በካይሮ የነዳጅ ቦቴ ተገልብጦ በተነሳ ከፍተኛ እሳት 31 ሰዎች ሞቱ

የነዳጅ ማመላለሻ ታንከሩ አውራ ጎዳናውን የሚከፍለውን መካከለኛ ክፍል አቋርጦ ከገባ በኋላ ተገልብጦ በእሳት መያዙን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የምስሉ መግለጫ, የነዳጅ ማመላለሻ ታንከሩ አውራ ጎዳናውን የሚከፍለውን መካከለኛ ክፍል አቋርጦ ከገባ በኋላ ተገልብጦ በእሳት መያያዙን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በሚገኝ የተጨናነቀ አውራ ጎዳና ላይ የነዳጅ ቦቴ ተገልብጦ በተነሳ ከፍተኛ እሳት 31 ሰዎች ሲሞቱ፣ 21 ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ረቡዕ ምሽት ከጥንታዊው የከተማዋ ማዕከል በስተሰሜን በሚገኘው የዋራቅ ሰፈር ቀለበት መንገድ ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በአቅራቢያው የሚገኙ ሆስፒታሎች፣ በቃጠሎ እና በጭስ መታፈን ጉዳት የደረሰባቸውን ታካሚዎች እያከሙ ይገኛሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ምስሎች በምሽቱ ሰማይ ላይ ከፍ ብሎ የሚታይ የእሳት ነበልባል እና ጥቁር ጭስ አሳይተዋል። በአቅራቢያው የነበሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ሲቃጠሉ እንደነበር ይታያል።

ባለስልጣናት እሳቱ እንዴት እንደተነሳ እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባይሰጡም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ግን የነዳጅ ቦቴው ተገልብጦ በአቅራቢያው በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ቤንዚን በማፍሰሱ ቃጠሎው መከሰቱን ዘግበዋል።

የአካባቢው ዓቃቤ ሕግ በአደጋው ዙሪያ ምርመራ የጀመረ ሲሆን ከሟቾቹ አስከሬን ላይ የዲኤንኤ ናሙና እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የግል ተቋራጭ ንብረት የሆነው የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪ በአውራ ጎዳናው ላይ በመጓዝ ላይ እያለ ከፍተኛ ኃይል ያለው የኤሌክትሪክ ገመድ ፊት ለፊቱ በመውደቁ አሽከርካሪው መኪናውን መቆጣጠር እንዳቃተው አል አህራም ጋዜጣ ለምርመራው ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

በመቀጠልም ተሽከርካሪው የመንገዱን አካፋይ በመዝለል ተገልብጦ በእሳት መያያዙን የመንግሥት ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።

ግብጽ ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ የእሳት አደጋዎችን ያስተናገደች ሲሆን መደበኛ ያልሆኑ የመኖሪያ አካባቢዎች እና ያረጁ መሰረተ ልማቶች ለአደጋዎቹ መበራከት ምክንያት ሆነዋል።

በተጨማሪም ሰፊ በሆነችው ካይሮ ጭምር የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ላይ መዘግየት መኖሩ እና በአካባቢው ነዋሪዎች የሚደረጉ ያልተደራጁ የነፍስ አድን ጥረቶች ሁኔታውን የበለጠ ውስብስብ ያደርጉታል።

ከስፍራው የወጡ ምስሎች የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መግቢያ መንገዶችን በመዝጋት እሳቱን ካጠፉ በኋላ ብዙ ሕዝብ በአውራ ጎዳናው ላይ ተሰብስቦ ያሳያሉ።

ከቦታው የተነሱ ምስሎች፣ እሳቱ ከጠፋ በኋላ በዋናው መንገድ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ያሳያሉ።
የምስሉ መግለጫ, ከቦታው የተነሱ ምስሎች፣ እሳቱ ከጠፋ በኋላ በዋናው መንገድ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ያሳያሉ

የጤና ሚኒስቴሩ ለእሳት አደጋው ምላሽ ለመስጠት 39 አምቡላንሶች መሰማራታቸውን ገልጿል።

በግብፅ የመንገድ ላይ የሚፈጠሩ የተሽከርካሪ ግጭቶች የተለመዱ ሲሆኑ ይህም ብዙውን ጊዜ በቂ ጥገና ካለመደረግ እና የትራፊክ ህጎችን በስፋት ካለማክበር ጋር ይያያዛል።

ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው ዓመት በግብፅ መንገዶች ላይ ወደ 6,000 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት አጠቃላይ ቁጥር በበርካታ መቶዎች ብልጫ አለው።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አውራ ጎዳናውን በማጽዳት ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ማድረጋቸውን የመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንኤምኤ ዘግቧል።