ባለፉት 50 ዓመታት በስኬታማ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የታዩት ወሳኝ ለውጦች

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ41 ዓመቱ ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዘመናዊው እግር ኳስ ዓለም በስፖርታዊ ብቃት እና ለረጅም ዓመታት በመጫወት ምሳሌ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በፊፋ የወንዶች ዓለም ዋንጫ የተመዘገቡ ሁለት ታሪካዊ ጎሎች በእግር ኳስ እና በወሳኝ ተጫዋቾች ገፅታ ላይ የተፈጠረውን ትልቅ የለውጥ ታሪክ ይናገራሉ።

በአውሮፓውያኑ 1970፣ በ30 ሰከንዶች ውስጥ 8 የብራዚል ተጫዋቾች አስደናቂ ቅብብል አድርገው የቀኝ መስመሩ ካርሎስ አልቤርቶ አክርሮ በመምታት ግብ አስመዝግቧል።

ብራዚሎች በጣሊያን ላይ ያስቆጠሩት ይህ የቡድኑ አራተኛ ግብ በፊፋ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ታሪክ ከታዩ ታላቅ ክስተቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል።

ከአምስት ዐሥርት ዓመታት በኋላ በ2022ቱ ፍጻሜ ደግሞ፣ እንደብራዚሉ ሁሉ ሰባት ቅብብል ካደረጉ በኋላ በክንፍ ተጫዋቹ አንሄል ዲ ማሪያ ጨራሽነት አርጀንቲናዎች በፈረንሳይ ላይ ግብ ለማስቆጠር 12 ሰከንዶች ብቻ ነበር የወሰደባቸው።

በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የአካል እንቅስቃሴ ፊዚዮሎጂ ዋና ባለሙያ የሆኑትዶ/ር ኦርላንዶ ላይታኖ፣ "የ1970ው ግብ በዚህ ዘመን ቢሆን አይቆጠርም ነበር" ይላሉ።

ያ የብራዚል ቡድን ዛሬ ላይ ያለ ቢሆን፣ እንቅስቃሴው በዘመናዊ ተከላካዮች ሊገታ ይችል ነበር። እናም ዶ/ር ላይታኖ እንደሚናገሩት፣ "ትልቁ ልዩነት ችሎታ ሳይሆን የአካል ብቃት - ፊዚዮሎጂ ይሆን ነበር።"

የታሪካዊው የብራዚል ቡድን ተጫዋቾች በ1970ው የዓለም ዋንጫ ከ30 ሰከንድ ጥቂት ከፍ ባለ ጊዜ ውስጥ ኳስ ተቀባብለው ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ...

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የታሪካዊው የብራዚል ቡድን ተጫዋቾች በ1970ው የዓለም ዋንጫ ከ30 ሰከንድ ጥቂት ከፍ ባለ ጊዜ ውስጥ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ...
የአርጀንቲና ተጫዋቾች ግብ አስቆጥረው ደስተቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ...ከ52 ዓመታት በኋላ የአርጀንቲና ተዋጮች በተመሳሳይ መንገድ ኳስ ተቀባብለው ግብ ያስቆጠሩት በ12 ሰከንድ ውስጥ ሲሆን፣ ይህም የእግር ኳስ ጨዋታ ፍጥነት ምን ያህል እንደተለወጠ አሳይቷል

'ለእያንዳንዱ ኢንች የሚደረግ ፍልሚያ'

በአውሮፓውያኑ 2014 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ወቅት ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር የሠሩት ዶ/ር ላይታኖ፣ ዘመናዊ እግርኳስ ተጫዋቾች ከቀድሞ ተጫዋቾች የተለየ የሥነ-ሕይወት አውድ ያላቸው ሆነዋል ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ የእንቅስቃሴ ሳይንስ እና ሕክምና ዕድገት እንዲህም የአጨዋወት ለውጦች፣ እግር ኳስን "ለእያንዳንዱ የሜዳ ኢንች ወደሚደረግ ፍልሚያ" ለውጠውታል። በመሆኑም "የዘመኑ ተጫዋቾች ፈጣንና ጠንካራ መሆን ይጠበቃቸዋል" ይላሉ።

