በሁለቱ የኢሕአፓ ፖለቲከኞች እና በጠበቃ አበራ ላይ "ታጣቂዎችን ሲያደራጁ ነበር" የሚል ተጨማሪ ክስ ቀረበባቸው

የፎቶው ባለመብት, Ezema/yishak welday
በሽብር የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞች አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም በጠበቃ አበራ ንጉሥ፣ ከ "ፅምዶ" እና ሌሎች ታጣቂዎች ጋር አላቸው ከተባለው ግንኙነት በተጨማሪ በዘይሴ ብሔረሰብ ውስጥ "ታጣቂ ኃይሎችን ሲያደራጁ ነበር" ሲል ፖሊስ ገለፀ።
ሦስቱ ተጠርጣሪዎች "ፅምዶ" ከሚባለው ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ እና ከታጣቂዎች ጋር አላቸው ከተባለው ግንኙነት በተጨማሪ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በዘይሴ ብሔረሰብ ውስጥ "ታጣቂ ኃይሎችን ሲያደራጁ" እንደነበር ፖሊስ በማስረጃ ስለማረጋገጡ ገልጿል።
ፖሊስ ተጨማሪውን ከባድ ክስ ያቀረበው፣ ፍርድ ቤት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ነው።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሰኞ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም. ለዋለው ችሎት ባቀረበው በዚሁ ማመልከቻው፣ በፍርድ ቤቱ በተሰጠው የ12 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ አከናወንኳቸው ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።
ተጠርጣሪዎቹ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ ዙሪያ በሚገኘው የዘይሴ ብሔረሰብ ውስጥ "ታጣቂ ኃይሎችን ሲያደራጁ የነበሩ መሆኑን በማስረጃ የማረጋገጥ ሥራ ሠርተናል" ሲል ፖሊስ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ እስከተያዙበት ቀን ድረስ "ጫካ ያሉ ፀረ-ሰላም ኃይሎች" ካላቸው አካላት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በስልክ ሲገናኙ እንደነበር ጠቅሷል።
ቢቢሲ የተመለከተው ይህ የፖሊስ ሪፖርት "ተከባብረው እና ተዋደው የሚኖሩ የዘይሴ ብሔረሰብን እና ሌሎች ብሔረሰቦችን እርስ በእርስ ለማጋጨት እየሠሩ ነበር" ሲል ተጠርጣሪዎቹን ወንጅሏል።
በዘይሴ ብሔረሰብ ዘንድ ከሚነሳው የአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተገናኘ በአካባቢው የፀጥታ መደፍረስ እና የሰዎች ሞት ሲከሰት እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ወገኖች ሲገለጽ ቆይቷል።
በተለይም በትግራይ ኃይሎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል በተፈጠረውን ውጥረት ሳቢያ፥ በአካባቢው የነበሩ የፌደዴራል የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግጭቶች እና ጉዳቶች ተስተውለዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ለችሎት በጻፈው ማመልከቻ ላይ፣ "በአካባቢው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ሳይኖር የዘይሴ ብሔረሰብ [አባላት] በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተጨፍጭፈዋል በማለት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አሠራጭተዋል" ሲል ተጠርጣሪዎቹን ወንጅሏል። ይህንንም "ሕዝብና መንግሥትን የማጋጨት እንቅስቃሴ ነው" ሲል ፈርጇል።
ከዘይሴ ብሔረሰብ ጋር በተገናኘ የቀረበው ውንጀላ፣ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ያልተጠቀሰ አዲስ ውንጀላ ነው።
ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም በቁጥጥር ስር በዋሉት በሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው ላይ ከዚህ ቀደም የቀረቡት የሽብር ወንጀሎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የፀጥታ ተቋማት እና በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ "የሽብር ጥቃት" ለመፈፀም በመንቀሳቀስ እንዲሁም ከህወሓት፣ "ፅምዶ" ተብሎ ከሚጠራው ኃይል እና በስም ያልተጠቀሱ ሌሎች "ፀረ-ሰላም ኃይሎች" ጋር ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ መጠርጠራቸውን የሚያብራራ ነበር።
ፖሊስ ዓርብ ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም በጻፈው በአዲሱ ማመልከቻው ላይም ተጠርጣሪዎቹን "በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ፅምዶ ብሎ ከሚንቀሰቀሰው ፀረ-ሰላም ኃይል ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መሆኑን በማስረጃ አረጋግጫለሁ" ብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ እና ጠበቆቻቸው በበኩላቸው፣ ከዘይሴ ብሔረሰብ ጋር በተገናኘ የተነሱ ውንጀላዎችን በፖሊስ የመጀመሪያ ሪፖርት ላይ ያልተጠቀሱ አዲስ ውንጀላዎች በመሆናቸው ውድቅ እንዲደረጉ ችሎቱን መጠየቃቸውን ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም በዘይሴ አካባቢ ምን ዓይነት "ፅንፈኛ እና ፀረ-ሰላም የታጠቀ ኃይል" እንዳለ እና ተጠርጣሪዎቹ ከታጣቂዎቹ ጋራ "ምን ያገናኛቸዋል" የሚሉ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ለፖሊስ ማንሳቱን ገልፀዋል።
ፖሊስ በሰጠው ምላሽ በስፍራው የታጠቁ ኃይሎች እንዳሉ እና "ታጣቂዎቹ የፈፀሟቸውን ጥቃቶች" መንግሥት እንደፈፀመ በመግለፅ፣ በተለይም ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ አበበ አካሉ "ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ አሠራጭተዋል" ማለቱን ጠበቃው አስረድተዋል።
በመቀጠልም በቀደመው ችሎት ላይ በተሰጠው የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የአንድ ሰው የምስክርነት ቃል መቀበሉን የጠቀሰው ፖሊስ፣ ነገር ግን በርካታ የምርመራ ሥራዎች እንደሚቀሩት ገልጿል።
ከእነዚህም መካከል የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ከጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን ማስመጣት፣ ወደ ስፍራው የተላከ የምርመራ ቡድን የሚያመጣውን ማስረጃ መጠበቅ፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና ከባንኮች ማስረጃዎችን ማስመጣት የሚሉት ይገኛሉ።
በመሆኑም የምርመራ ሥራውን ለማጠናቀቅ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ዛሬ ጠዋት በነበረው ችሎት ላይ ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ከእስር ቢለቀቁ በምስክሮቹ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ስጋቱን ገልጿል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው የፖሊስን ጥያቄ መቃወማቸውን አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል።
ፖሊስ አስመጣለሁ የሚላቸው ማስረጃዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ካሉ ተቋማት መሆኑን በማንሳት፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢፈቱ "ከተቋማት የሚመጡ ሰበዶችን ሊያጠፉ እና ሊሰውሩ የሚችሉበት ሥልጣን የላቸውም" በሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ "በምርመራው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ" በሚል ዋስትና እንዳይሰጥ መጠየቁ "አግባብ አይደለም" በሚል መከራከራቸውን ጠበቃው አክለዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ፣ ከሰዓት በነበረው ውሎ ለፖሊስ ተጨማሪ 10 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለነሐሴ 21/2018 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።















