ከባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚሰራበት እና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የቻይና "የወፍራሞች እስር ቤት"

የፎቶው ባለመብት, TL Huang
ቻይናውያን በትልቅ የስፖርት አዳራሽ ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ለምግብ ሲሰለፉ እና አልጋዎች በረድፍ በተደረደቡባቸው 'ዶርሞች' ውስጥ ሲተኙ የሚሳዩ ምስሎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተለቀቁ ነው።
እነዚህ የአካል ብቃት መጠበቂያዎች የቅንጦት ስፓ ያለባቸው ስፍራዎች ሳይሆኑ በቻይና ውስጥ የሚገኝ ወታደራዊ መሰል የክብደት መቀነሻ ካምፖች ናቸው።
አንዳንዶች "የወፍራሞች እስር ቤቶች" በማለት የሚጠሯቸው እነዚህ ካምፖች ውስጥ ያሉ ሕጎች ጥብቅ ናቸው። ማቆያ የሚሆኑ ቀላል ምግቦችን መመገብ ክልክል ነው፤ የሰውነት ክብደትን በቀን ሁለት ጊዜ መመዘን ግዴታ ነው።
ዓለም አቀፉ ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት ቀውስ ባጋጠማት ቻይና ውስጥ ከ100 ሺህ በላይ እንዲህ ዓይነት ካምፖች እንደሚገኙ የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል።
600 ዶላር የሚከፍሉ ሰዎች መኝታ፣ ምግብ እንዲሁም በየቀኑ የሚሰራ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ያገኛሉ።
በኢንስታግራም ገጿ ላይ ልምዷን የምታጋራው ቲኤል ሁአንግ፤ ለ28 ቀናት ካምፑን ለቅቃ እንዳትወጣ ተደርጋ ስለነበር እና ክብደቷን በየጊዜው እድትከታተል ትገደድ ስለነበር "እስር ቤት ውስጥ እንዳለች" እንደተሰማት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"አሠልጣኞቻችን ይቆጣጠሩናል፤ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን በድብቅ አለማስገባታችንን እና በሁሉም ክፍለ ጊዜዎቻችን መገኘታችንን ያረጋግጣሉ። ያለ አሳማኝ ምክንያት ክፍለ ጊዜዎችን ማቋረጥም ሆነ ካምፑን ለቅቆ መውጣት አይፈቀድልንም ነበር" ብላለች።
ሁአንግ ይሄ ዘዴ ውጤታማ ሆኖ ብታገኘውም የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ግን እንዲህ ዓይነት ጫፍ የረገጡ አካሄዶች ከፍተኛ አካላዊ ሥነ-ልቦናዊ አደጋዎች እንዳሏቸው ያስጠነቅቃሉ።
የአካል ብቃት አሰልጣኝ እና የሥነ-ምግብ ባለሙያው ሉክ ሃና "አንዳንድ ካምፖች በቀን አንድ ኪሎ ግራም ክብደት መቀነስን ግብ አድርገው ይይዛሉ። ይህም ግብ በሕክምና ባለሙያዎች ክትትል ለሚደረግላቸው አዋቂ ሰዎች እንኳ ከሚመከረው ለአደጋ የማያጋለጥ የክብደት መቀነስ መጠን በብዙ የበለጠ ነው" ይላል።
ታድያ እነዚህ ካምፖች የሚሠሩት እንዴት ነው? እንዴትስ ታዋቂ ሊሆኑ ቻሉ?