የ1970ዎቹ ተጫዋቾች ከ2020ዎቹ ጋር ያላቸውን ቁመት፣ ፍጥነት እና ሰውነት የሚያነጻጽር ሥዕል

በዩናይትድ ኪንግደም ወልቨርሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ ጥናት መሠረት፣ ባለፉት አምስት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው አብዛኛው ጎበዝ ተጫዋቾች ረዘም እና ቀጠን ያሉ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው ይህን ይፋ ያደረገው ከ1970ዎቹ እስከ 2020ዎቹ ድረስ በእንግሊዝ ከፍተኛው የእግር ኳስ ሊግ በሆነው እና ዛሬ ከመላው ዓለም ከዋክብት ተጫዋቾች በሚጫወቱበት ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ የተጫወቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጫዋቾችን መረጃ አወዳድሮ ነው።

ከ1973 እስከ 2013 ድረስ የተጫዋቾች አማካይ ቁመት ከአራት ሴንቲ ሜትር በላይ ጨምሯል።

ይህ ቁመት ላይ የማተኮር አዝማሚያ በቀጣዩ ዐሥር ዓመት ውስጥም በግብ ጠባቂዎች እና በተከላካዮች ላይ ሲቀጥል ለአጥቂዎች እና ለመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ግን በመጠኑ ቀንሷል።

በእንግሊዝ ከፍተኛ ዲቪዝዮን የሚገኙ ረዣዥም ተጫዋቾች

ተመራማሪዎቹ፣ በከፍተኛ ሊግ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች "ቀጥ እና ረዘም ያለ የተስተካከለ ቁመና ያላቸው፣ ትከሻቸው ያልገዘፈ፤ ቀጠን ያሉ እና አነስተኛ ስብ ያላቸው እየሆኑ ነው" የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

ይህ የሰውነት ውቅር ዓይነት ተፈላጊ የሆነው፣ በመጫወቻ ሜዳዎች መሻሻል እና ከዘመኑ ተጫዋቾች በሚጠበቀው ከፍተኛ የሥራ ጫና ምክንያት መሆኑን የጥናቱ ባለሞያዎች ያነሳሉ።

በ1970ዎቹ፣ በክረምት ወቅት ሜዳዎች ብዙውን ጊዜ ጭቃማ ይሆኑ ነበር፤ "በመሆኑም ተጫዋቾች ጥሩ ለመጫወት ጡንቻ ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል" ይላሉ ከጥናቱ አዘጋጆች አንዱ ፕሮፌሰር አላን ነቪል።

ነገር ግን በአሁኖቹ የተሻሻሉ ሜዳዎች፣ "ቀላል እና ቀጭን ተጫዋቾች ረዘም ላለ ጊዜ ሳይደክሙ መጫወት ይችላሉ" ባይ ናቸው።

የዘመኑ ተጫዋቾች አብዛኛው ጉልበታቸው በፍጥነት ላይ እንደሚውል ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

'ለማሸነፍ ብዙ መሮጥ'

በ1970 እና 1980ዎቹ በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር ፍጥነትን መሻገር በተጫዋቾች እምብዛም እንዳልተለመደ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በ2022 የዓለም ዋንጫ ወቅት ግን ቢያንስ 10 ተጫዋቾች በሰዓት ከ35 ኪ.ሜ. በላይ የማካለል ፍጥነት አሳይተዋል። እናም ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ ውስጥ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ፍጥነታቸውን ያስመዘግባሉ።

"ያለፈውን ዘመን አጥቂዎች ካየን፣ በጨዋታ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ እየተራመዱ ሊያሳልፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጥቂት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ብቻ ሊሮጡ እና ግብ ሊያስቆጥሩ ይችሉ ነበር። አሁን ግን ይህ አይሠራም" ይላሉ የኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ የአካል እንቅስቃሴ ፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር የንስ ባንግስቦ።

በ2024 በጀርመን በተካሄደው የወንዶች የአውሮፓ ሻምፒዮና ላይ፣ ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ በአማካይ 12 ጊዜ በሰዓት 25 ኪ.ሜ. እና ከዚያ በላይ ፍጥነት ላይ ደርሰዋል ሲል የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ገልተጿል።

