቅድመ ትግበራ ውይይት ዝርዝር ነገሮችን ለመነጋገር እና ለይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓቱ መሠረት የሚጥል ይሆናል”ብለዋል።

    ኢራን በበኩሏ በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ካዘም ጋሪባባዲ በኩል ሁለቱ አገራት ከስምምነት መድረሳቸውን አረጋግጠው አርብ እንደሚፈረም ተናግረዋል።

    “ከአሁን ጀምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ ሊባኖስን ጨምሮ እንደሚቆሙ" ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው፣ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን ላይ የጣለችውን እገዳም እንደምታነሳ አስታውቀዋል።