በሩሲያ የወረርሽኝ ተመራማሪ መሞቷን ተከትሎ አሜሪካ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለች ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በሳይቤሪያ በሚገኝ የወረርሽኝ ምርምር ማዕከል ውስጥ የላብራቶሪ ቴክኒሺያን የሆነች ሩሲያዊት መሞቷን ተከትሎ አሜሪካ ሁኔታውን "በጣም በጥንቃቄ" እየተከታተለች መሆኗን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለፁ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደግሞ ክስተቱ የሳንባ ምች ወረርሽኝ መስፋፋትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት ዋሽንግተን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች እንደምትገኝ ተናግረዋል። ሆኖም አሁን ላይ ምንም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ አክለዋል።
ተመራማሪዋ የሞተችው "ምክንያቱ ባልታወቀ የሳንባ ምች" መሆኑን የገለፁት የኢርኩትስክ አስተዳዳሪ፣ ከግለሰቧ ሥራ ጋር የተያያዙ "ምንም አይነት ረቂቅ ህዋሳት" በተወሰደው የሟቿ ናሙና ውስጥ አልተገኙም ብለዋል።
ግለሰቧ ለበሽታው የተጋለጠችው ለምርምር የተዘጋጀውን በበሽታው ውህድ የተሞላ የቤተ ሙከራ ቱቦ ከሰበረች በኋላ አሊያም ወረርሽኙ በተፈጥሮ በዱር አይጦች መካከል የሚገኝበት አካባቢ ካደረገችው የመስክ ጉዞ በኋላ እንደሆነ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ምናልባትም ወረርሽኙ ከሩሲያ ሊስፋፋ የሚችልበትን አደጋ ከመከላከል አንጻር ዋሽንግተን ምን እርምጃ እንደምትወስድ የተጠየቁት ትራምፕ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ "ከክሬምሊን ጋር አልተነጋገርኩም" ብለዋል።
"ይህ ችግር ሲያጋጥማቸው ማየት አልወድም" ያሉት ትራምፕ፣ "እኛ ግን ድጋፍ እናደርጋለን፤ እንዲህ ያለ ችግር ያጋጠማቸውን ሁሉ ሁልጊዜ እንረዳለን" ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የኢርኩትስክ አስተዳዳሪ ኢጎር ኮብዜቭ፣ ከላብራቶሪ ቴክኒሺያኗ ሞት በኋላ የሕክምና እርዳታ ፈልገው የቀረቡ ሌሎች የተቋሙ ሰራተኞች አለመኖራቸውን ገልፀዋል።
የሩሲያ የሸማቾች እና የጤና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የባዮሎጂካል ደኅንነት ቡድን በኢርኩትስክ የሚገኘውን "የሳይቤሪያና የሩቅ ምሥራቅ ፀረ-ወረርሽን ተቋም" መመርመሩን እና ምንም ዓይነት የድንገተኛ አደጋ ሁኔታ እንዳልተገኘ አስታውቋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ ሕዝቡ "የተለያዩ ወሬዎችን ከመስማት እንዲቆጠቡ" እና የሩሲያ በሸማቾች እና ጤና ቁጥጥር ባለስልጣኑ ሮስፖትሬብናድዞር የሚሰጡ መግለጫዎችን እንዲከታተሉ አሳስበዋል።
ከሟቿ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው የሚታወቁ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ለጥንቃቄ ሲባል በሕክምና ክትትል ሥር እንደሚገኙ የሩሲያ ሚዲያዎች ባለፈው ሳምንት ዘግበዋል።
"በሩሲያ ስለተጠረጠረው የወረርሽን ጉዳይ አዲስ መረጃ ይኖር እንደሆን" በአንድ ጋዜጠኛ የተጠየቁት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ "እንደሚታወቀው የላቦራቶሪው አንድ ሠራተኛ ተይዛለች፤ እናም በሽታው ቢያንስ እዚያው ውስጥ ሊዛመት ይችል ይሆናል የሚል ስጋት አለ። በዚህ ምክንያት አግልሎ የማከም እርምጃዎች ሲወሰዱ አይታችኋል" ብለዋል።
"እንደዚህ ያለ ነገር ከቁጥጥር ውጭ ከወጣ በፍጥነት ሊዛመት ይችላል። ስለዚህ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልንና ቁጥጥር እያደረግን ነው። ለፍርሃት የሚዳርግ ሁኔታ ነው ብዬ አላስብም፣ ነገር ግን ትኩረት የሚሻ እና ዐይናችንን እንድንጥልበት የሚያደርግ ጉዳይ ነው፤ እኛም ይህንኑ እያደረግን ነው።"
በበሽታው ህይወቷን ያጣችው ሴት፣ እድሜዋ በ20ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነበር። በቅርቡ ሞንጎሊያ ድንበር አጠገብ ወደሚገኘው የቡርያቲያ ክልል ተጉዛ እንደነበር ተገልጿል።
ወረርሽኙን የሚያስከትለው 'የርሲኒያ ፔስቲስ' በመባል የሚታወቀው ባክቴሪያ፣ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአውሮፓ ሕዝብ ግማሽ የሚሆነው እንዲሞት አድርጓል።
ወረርሽኙ በወቅቱ "ጥቁር ሞት" በመባል ይታወቅ ነበር። ይህ ባክቴሪያ በአካባቢው በሚገኙ እንደ ማርሞት ያሉ የአይጥ ዝርያ እንስሳት ውስጥ ይገኛል።
ከ100 ዓመታት በፊት የተመሰረተው "የሳይቤሪያና የሩቅ ምሥራቅ ፀረ-ወረርሽኝ ተቋም" በአውሮፓውያኑ በ1920ዎቹ ለተከሰተ ወረርሽኝ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ ነው።



































