ከመጠን ያለፈ ላብን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚዘዋወሩ መረጃዎች አንዱ እንዴት ቀኑን ሙሉ የማላብ ስሜት ሳይሰማን መዋል እንችላለን? ለሚለው መልስ የሚሰጡ ናቸው።
ከሰውነት ላብ እንዳይመነጭ አልያም ጠረን እንዳይኖረው ለማድረግ ብብት ላይ የሚቀቡ እንዲሁም የሚረጩ ዲዮድራንቶችን የሚያስተዋውቁ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
አንዳንዶቹ መላ ሰውነታቸውን ዲዮድራንት ሲቀቡ ይታያል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ከሰውነት ላብ እንዳይመነጭ ማድረግ አይቻልም። ላብ የሚወጣን ንጹህ ስላልሆንን ሳይሆን ተፈጥሯዊ ሂደት ስለሆነ ነው።
በዩኬ በሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ብሪስትል የሚሠሩት የሥነ ሰውነት ባለሙያ ፕ/ር ማይክል ስፒር "ማላብ አስፈላጊና ጤናማ ሂደት ነው" ይላሉ።
ብዙዎች የሚያልባቸው በሙቀት ወቅት ወይም ሲጨነቁ አልያም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነው። ሰውነት ሙቀትን ማስተካከል የሚችለው በላብ አማካይነት ነው።
የላብ ጠረን እንዴት ይፈጠራል?
ሰውነት ሲግን በላብ መልክ ጨው አዘል ፈሳሽ ያመነጫል። ይሄ ፈሳሽ ሲተን ሙቀትን ይዞ በመሄድ የሰውነትን ግለት ያበርዳል።
ሰውነት ላይ ጠረን የሚፈጠረው ግን በዚህ ላብ ምክንያት አይደለም።
በሰው ልጆች ሰውነት ከሁለት እስከ አራት ሚሊዮን የላብ እጢዎች ይገኛሉ። ሁለት ዓይነት ላብ ያመነጫሉ። አንደኛው ሰውነትን የሚያቀዘቅዝ ሲሆን ሌላኛው በስብ የተሞላ ነው።
ከክንዳችን ሥርና በመራቢያ አካላት አቅራቢያ ላይ የሚመነጨው በስብ የተሞላው ላብ ሲሆን በባክቴሪያ አማካይነት ይሰባበራል። ጠረን የሚወጣውም በመሰባበር ሂደቱ ወቅት ነው።
ሰውነት ንጹህ እንደሆነ እንዲሰማን ማድረግ መልካም ቢሆንም ላብ ተፈጥሯዊና ጤናማ ስለሆነ ለማስቆም መሞከር ተገቢ አይደለም።
ፕ/ር ማይክል እንደሚሉት፣ ላብን ለማስቆም ከመሞከር ይልቅ ምቹ ኑሮ ለመግፋት ላብን ለመቆጣጠር መሞከር ይመከራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰውነታችን ሁሌም ንጹህ እንዲሆን ምን እናድርግ?
ላብና ጠረንን ለመቆጣጠር አዘውትሮ በሳሙናና ውሃ መታጠብን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በየቀኑ መታጠብ ይሻላል ወይስ በሳምንት ሦስት ጊዜ መታጠብ በሚለው ላይ የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ።
ፕ/ር ማይክል እንደሚሉት ሰውነታችንን ስንታጠብ ለእግራችን፣ ለክንዳችን ሥርና ለመራቢያ አካላት ትኩረት መስጠት አለብን።
"ብዙዎች ሻወር ሲወስዱ ውሃው ሰውነታቸው ላይ ይፈሳል እንጂ እግራቸውን ማሸት ይዘነጋሉ" ይላሉ ባለሙያው።
ከጥጥ የሚሠሩ ልብሶች ላብ መምጠጥ ይችላሉ። በተቃራኒው ሴንተቲክ ልብሶች ላብን ቆዳ ላይ አምቀው በመያዝ ሰውነትን ምቾት ይነሳሉ።
ዲዮድራንትና ሌሎችም ላብን ለመቆጣጠር የሚውሉ ምርቶችም ያግዛሉ። ዲዮድራንት በብዛት የሚሠራው ከአልኮል ስለሆነ ቆዳ ላይ አሲድ በመፍጠር ባክቴርያ እንዳይከማች ይረዳል።
ላብን ለማጥፋት ሰውነት ላይ የሚነፉ ኬሚካሎች አልሙንየም ጨው ስላላቸው የላብ እጢን በመድፈን ላብ እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። እነዚህን ምሽት ላይ መጠቀም ይመከራል። ከዚያም ጠዋት ላይ መታጠብ ይቻላል።
የቆጣ ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ምሽት ላይ የላብ እጢ የሚሠራው ቀስ ብሎ ስለሆነ አልሙንየም በቀላሉ በቆዳ ይመጠጣል። ቆዳ ላይ ጨው የሚከማቸው ቀስ በቀስ ስለሆነም ውጤቱ እስኪታይ ይዘገያል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ላብ የሚቀንሱ ኬሚካሎች ይጎዳሉ?
