የእስራኤል ጦር በሄብሮን የሚገኙ የፍልስጤማውያን ሕንጻዎችን ማፍረስ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
የእስራኤል ጦር ሁለት የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤም ታጣቂዎች ከተገደሉ በኋላ በሄብሮን ከተማ የሚገኙ የፍልስጤም ሕንፃዎችን ማፍረስ ጀመረ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦሩ ሁለቱ ታጣቂዎች የመጡበትን ሰፈር "ያወድማል"፤ እስራኤልም በወረራ በያዘችው የዌስት ባንክ "ሰፊ እርምጃ" ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት ታጣቂዎቹ ከመገደላቸው በፊት ከሄብሮን ውጭ በሚገኝ የፍተሻ ኬላ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ሌሎች ሦስት ወታደሮች ቆስለዋል።
ይህ የሆነው አክራሪ የአይሁድ ሰፋሪዎች የወይራ ፍሬ በሚሰበሰብበት ወቅት ፍልስጤማውያንን ዒላማ እያደረጉ ባለበት እንዲሁም የእስራኤል አጠቃላይ ምርጫ አራት ቀናት በቀሩት ወቅት ነው።
በቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል በወታደሮች እና በታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ያሳያል። ሌላ ቪዲዮ ደግሞ ሁለት ታጣቂዎች ሽጉጥና ጠመንጃ ይዘው ከመኪና ሲወርዱ እና በፍተሻ ኬላ ላይ ወታደሮች ላይ መተኮስ ሲጀምሩ ያሳያሉ።።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ይህ ክስተት በምርጫ ዘመቻው ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የጀመረ ሲሆን ኔታንያሁ የሊኩድ ፓርቲያቸው አርብ ጠዋት ላይ የጀመራቸውን የምርጫ ዘመቻዎች እንደሚሰርዝ ተናግረዋል።
በኋላ ላይ ኔታንያሁ ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ ጦር "ይህን ቦታ አፍርሰው ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይሩት" ተናግረዋል፤ ይህም አጥቂዎቹ የመጡበት የሄብሮን ሰፈርን ያመለክታል።
የእስራኤል ኃይሎች ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ፍልስጤማውያንን ቤቶች ማፍረሳቸው የተለመደ ነው።
ይህንን የእስራኤል ድርጊት የመብት ተሟጋች ቡድኖች የጋራ ቅጣት በማለት ይተቹታል።
ኔታንያሁ እቅዳቸውን ቀደም ሲል በዌስት ባንክ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ የመኖሪያ ሕንፃዎች ፈርሰው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው ከነበሩበት ጋር አመሳስለውታል።
በተጨማሪም በዌስት ባንክ ውስጥ በአስርተ ዓመታት ውስጥ ትልቅ ነው ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ማቀዳቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ይህ እቅድ መቼ ሊተገበር እንደሚችል አልገለፁም።
200,000 አካባቢ ነዋሪዎች ባሏት በሄብሮን ከተማ እና በአቅራቢያዋ በምትገኘው ሃልሁል ከተማ ዙሪያ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል ብለዋል።
የኔታንያሁ የቀኝ ክንፍ የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪክ እስራኤል በዌስት ባንክ "ልክ እንደ ጋዛ ወይም ሊባኖስ" ዘመቻ እንድትጀምር ጥሪ አቅርበዋል።
የቀኝ ክንፍ ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጂቪር ደግሞ እስራኤል የፍልስጤምን መንግሥት እንድታፈርስ ጠይቀዋል።
ሐሙስ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከምርጫው በፊት ኔታንያሁን በመተቸት መንግሥትን እያዳከሙ ነው ሲሉ ከስሰዋል። ወደፊትም በአገሪቱ ላይ ለሚሰነዘረው ማንኛውም ጥቃት "ኃላፊነት የሚወስዱት" እነርሱ ናቸው ብለዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለተገደሉት ወታደሮች ቤተሰቦች ሀዘናቸውን ገልጸው አጥቂዎቹን የገደሉትን አሞካሽተዋል።
የእስራኤል ጦር፣ በታጣቂዎቹ ተሽከርካሪ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥይት ማግኘቱን አስታውቋል።
ታጣቂዎቹ በአቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም አስበው እንደነበር፣ ነገር ግን የፍተሻ ኬላ ሲያጋጥማቸው እዚያው ተኩስ ለመክፈት ወስነዋል ተብሎ እንደሚታመን እስራኤል ጦር ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በዌስት ባንክ በእስራኤል ኃይሎች ወይም ሰፋሪዎች ቢያንስ 96 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው፣ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ አራት እስራኤላውያን በፍልስጤማውያን መገደላቸውን አስታውቋል። ይህ ቁጥር አርብ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት የተገደሉትን አይጨምርም።