"የለውጥ ጊዜው አሁን ነው"

የፎቶው ባለመብት, TL Huang
ሁአንግ ስለእነዚህ ካምፖች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችው ቻይናዊት ከሆነችው እናቷ ነው። ብቻዋን ወደ ቻይና ከተጓዘች በኋላ "እጅግ ጤነኛ ያለመሆን" ስሜት እየተሰማት እንደነበር የምትናገረው ሁአንግ፤ ባደረገችው ጉዞ ምክንያት የዘውትር ልምዷ እንደተዛባ እና በ'ዴሊቨሪ' የሚመጡ ምግቦችን በብዛት ስትመገብ እንደነበር ታስረዳለች።
በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ኪሎ ገደማ በመጨመሯ ከዘመዶቿ ትችት አዘል አስተያየቶች ሲሰጣት ነበር። እነዚህ አስተያየቶች "ለመለወጥ ጊዜው አሁን ነው" የሚል ስሜት እንደፈጠረባት ትናገራለች።
"የውፍረት ማሸማቀቅ እየደረሰብኝ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። በተመሳሳይ ጊዜም ደግሞ ለእኔ ካላቸው መልካም አሳቢነት በመነጨ ግሳጼ ያለው ፍቅር እየሰጡኝ እንደሆነም ገምቻለሁ" ትላለች።
ወደ ካምፑ መግባት የልምድ መለወጥ የሚያስከትው ከፍተኛ ድንጋጤ (culture shock) ቢፈጥርባትም፤ በጋራ ክብደት ለመቀነስ በተሰባሰቡት ሰዎች መካከል ጠንካራ የጓዳዊነት ስሜት ተፈጥሮ እንደነበር ታስታውሳለች።
ቀናቸው የሚጀመረው ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ተነስተው ክብደታቸው በመመመዘን ነው። ከፍተኛው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለአራት ሰዓት ይሰራሉ። በሳይክል መሰል መሳሪያ ላይ እግር ማንቀሳቀስ፣ በሚያነጥር ስፖንጅ ላይ መንጠር ለአጭር ደቂቃዎች የሚቆዩ ግን ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና ክብደት ማንሳት ከሚሠሯቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ናቸው።
ቁርሳቸውን የሚበሉት አራት የተቀቀለ እንቁላል፣ ግማሽ ቲማቲም እና ሁለት ቁራጭ ኪያር ሊሆን ይችላል። ሁአንግ የሚቀርብላቸው ምግብ "ጥሩ፣ የተመጣጠነ እና የዕለት ተዕለት የቻይና ምግቦችን ለመተካት ታስቦ የተዘጋጀ" እንደሆነ ገልጻለች።
ተሳታፊዎቹ ራት ከመመገባቸው አስቀድሞ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል ላይ በድጋሚ ይመዘናሉ። ሰውነታቸውን ታጥበው መተኛት የሚፈቀድላቸው ከዚህ በኋላ ነው።
ሁዋንግ ወደ ካምፑ በገባችበት መጀመሪያው ሳምንት ሁኔታው "በጣም አዲስ" ሆኖባት የነበረ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ለተጨማሪ ሦስት ሳምንታት መቀጠል እንዳለባት ተገንዝባለች። ከጓደኞቿ ጋር መጻጻፍ ቆይታዋን እንድትቀጥል እንደረዳት ተናግራለች።
ምንም እንኳ ስፍራው እስር ቤት የሚመስል ብላ ብትገልጸውም መግባቷ ጥሩ እንደሆነ ታስረዳለች። በ28 ቀናት ቆይታዋ 6 ኪሎ ግራም እንደቀነሰች ገልጻለች።
"ጠንካራ የሆነ አዲስ ጅማሬ ሰጥቶኛል፤ ያስፈልገኝ የነበረውን ሥርዓት እንድይዝ ረድቶኛል" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"መበደኛውን የእድገት ሂደት መገደብ"
ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነቱ ክብደት የመቀነስ መንገድ ላይ ጥንቃቄ ያሳስባሉ። ለንደን የሚገኘው የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሉክ ሃና እንደሚናገረው፤ የካምፖቹ አካሄድ አሳሳቢ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ክብደት በሚቀንሱበት ወቅት ከስብ ጋር አብሮ የጡንቻ ሕብረ ሕዋስም (muscle tissue) ይቀንሳል።
ስለዚህ ከልክ በላይ የሰውነት እንቅስቃሴ እንደማድረግ ያሉ ጫፍ የወጡ ዘዴዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ ሰዎች የጡንቻ ሕብረ ሕዋሳቸውን የማጣት ዕድላቸው ይጨምራል። በተለይም ዘዴው ተግባራዊ የሚሆነው ሕጻናት እና ወጣቶች ላይ ከሆነ ይህ ስጋት አሳሳቢ እንደሚሆን ያክላል።
"መደበኛ እድገትን እያስተጓጎልሽ ሊሆን ይችላል። ወደፊት ቁመትሽ የሚረዝምበት መጠን እና የአጥንት ጤንነትሽ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል" ሲል ያብራራል።
በተጨማሪም እንደ የምግብ ፍላጎት መዛባት ያሉ ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይጠቅሳል።
"አንዳንድ ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ክብደት ይቀንሳሉ፤ ይህም ነገሩን ሳቢ ያደርገዋል። ነገር ግን ብዙዎቹ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሲመለሱ ክብደቱ ወዲያውኑ ይመለስባቸዋል። ምክንያቱም ካምፑ ለችግሩን መሠረታዊ ምክንያቶች ወይም ጉዳዮች መፍትሔ አያበጅም" ሲል ያስረዳል።
