ማዳጋስከር ብጥብጥ ለማስነሳት አሲሯል ያለችውን የፈረንሳይ ዜጋ አሰረች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ማዳጋስከር በአገሪቱ ውስጥ ብጥብጥ እና ሁከት ለመፍጠር ሲያሴር ደረስኩበት ያለችውን የፈረንሳይ ዜጋ አስራለች።
ፈረንሳያዊው የቀድሞ የሰራዊት አባል በአገሪቱ ውስጥ ቀውስ ለመፍጠር በማሴር ተጠርጥረው መታሰራቸውን የማዳጋስከር ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የማዳጋስካር አቃቤ ሕግ ፈረንሳያዊውን ተጠርጣሪ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት መበዝበዝን ጨምሮ በርካታ የክስ መዝገቦችን ከፍቶበታል።
ባለፈው ሳምንት ሊከናወን ታቅዶ የነበረ ብጥብጥ ተቀነባብሮ እንደነበር የገለጸው አቃቤ ሕግ፣ የአገሪቱ የጦር አባልም በዚሁ ድርጊት ተሳታፊ እንደነበር ገልጿል።
የማዳጋስከር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በተመሳሳይ ብጥብጥን ከመደገፍ እና ማቀነባበር ጋር በተያያዘ አንድ የፈረንሳይ ዲፕሎማትን ከአገሪቱ አባሯል። ፈረንሳይ ዲፕሎማቷ በዚህ ድርጊት መጠርጠሩን ውድቅ አድርጋለች።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፓሪስ የሚገኘውን የማዳጋስከር አምባሳደር በመጥራት በዲፕሎማቱ ላይ የተወሰደውን እርምጃ በጽኑ ተቃውሟል። ስርዓቱን ለማወክ በሚደረግ ሴራ ውስጥ ዲፕሎማቱ አለመሳተፉን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ በጽኑ ገልጿል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ "ክሱ መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን ፈረንሳይ ለማዳጋስከር ከምታደርገው ድጋፍ የሚቃረን ነው" ብሏል።
የማዳጋስከር አቃቤ ሕግ በበኩሉ ፈረንሳያዊው ተጠርጣሪ የሐሰት መረጃዎችን በማናፈስ እና ተፈላጊ ሰዎችን በመደበቅም መሳተፉን ይፋ አድርጓል።
ባለስልጣናት በዋትስአፕ የቡድን ውይይት ላይ አገኘነው ያሉትን መረጃ በማጣቀስ ተቃዋሚዎችን ለማነሳሳት የኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ፣ የሠራዊት አባላት በመንግሥት ላይ እንዲያምጹ እና ወጣቶች ብጥብጥ እንዲያስነሱ ታቅዶ እንደነበር ደርሼበታለሁ ብሏል።
ባለፈው መስከረም ለሳምንታት የዘለቀው የማዳጋስከር ወጣቶች ተቃውሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አንድሪ ራጆሊና ከስልጣን አንስቷል።
ተቃውሞውን ተከትሎ ኮሎኔል ማይክል ራንድሪያኒሪና መፈንቅለ መንግሥቱን መርተው ባለፈው ጥር ወር የአገሪቱ መሪ ሆነው ተሹመዋል።
ቢሆንም ግን የተወሰኑ የወጣት ቡድኖች ትግላችን ሊጠለፍ አይገባም በሚል አሁንም በኮሎኔል ማይክል ላይ ተቃውሞ አላቸው።
ሰሞኑን በተደረገው ዘመቻ ማዳጋስከር ወጣቶችንም አስራለች። አቃቤ ሕግ እንደገለጸው የታሰሩት ወጣቶች በመደበኛ የክስ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በአንጻሩ ፈረንሳያዊው የቀድሞ ወታደር ግን በከፍተኛ ጥበቃ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችው ማዳጋስከር ከፈረንሳይ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላት ሲሆን፣ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ በተደጋጋሚ አለመረጋጋት ሲፈትናት ቆይቷል።














