የኒውክሌር መርሃ ግብር እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውይይት ይደረግባቸዋል- የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለማረጋገጥ እና የፊታችን አርብ በስዊትዘርላንድ ስለሚደረገው ይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓት ለብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ቴህራን አሜሪካ ላይ ስላላት የአመኔታ ችግር በድጋሚ ገልፀው፤ አገራቸው የአሜሪካን ቃል ኪዳኖች አፈፃፀም “እንደምትከታተል” ጠቅሰዋል።
እስራኤል ቤይሩትን ማጥቃቷን ተከትሎ ቴህራን መዛቷ “የስምምነቱን ይዘት እንዲፋጠን ያገዘ እና አንዳንድ ጉዳዮችን የፈታ” እንደነበር ጠቁመዋል።
ምክትል ሚኒስትሩ ኢራን ድርድሩ በ60 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላት ተናግረዋል። በኢራን ላይ የተጣሉ ሁሉም ማዕቀቦች እንዲነሱ እና ከአገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ድርድር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች ውስጥ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በዚህ 60 ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ ጉዳት የደረሰበትን የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ዳግም ለመገንባት የሚያስችሉ ጉዳዮችም የድርድሩ አካል ናቸው ብለዋል።










