ትራምፕ ቢቢሲ ላይ ለመሠረቱት ክስ ቃለ መሀላ በመፈጸም ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ታዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Kent NISHIMURA / AFP via Getty Images
የአሜሪካ ዳኛ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢቢሲ ላይ ለመሠረቱት የሥም ማጥፋት ክስ እስከ ታኅሳስ መጀመሪያ ድረስ በቃለ መሀላ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ውሳኔ ሰጡ።
ትራምፕ ቢቢሲ በፓናሮማ ዘጋቢ ፊልም ከካፒቶል ሂል አመፅ በፊት እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ያደረጉትን ሁለት የንግግር ክፍሎችን አያይዞ በመስራቱ ክስ መሥርተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በቃለ መሀላ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ የተያዘላቸውን ቀጠሮ "የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ" በመጥቀስ ሰርዘዋል።
ይሁን እንጂ ቢቢሲን የወከሉ ጠበቆች በቀጠሮ ቀኑ ትራምፕ በጆርጂያ የምርጫ ዘመቻ ላይ እንደነበሩ እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከማክበር ዘመቻውን አስቀድመዋል ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ክስ ሁለቱ ወገኖች ማስረጃ የሚሆኑ የውስጥ እና ሌሎች ሰነዶችን የሚያቀርቡበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
የቢቢሲ ጠበቃ የሆኑት ቻርለስ ቶቢን ሐሙስ ዕለት ለሚያሚ ፍርድ ቤት እንዳሉት ማስረጃ ለማቅረብ በቀሩት ሁለት ወራት ውስጥ ትራምፕ በቃለ መሀላ መመለስ ያለባቸውን ጥያቄ አልመለሱም።
ዳኛ ኤነሪኬ ሊት ትራምፕ እስከ ታኅሳስ 11 ድረስ ጥያቄዎችን መመለስ አሊያም ማዕቀብ ይገጥማቸዋል ብለዋል። ይህም ክሱን ሊያሰርዝ የሚችል ውሳኔ ሊሆን ይችላል።
በአሜሪካ ሕግ በቃለ መሀላ ጥያቄዎችን መመለስ ከፍርድ ቤት ውጭ የሚሰጥ መግለጫ ሲሆን፤ በኋላ ላይ ለፍርድ ቤት ሂደት ለመጠቀም በሚል ይቀረፃል። ሕጋዊ ቅቡልነት ያለውም ሲሆን፤ ቃለ ምልልሱን የፍርድ ቤት ባለሙያዎች ከሰነዱት በኋላ በክስ ሂደቱ እንደ ማስረጃ ይቀርባል።
የቃለ መሀላ ጥያቄ በአመዛኙ ዳኛ በአካል መቅረብ ሳያስፈልግ በጠበቆች ቢሮ የሚደረግ ነው።
በሥም ማጥፋት ክስ ከሁለቱም ወገኖች ጠበቆች ይገኛሉ።
ትራምፕ በተያዘላቸው ቀጠሮ ባለመገኘታቸው ባለፈው ሳምንት ጠበቆች ዳኛው ትራምፕ እንዲገኙ እንዲያስገድዱ ጠይቀዋል።
በቀጠሮው ቀን ትራምፕ በዶልተን ጆርጂያ የመካከለኛ ዘመን የምርጫ ዘመቻ ላይ እና በፍሎሪዳ ማራ ላጎ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ እየተሳተፉ ነበር።
ረቡዕ ዕለት በቀረበ ሌላ አቤቱታ የትራምፕ ጠበቆች ፕሬዝዳንቱ በአዲሱ የጎርጎሮሳዊያን ዓመት ከጥር 11 እስከ 22 ባለው መቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ጠበቆቹ ቢቢሲ ፕሬዝዳንቱ በቃለ መሀላ ጥያቄ ላለመሳተፍ ቀጠሮ እየሰረዙ ነው ማለቱ "ስህተት" ነው ብለዋል።
ትራምፕ በፍሎሪዳ ግዛት የመሠረቱት ክስ ቢቢሲ ሆን ብሎ በተንኮል ሁለት ንግግሮችን ገጣጥሟል በሚል ይከሳል።
ቢቢሲ ለስህተቱ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ለአመፅ ቀጥተኛ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን የሚያመላክት ስህተት ማቅረቡን አምኗል።
ከዚህ በኋላ ድርጅቱ የቀረበው ፕሮግራም የሥም ማጥፋት ህጋዊ መስፈርቶችን አያሟላም፤ ሥርጭቱም በአሜሪካ የለም በሚል ክሱ እንዲዘጋ ጠይቋል።



