ሆኖም ይህ ቁጥር በተጫዋች አሰላለፍ የሚወሰን ሲሆን፣ የመሀል ተከላካዮች እና የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች በአማካይ 8 ጊዜ ከፍተኛው ፍጥነት ላይ ይደርሳሉ። አጥቂዎች በአንጻሩ 12 ጊዜ ፣ የመስመር ተከላካዮች ደግሞ 14 ጊዜ ይደርሳሉ።

በ2022 የዓም ዋንጫ ፈጣን 10 ተጫዋቾችን የሚያሳይ ዝርዝር

ፕሮፌሰር ባንግስቦ እንደሚሉት፣ ፈጣን መሆን አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ዋናው አስፈላጊ ጉዳይ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ፍጥነት ማስመዝገብ ነው።

"በአሁኑ ጊዜ የእግር ኳስ መሠረታዊ ጥያቄ ማገገም መቻል ነው - በፍጥነት የማገገም ችሎታ" ሲሉም የቀድሞው ፕሮፌሽናል ተጫዋች እና በእግር ኳስ አካል ብቃትና ፊዚዮሎጂ ታዋቂ ከሆኑ የዓለም ባለሞያዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ባንግስቦ አክለው ይገልጻሉ።

ይህ በአንድ ጨዋታ ውስጥ በፍጥነት እያገገሙ መቀጠል አስፈላጊ የሆነው፣ በተለይም ባለፈው ዐሥር ዓመት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ጫና ፈጥሮ የመጫወት ቴክኒክ ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው። ይህ ቴክኒክ፣ የተቀናቃኝ ተከላካዮች ኳሱን ወደፊት ከማሻገራቸው በፊት ከእግራቸው ላይ በፍጥነት እና በተቀናጀ መንገድ ለመንጠቅ የሚደረግ ሙከራ ነው።

አስደናቂው ነገር ታዲያ፣ ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ የሚሸፍኑት አጠቃላይ ርቀት ብዙ አልጨመረም።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በ1970ዎቹ ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ በአማካይ 8.7 ኪ.ሜ. ይንቀሳቀሱ ነበር ይህም በ1990ዎቹ ወደ 11.4 ኪ.ሜ. ከፍ ብሎ ከዚያ በኋላ ቅናሽ አሳይቷል።

እንደ ፊፋ መረጃ በ2022 የዓለም ዋንጫ ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ በአማካይ 10.6 ኪ.ሜ. ርቀት ሸፍነው ነበር።

ተጫዋቾች በጣም ብዙ እየተጫወቱ ነውን?

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ አንዳንድ በተሻለ ብቃት ላይ የሚገኙ እግር ኳስ ተጫዋቾች በብዙ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፉ ቢሆንም፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ ክለቦች አብዛኛው ተጫዋቾች በዓመት የሚጫወቱት የጨዋታ ቁጥር 42 አካባቢ ነው።

ነገር ግን አንዳንድ ወሳኝ ተጫዋቾች ላይ ከፍ ያለ ጫና ሊኖር ይችላል።

ለምሳሌ፣ የሊቨርፑል እና የኔዘርላንድስ ተከላካይ ቪርጂል ቫን ዳይክ፣ በዚህ ዓመት እስካሁን 65 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። ከእነዚህ ውስጥ 10 ጨዋታዎች ለብሔራዊ ቡድኑ ያደረጋቸው ናቸው።

ቫን ዳይክ የብሔራዊ ቡድኑን ማሊያ ለብሶ ሜዳ ውስጥ ሲያጨብጭብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሊቨርፑሉ ኔዘርላንዳዊ ተከላከይ ቪርጂል ቫን ዳይክ በዚህ ዓመት ለክለቡ እና ለአገሩ በ65 ጨዋታዎች ተሰልፏል

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ኅብረት፣ በተጫዋቾች ላይ ያለው የጨዋታ ጫና መጠን የከፋ እንዳልሆነ ጠቅሶ ለእረፍት እና ለማገገም የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርቧል።

