አን ሳን ሱ ኪ ተጨማሪ 7 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ተፈረደባቸው

የማይናማር የጦር ፍርድ ቤት አን ሳን ሱ ኪ ለተጨማሪ 7 ዓመታት በእስር እንዲያስልፉ ፈረደባቸው።

ይህም የቀድሞ የማይናማር መሪ በእስር እንዲያሳልፉ የተፈረደባቸውን ዓመታት ወደ 33 ከፍ ያደርጋል።

ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የአገሪቱ ጦር በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡትን አን ሳን ሱ ኪን በኃይል ገልብጦ ስልጣን ከያዘ በኋላ ፖለቲከኛዋ በቁም እስር ላይ ቆይተው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ አን ሳን ሱ ኪ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር።

መሪዋ ዛሬ አርብ በቀረበባቸው አምስተኛ እና የመጨረሻ ክስ በጦር ፍርድ ቤት ቀርበው ብይን ተሰጥቶባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ሳን ሱ ኪ ለአንድ ሚንስትር ለመንግሥት ስራ የሚውል ሄሊኮፍተር ሲከራዩ መመሪያዎችን አልተከተሉም በሚል በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

ሳን ሱ ኪ ከዚህ ቀደም የኮቪድ ክልከላዎችን በመተላለፍ፣ መገናኛ ራዲዮችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እና የሚስጥር አጠባበቅ መመሪያን መጣስ የሚሉትን ጨምሮ በ14 ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው ነበር።

ሳን ሱ ኪ የቀረቡባቸውን ክሶች ያጣጥላሉ። በዚህ ዓመት የተደረጉ የችሎት ውሎዎች ሕዝቡ እና መገናኛ ብዙሃን እንዳይከታተሉ ተከልክሏል።

የፖለቲከኛዋ ጠበቆችም ለመገናኛ ብዙሃን እንዲናገሩ አይፈቀድላቸውም።

የ77 ዓመቷ አን ሳን ሱ ኪ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ለረዥም ጊዜ በማይናማር መዲና ለቁም እስር ተዳርገዋል።

የፖለቲካ እስረኞች መብት ተሟጋች የሆነ ተቋም እንደሚለው ከሆነ የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት ካደረገ በኋላ የሳንሱኪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት የሆኑ 16ሺህ 600 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን እስካሁን ድረስ 13ሺህ የሚሆኑት እስር ላይ ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንት የመንግሥታቱ የጸጥታው ምክር ቤት በማይናማር ግጭት እንዲቆም እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር።

በጸጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ እና ቻይና ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ጦሩ በምርጫ ስልጣን የያዘን መንግሥት ገልብጦ ወንበር ላይ መቀመጡ በማይናማራ ለበርካታ ቀናት የዘለቀ ተቃውሞ አስከትሎ ነበር።

ጦሩ ከፍርድ ውጪ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል እና መንደሮች ላይ የአየር ጥቃቶችን በመሰንዘር ክስ ይቀርብበታል።

እስካሁን ድረስ ከ2ሺህ 600 በላይ ሰዎች የጦሩን አገዛዝ በመቃወማቸው ሳይገደሉ አይቀርም ተብሎ ይገመታል።