ትራምፕ 300 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች በቺካጎ እንዲሰማሩ አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቺካጎ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ወንጀል ሲሉ የገለፁትን ሁኔታ የሚቆጣጠሩ 300 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ለማሰማራት ትዕዛዝ ሰጡ።
እርምጃው የመጣው የኢምግሬሽን ባለሥልጣናት በዲሞክራቶች በሚመራው ከተማ ተቃውሞ ማስተናገዳቸውን እና ተሽከርካሪያቸው ሆን ተብሎ ከተገጨ እና አንድ የታጠቀች ሴትን ተኩሰው መምታታቸውን በተናገሩ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ለሳምንታት በርካታ ግዛቶች እና መሪዎቻቸው የትራምፕ ወታደር የማሰማራት ዕቅድ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እንደሆነ ሲገልፁ ቆይተዋል።
የኢሉኖይ ግዛት አስተዳዳሪ ጄቢ ፕሪትዝከር ትራምፕ "ቀውስ ለመፈብረክ እየሞከሩ ነው" ብለዋል።
ወታደር የማሰማራት ዜናው የተሰማው ሌላኛው ለዘብተኛ ግዛት የሆነው ኦሪገን ፖርትላንድ የሚገኙ የፌደራል ዳኛ የትራምፕ አስተዳደር በግዛቱ 200 ወታደሮችን ለማሰማራት የያዘውን ዕቅድ ውድቅ ካደረጉ በኋላ ነው።
ዳኛ ካሪን ኢመርጉት ትራምፕ ስለ ፖርትላንድ ያወጡትን መግለጫ "ከእውነታው ጋር ያልተገናኘ" ያሉት ሲሆን፤ እርምጃው ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው ብለዋል።
ካለ ኢሪገን ግዛት ፈቃድ አለመረጋጋትን በወታደራዊ መንገድ ለመፍታት የሚወሰድ እርምጃ የግዛቱን እና የሌሎችን ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።
እርምጃው በከተማዋ ውጥረቱን የሚያባብስ እና ተቃውሞዎች እንዲጨምር የሚያደርግ ነው ሲሉም አክለዋል።
የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ቺካጎ መድረሳቸው እስካሁን ግልፅ ባይሆንም፤ እርምጃውን በሕግ ለመታገል ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ አይቀርም።
ቺካጎ በዲሞክራቶች በሚመሩ ከተሞች በአወዛጋቢው የወታደር ማሰማራት እንቅስቃሴ ዋሽንግተን፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሜንፈስ እና ፖርትላንድን በመከተል ዒላማ ውስጥ የገባች አዲሷ ከተማ ሆናለች።
ወታደር ማሰማራቱ ሕጋዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች የተነሱበት ሲሆን፤ የብሔራዊ ዘብ ወታደሮች በተለምዶ በግዛት አስተዳዳሪዎች የሚሰማሩ ናቸው።
መንግሥት የአሜሪካን ጦር ለአገር ውስጥ ጉዳዮች ማሰማራትን ክፍለ ዘመን የተሻገረ ሕግ ይከለክላል።
ቺካጎ የኢምግሬሽን ሕግ አፈፃፀም ምክንያት በርካታ ተቃውሞችን ያስተናገደች ሲሆን፤ አብዛኞቹ የተቃውሞ ሰልፎች በአሜሪካ የኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቢሮዎች ላይ ተካሂደዋል።
ቅዳሜ ዕለት የትራምፕ ወታደሮችን ለማሰማራት ትዕዛዝ ከመስጠታቸው በፊት የአሜሪካ የድንበር ጥበቃ አባላት ከተቃዋሚዎች ጋር መጋጨታቸውን የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት አስታውቋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ትራምፕ ወታደራዊ መኮንኖችን ሲያነጋግሩ በአሜሪካ ከተሞች ላይ እየተደረገ ስላለው የወታደሮች ስምሪት ጠቅሰዋል።
ለጦር መሪዎቹ የአሜሪካ ከተሞች ለወታደሮች "የውስጥ ጠላቶችን" ለመዋጋት እና አለመረጋጋትን ለማስቆም "የስልጠና መስክ" እንዲሆኑ ያላቸውን ፍላጎት ተናግረዋል።
ቺካጎን ጨምሮ በዲሞክራቶች የሚመሩ ከተሞች "በጣም ደኅንነት የሌለባቸው ስፍራዎች ናቸው፤ አንድ በአንድ እንፈታቸዋለን" ብለዋል።
ትራምፕ ወንጀልን እና የተኩስ ልውውጦችን በመጥቀስ ለአንድ ወር ያህል ወደ ችካጎ ወታደሮችን እንደሚልኩ ሲዝቱ ቆይተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በቺካጎ አሰቃቂ ወንጀሎች በጣም እንደቀነሱ መረጃዎች ያሳያሉ። ከጥር እስከ ሰኔ ባሉት ወራት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የግድያ መጠን በአንድ ሦስተኛ መቀነሱን የወንጀል ፍትህ ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ ከሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ጋር ሲነፃፀር አጠቃላይ ወንጀል በቺካጎ ከአመካኙ በላይ ነው።















