አን ሳን ሱ ቺ ከማረሚያ ቤት ወጥተው በቤት ውስጥ የቁም እስረኛ ሆኑ

በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የማይናማር መሪ አን ሳን ሱ ቺ ከማረሚያ ቤት ወደ ቤት እስር ወጥተው ቤት ውስጥ የቁም እስረኛ ሆኑ።

ከሁለት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ከመሪነት ከተነሱ በኋላ በእስር ላይ ቆይተዋል።

አን ሳን ሱቺ በሳምንቱ መጀመሪያ በናይ ፒ ታው ወደሚገኝ የመንግሥት ህንጻ መወሰዳቸውን የማረሚያ ቤቱ ምንጮች ለቢቢሲ በርማ ተናግረዋል።

ሱቺ ለአንድ ዓመት ያህል ለብቻቸው ታስረው ነው የቆዩት።

የ78 ዓመቷ አዛውንት በወታደራዊ ፍርድ ቤት የ33 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

አን ሳን ሱቺ ከሁለት ዓመት በላይ ስለታሰሩበት ሁኔታም ሆነ ወደ ቁም እስር ስለመዛወራቸው በይፋዊ መልኩ የተሰጠ መግለጫ የለም።

ሆኖም አገሪቷ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመረጠቻቸውን ሱ ቺ እንዲፈቱ በርካታ ጥሪ ሲቀርብላቸው ለነበሩት ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንደ አዎንታዊ ሁኔታም ታይቷል።

ሱ ቺ በህመም ላይ ናቸው ተብሎ ቢነገርም የአገሪቱ ጦር ሠራዊት እነዚህን ሪፖርቶች አስተባብሏል።

ሆኖም ሱቺ የታሰሩበት የናይ ፒ ታው ማረሚያ ቤት ምንጭ ለቢቢሲ በርማ እንዳረጋገጡት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ባለንበት ወር ሱቺን መጎብኘታቸውን ቢናገሩም፣ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በተጨማሪም የጦሩ ሠራዊቱ ባለሥልጣናት በሱቺ እና በታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መካከል ውይይት አዘጋጅተው እንደነበር ቢቢሲ በርማ ቢዘግብም ጉዳዩን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

በማይናማር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ አገሪቱ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገብታ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በጦሩ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም የተነሳውን ሁከት ማስቆም አላስቻለውም።

የ78 ዓመቷ የሰላም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሱ ቺ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት በቤት ውስጥ እስር ቢቆዩም በኋላ በመዲናዋ ወደሚገኝ ማረሚያ ቤት ተወስደው ብቻቸውን እንዲታሰሩ ተደርገዋል።

ሱ ቺ የቀረበባቸውን የሙስና ወንጀል ክሶች ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የፍርድ ቤቱን ሂደት ቀልድ ሲሉም አውግዘውታል።