"የጨዋታ መብዛት በግልጽ ለጉዳት ከመጋለጥ ጋር የተያያዘ ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ባንግስቦም ይህን ሀሳብ ያጠናክራሉ።

በ2023 ይፋ የሆነ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ጥናት፣ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳቶች መጠን "አሳሳቢ" በሆነ መጠን መጨመሩን አመልክቷል። ከ10 ጉዳቶች ውስጥ ስድስቱ የሚከሰቱት ተጫዋቾች በሚሮጡበት ጊዜ ነው።

ለዚህ ትክክለኛ ምክንያቱ በጥናት ባይረጋገጥም፤ ነገር ግን ጫና ፈጥሮ የመጫወት ሁኔታ መጨመሩ እና በተጨናነቀ የጨዋታ መርሃ-ግብር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አጥኚዎቹ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ፕሮፌሰር ላይታኖ "አሁን ላይ ተጫዋቾች ጉልበታቸውን አሟጠው ይጫወታሉ። በቂ የማገገሚያ ጊዜ ካላገኙ ግን አካላቸው ይወድቃል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

'አንጋፋ ተጫዋቾች እየበዙ ነው'

ክሬግ ጎርደን በልምምድ ላይ ኳስ ሲይዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ43 ዓመቱ የስኮትላንድ ግብ ጠባቂ ክሬግ ጎርደን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከተሰለፉት በዕድሜ ትልቁ ነው

ነገር ግን መልካም ዜናም አለ።

ከሥልጠና ዘዴዎች እስከ አመጋገብ እና ማገገም ድረስ ያሉ የስፖርት ሳይንስ ዕድገቶች፣ እግር ኳስ ተጫዋቾች በከፍተኛ የብቃት ደረጃ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ መጫወት እንዲችሉ አድርጓቸዋል።

በክለቦች ውድድር ደረጃ በዓለም እጅግ ተወዳጅ በሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች አማካይ የተጫዋቾች ዕድሜ በ1992 ከነበረበት 24.9 ዓመት በ2018 ወደ 26.5 ዓመት ከፍ ብሏል።

እንደ ፊፋ መረጃ፣ ያለፉት ሦስት ዓለም ዋንጫዎች በታሪክ ውስጥ "ከፍተኛ ዕድሜ ያላቸው" ነበሩ፤ 2018 የተካሄደው ውድድር 27.9 ዓመት በመሆን ከፍተኛውን አማካይ የተጫዋች ዕድሜ መዝግቦታል።

እንደ ፊፋ መረጃ ከሆነ፣ ያለፉት ሦስት የዓለም ዋንጫዎች በታሪክ ውስጥ "በዕድሜ የገፉ" ተጫዋቾች የተሳተፉባቸው የነበሩ ሲሆን፣ የ2018ቱ ውድድር 27.9 ዓመት አማካይ የተጫዋቾች ዕድሜን በማስመዝገብ ተስተካካይ አልተገኘለትም።

በ1990ው የዓለም ዋንጫ፣ 35 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰባት ተጫዋቾች ብቻ ተሳትፈው ነበር፤ በ2022 በተካሄደው ውድድር ደግሞ ቁጥራቸው 41 መድረሱ ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ደግሞ፣ የፊፋ የቡድኖች ዝርዝር መረጃ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆነ 72 ተጫዋቾች መኖራቸውን ያሳያል።

ስምንት ተጫዋቾች 40 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሲሆኑ፣ ይህም ከቀደሙት ሁሉም የዓለም ዋንጫዎች ላይ በድምሩ ከነበሩት በላይ ነው።

ዶክተር ላይታኖ ስለዚህ ሁኔታ ሲያስረዱ "ራሳቸውን የሚንከባከቡ እና ትክክለኛውን የሥልጠና እንዲሁም የማገገሚያ ደንቦችን የሚከተሉ ተጫዋቾች፣ ከቀድሞው ዘመን በተሻለ ሁኔታ በከፍተኛ ብቃት ላይ ሆነው ረዘም ላለ ጊዜ የመጫወት ዕድላቸው በጣም ሰፊ ነው" ብለዋል።