ከአልዛይመርስና ሌሎችም ሕመሞች ጋር ላብ የሚቀንሱ ኬሚካሎች ትስስር ሊኖራቸው ይችላል የሚል መላ ምት ነበር።
የቆዳ ሕክምና ባለሙያ ኖራ ጃፋር "ይሄ ትክክል መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አልተገኙም። ላብን በሚቀንሱ ምርቶች ውስጥ የሚገኘው የአልሙንየም ጨው ከሰውነት በቀላሉ ይወገዳል። ላብን ለማጥፋት ቆዳ ላይ የሚፈጥሩት መከላከያ ከሰውነት ቆዳ ጋር በተፈጥሯዊ መንገድ መወገድ ይችላል" ይላሉ።
ሆኖም ግን እነዚህን ንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ያላግባብ መጠቀም ቆዳ ላይ ጉዳት ያስከትላል።
"ለ72 ሰዓታት ወይም ለ48 ሰዓታት የሚቆዩና ሲታጠቡ በቶሎ የማይለቁ ምርቶች የቆዳችንን ቀዳዳ ይደፍናሉ። ችግር ሊያስከትሉም ይችላሉ" ይላሉ ፕ/ር ማይክል።
አልሙንየም ያላቸው ምርቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች አስቀድመው ብብታቸውን ማድረቅ ይኖርባቸዋል። ውሃ ከአልሙንየም ጋር ሲደባለቅ ሃይድሮክሎሪክ አሲድ በመፍጠር ቆዳን ይጎዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተፈጥሯዊ መንገድ ላብን መቆጣጠር ይቻላል?
ተፈጥሯዊ ዲዮድራንት መጠቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ መጥቷል። አልሙንየምና ሰው ሠራሽ ጠረን የሚፈጥሩ ኬሚካሎችን ማስወገድ የሚሹ ሰዎች ይመርጧቸዋል።
ተፈጥሯዊ ባክቴሪያ የሚከላከሉ ምርቶች ከዕፅዋት ነው የሚሠሩት። የላብ ጠረንን ለማጥፋትና ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽን ለመምጠጥ ይረዳሉ።
"የላብ እጢን ስለማያግዱ ሰውነት አይጎዱም። ላብን ከማጥፋት ይልቅ ጠረኑን ማጥፋት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ተፈጥሯዊ ቢሆኑም ቆዳን ሙሉ በሙሉ አይጎረብጡም ማለት አይደለም። ቅባትና እርሾን የመሰሉ ተፈጥሯዊ ምርቶች ስሱ ቆዳን ሊጎዱ ይችላሉ" ሲሉ ዶ/ር ኖራ ያስረዳሉ።
የእነዚህ ምርቶች ውጤታማነት እንደየሰው ይወሰናል። ሰውነት ውስጥ ያለው ባክቴሪያ ዓይነትና ዲዮድራንቶቹ ውስጥ ያሉ ምርቶች የላብ ጠረንን የመከላከል ሂደትን ይወስናሉ።
በጣም ለሚያልባቸው ሰዎች እነዚህ ምርቶች ጠንካራ አይደሉም። አልሙንየምን ለማስወገድ ግን ጥሩ አማራጭ ናቸው።
የብዙዎች ጥያቄ ሙሉ ሰውነትን ዲዮድራንት መቀባት ትክክል ነው ወይ? የሚለው ነው። በአሜሪካና ዩኬ ለመላው ሰውነት የሚሆኑ ዲዮድራንቶች ይተዋወቃሉ።
ሰውነትን ከታጠቡ በኋላም ዲዮድራንቶቹ እንደሚቆዩና እስከ 72 ሰዓት እንደማይጠፉ ይገለጻል። ሆኖም ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት መላው ሰውነትን ዲዮድራንት መቀባት አስፈላጊ አይደለም።
"የብልት ከንፈርና ብሽሽት አካባቢ ያለው ሰውነት ስሱ ነው። ዲዮድራንት በእነዚህ ቦታዎች መቀባት ቆዳ እንዲቆጣ ያደርጋል፤ ኢንፌክሽንም ያስከትላል። ተፈጥሯዊ የባክቴሪያ ምርትን ስለሚያስተጓጉል ይጎዳል" ሲሉ ዶ/ር ኖራ ያስረዳሉ።
እነዚህን የሰውነት ክፍሎች በውሃና ሳሙና ማጽዳትን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከመጠን ያለፈ ላብ ሲከሰትስ?
ሰውነት ሙቀትን ለመቆጣጠር ከሚያስፈልገው በበለጠ ላብ ማመንጨት (hyperhidrosis) የሚገጥማቸው ሰዎች አሉ።
ስብ የተቀላቀው ላብ የሚያመርተው የሰውነት ክፍል ከመጠን ያለፈ ላብ ሲያመነጭ የሚፈጠር ሁኔታ ነው።
በአንዳንድ ሁኔታዎች የጤና እክል መኖሩን ይጠቁማል። አንዳንዴም ከሆርሞን ለውጥ፣ ከማንቁርት ሕመም፣ ከኢንፌክሽንና ሰውነት ምግብን ማብላላት ሲሳነው ከሚገጥም ችግር ጋር ይተሳሰራሉ።
ከፍተኛ መጠን ያለው አልሙንየም ጨው ያላቸው ምርቶችን በሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ይቻላል።
የላብ እጢን በቀዶ ሕክምና ማስወገድም ሌላው አማራጭ ነው።
"ከመጠን ያለፈ ላብ እንዳላቸው የሚሰማቸው ሰዎች ሊያፍሩ አይገባም። የሕክምና እገዛ ማግኘት ነው ያለባቸው" ሲሉ ፕ/ር ማይክል ያስረዳሉ።














