ሩሲያ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ
ጦር መርከቦች እና ሌሎች ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሊውል የሚችል መረጃ ለኢራን ማቅረቧን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣናት እንደነገሩት የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገበ።
በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ሆነው ሲቢኤስ ኒውስ
ያነጋገራቸው ሌላ የአሜሪካ ባለሥልጣንም፤ ሩሲያ ዋሽንግተን በቀጣናው ያላትን ይዞታ የተመለከተ መረጃ ለኢራን እያቀረበች መሆኑን
ተናግረዋል።
ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት አሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር
ፒት ሄግሴት በበኩላቸው፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ማን ማንን እያናገረ እንደሆነ ያውቃሉ” ብለዋል።
ኤፒ ያነገጋገራቸው ምንጮች ይህንን ቢናገሩም፤
ሩሲያ መረጃ በማቅረብ የኢራንን እርምጃ እየመራች ነው የሚለው በአሜሪካ
የስለላ መረጃ የተረጋገጠ እንዳልሆነ አክለዋል ተብሏል።
ይህ መረጃ፤ ሩሲያ ከሳምንት በፊት አሜሪካ እና
እስራኤል ኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት የሚጠቁም የመጀመሪያ ምልክት ተደርጎ መወሰዱን ዘገባው ያመለክታል።
በኒውክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት ለረዥም ጊዜ መገለል
ከደረሰባት ኢራን ጋር ወዳጅነታቸውን ካስቀጠሉ አገራት አንዷ ሩሲያ ነች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሄግሴት ከሲቢኤስ
ኒውስ ’60 ሚኒትስ’ የተሰኘው ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ሩሲያ በቀጣናው ስለሚገኘው የአሜሪካ ጦር እንቅስቃሴ ለኢራን
መረጃ እያቀረበች ነው ስለመባሉ ተጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ አሜሪካ “ሁሉንም ነገር
እየተከታተለች” እንዲሁም በውጊያ ዕቅዷ ውስጥ እያካተተች እንደሆነ ተናግረዋል።
“የአሜሪካ ሕዝብ፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ
ማን ማንን እያነጋገረ እንደሆነ እንደሚያውቁ እርግጠኛ መሆን ይችላል” ብለዋል። “በይፋ የሚደረግም ሆነ በጀርባ የሚከወን፤ መፈጠር
የሌለበትን ማንኛውም ነገር እየተጋፈጥን ነው፣ በኃይል እየተጋፈጥነው ነው” ሲሉም ለሲቢኤስ ኒውስ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ማስዑድ ጋር መነጋገራቸው እና ሐዘናቸውን መግለጻቸውን ክሬምሊን አስታውቋል። ሩሲያ የኃይል እርምጃዎች መቆም አለባቸው
የሚል አቋም እንዳላትም ገልጸዋል ተብሏል።
የፑቱን ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ እንደሚያመክተው፤
ሁለቱ አካላት ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ተስማምተዋል።