አሠልጣኝ እና የሥነ ምግብ ባለሙያው የተሻለ መፍትሔ የሚለው ሰዎች በለመዱት አካባቢ ሆነው ቀስ በቀስ ልምዳቸውን እንዲለውጡ ማድረግን ነው። መደበኛ ገንቢ ምግቦችን ማጣጣም፣ በቂ ፕሮቲን ማግኘት እና ስፖርትን እንደ ቅጣት ሳይሆን ለክህሎት፣ ለጨዋታ እና ለደስታ እንደሚደረግ እንቅስቃሴ መውሰድ እንደሚገባ ያስረዳል።
በእርግጥ ቲኤል ሁአንግ በቅርቡ በለቀቀው የኢንስታግራም ቪዲዮ ላይ ከባዱ ነገር ወደ ቤት መመለስ እንደበር ተናግራለች። በካምፑ በነበራት ጥብቅ ቆይታ ምክንያት ሰውነቷ "መደበኛው" አመጋገብ ምን እንደሆነ ዘንግቶታል።
ጤናማ የሚባለው የአመጋገብ ሥርዓት በቀን ቢያንስ አምስት ዓይነት አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ማካተት እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ። ይህንን እየተመገቡ በሳምንት ለ150 ደቂቃዎች እንቅስቃሴ ለማድረግ መሞከር ያስፈልጋል።
ስኳር ካለባቸው መጠጦች ይልቅ ውሃ መጠጣት እንዲሁም ከፍተኛ ስብ እና ስኳር ያላቸውን ምግቦች መቀነስም እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, TL Huang
ማግለል
የቢቢሲ ግሎባል የቻይና ክፍል ባልደረባ የሆነችው ዋንቺንግ ዣንግ እንደምትናገረው እነዚህ ካምፖች በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ መጀመሪያ የተስፋፉት የክብደት መቀነሻ ተቋማቱ እንዴት እንደሚሰሩ የሚያሳይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ከተላለፈ በኋላ ነው።
እዚህ ፕሮግራም ላይ የነበሩ አሰልጣኞች የራሳቸውንም የክብደት መቀነሻ ካምፕ ከፍተዋል። የካምፖቹ ብዛት በከፍተኛ መጠን የጨመረው ግን ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ከማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው።
ዣንግ፤ "የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ብትመለከቺ በካምፕ አዘጋጆች ወይም በተሳታፊዎች የሚለቀቁ በጣም ብዙ ይዘቶችን ታገኛለሽ" ትላለች።
ጋዜጠኛዋ እንደምትናገረው፤ ሁአንግ እንደገባችበት ያሉ የተለመዱት ካምፖች ያሉ ሲሆን ሰዎች በድብቅ ምግብ እንዳያዝዙ ከዶርም ውጪ ባሉ ሥፍራዎች ላይ የደኅንነት ካሜራዎችን እስከመግጠም የሚደርሱም አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች "በሚያምር ሐይቅ ፊት ለፊት በተቀመጠ በኤሌክትሪክ መራመጃ ላይ የሚሰሩባቸው እጅግ ዘመናዊ እና የቅንጦት ቦታዎችም" ቻይና ውስጥ ይገኛሉ።
የዚህ ሁሉ መንስዔ በዓም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው ከመጠን ያለፈ ውፍረት ነው። ከዓለም አገራት ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከ50 በመቶ በላይ አዋቂ ዜጎቻቸው ወፍራም ወይም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለው ምድብ ውስጥ ይገባሉ።
የቻይና የጤና ባለሥልጣናት መረጃ እንደሚያመለክተው ከአገሪቱ አዋቂ ዜጎች ውስጥ 34 በመቶ የሚሆኑት ወፍራም ሲሆኑ 16 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሚለው ምድብ ውስጥ ይካተታሉ።
የቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ዣንግ እንደምትገልጸው እነዚህ ካምፖች እንዲስፋፉ ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ባህል ነው። ቻይናው ውስጥ ሰዎች ለሰውነት ክብደት ያላቸው ምልከታ "ተቀባይነት" የሚጎድለው መሆኑን የምትገልጸው ጋዜጠኛዋ፤ "ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆንሽ በሥራ ቦታ ወይም ፍቅረኛ የማግኘት ሂደት ውስጥ የበለጠ መገለል ሊያጋጥምሽ ይችላል" ትላለች።
የተቀነባበሩ የሩዝ ምርቶች፣ ጣፋጭ ኬኮች፣ እና ኑድልስ ሌላኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን ከቤት ውጭ ከማሳለፍ ይልቅ በቤታቸው ሆነው በስልኮቻቸው ላይ ማሳለፋቸውም የሚጠቀስ ምክንያት ነው።
ሁአንግ አሁን በታይላንድ በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ በቀን ለሁለት ሰዓታት የአካል ብቃት የሚደረግበት ሌላ የ30 ቀናት የክብደት መቀነስ ውድድርን እንደተቀላቀለች ኢንስታግራም ገጿ ላይ የምትለጥፋቸው ምስሎች ያሳያሉ።















