ሜታ እየቸበቸበው ያለው 'ስማርት መነጽር' እና የሚቀርብበት ቅሬታ

የሜታ ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ማርክ ዙከርበርግ ስለ ሜታ ሬይባን ስማርት መነጽር መድረክ ላይ ሲያወራ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

'ከስማርት መነጽሮች' ጋር የተያያዙ አዳዲስ ቅሬታዎች እየተሰሙ ነው።

ሆኖም ግን በመላው ዓለም የሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመጪዎቹ ዓመታት ሚሊዮኖችን መነጽሮችን ለመሸጥ ተዘጋጅተዋል።

ሴቶች በባሕር ዳርቻዎች ሲዝናኑ፣ ወደ መደብሮች ሲጓዙ ወይም መንገድ ላይ ቆመው የሜታን "ስማርት" ሬይባን መነጽር ባጠለቁ ወንዶች ያለእውቅናቸው ወይም ፈቃዳቸው የተለመዱ ጥያቄዎችን ሲጠየቁ ተቀርፀዋል።

ሴቶች ስለቪዲዮዎቹ እውቅና የሚኖራቸው በማኅበራዊ ትስስር ገፆች ከተሰራጩ እና በኦንላይን ጥቃት ሲደርስባቸው ነው። በሕዝባዊ ስፍራዎች ፎቶግራፎችን ማንሳት በጥቅሉ ሕጋዊ ስለሆነ የሕግ እርምጃ ለመውሰድ መንገዱ ጠባብ ነው።

አንድ ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው በሚስጥር የቀረፃትን ሰው ምስሎቹን እንዲያስወግድ ስትጠይቅ፤ ይህን ማድረግ "የሚያስከፍል አገልግሎት" እንደሆነ ተነግሯታል።

በአሁኑ ወቅት የሜታ መነጽር በገበያው ላይ በጣም ተወዳጅ ሲሆን፤ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ወይንም ስማርት መነፅር ገበያው 80 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይገመታል። ኩባንያው ባለፉት ዓመታት ይህን ቴክኖሎጂ ለገበያ ካቀረቡ ግዡፍ ኩባንያዎች ውስጥ የመጀመሪያው ነው።

መነጽሩ ለማየት የሚያዳግቱ አነስተኛ ካሜራዎች እና መረጃን የሚያሳዩ ሌንሶች የተገጠሙለት ነው። መነጽሩን የሚያደርጉ ሰዎች በትንሽ ምልክት ቪዲዮ መቅረፅ አሊያም ፎቶግራፎችን ማንሳት ይችላሉ።

መነጽሮቹ ከሙከራቸው ጀምሮ ከግላዊ እና ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምስሎች ጋር በተያያዙ ክሶች ቢቀርቡም፤ ሜታ ለተጠቃሚዎች ስለሁኔታው አስቀድሞ እንደሚያሳውቅ በመጥቀስ ይከራከራል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንዲሁም ሆኖ የመነጽሩ ሽያጭ ማደጉ ቀጥሏል። እስከዛሬ ድረስ ሰባት ሚሊዮን መነፅሮች መሸጣቸውን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል።

የሜታ ቃል አቀባይ ትሬሲ ክሌይተን ሰዎች ቴክኖሎጂውን በኃላፊነት መጠቀም እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪው አዲስ የምርት ዘርፍ ሆኖ የተወሰደውን 'ስምርት መነጽር' ለማምረት ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎችም እያቀዱ ነው።

አፕል እና ጎግልን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና የምናባዊ እውነታን ቴክኖሎጂን በማከል በቅርብ ዓመታት ምርቶቻቸውን ለገበያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተጠቃሚዎች እነዚህን መነጽሮች የሚጠቀሙበት መንገድ ሁሉም መጥፎ እንደማይሆን ግን እርግጥ ነው።

ሁሌም የሜታን ሬይባን መነጽር የሚጠቀመው ማርክ ስሚዝ በእጆቹ ስራ እየሰራ ስልክ ለማነጋገር እንዲሁም ሙዚቃ እና ፖድካስቶችን ለመስማት መነጽሩ ከጆሮ ማዳመጫዎች የተሻለ ሆኖ ማግኘቱን ይናገራል።

እንዲህም ቢሆን ግን ማርክ የግላዊነት ጉዳይ የማይደበቅ እክል ነው ይላል። በተለይም መነጽሩ ምስሎችን ሲቀርፅ የሚበራው መብራት በቀን እምብዛም አለመታየቱ አብዛኞቹ ሰዎች መደበኛ መነጽሮችን አጥልቀዋል ተብሎ እንዲታሰብ ያደርጋል።

ተመራማሪዎች በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት 100 ሚሊዮን ሰዎች 'ስማርት መነጽሮችን' ይገዛሉ ብለው ይጠብቃሉ።

ይህ ግምት እውን የሚሆን ከሆነ እንደ ፍርድ ቤት፣ ሙዚየሞች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና መፀዳጃ ቤቶች ባሉ በተከለከሉ ስፍራዎች ሚሊዮን መነጽሮች ከካሜራ ጋር ሲቀርቡ ሕጎችን እና ደንቦችን ማስፈፀም አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ሜታ በመነጽሮቹ ላይ ፊት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ አባሪ ለማድረግ ማቀዱም ተነግሯል። ይህም ማለት መነፅሩን ያደረጉ ተጠቃሚዎች ሰዎችን በድብቅ ከመቅረፅ ባለፈ ማንነታቸውንም በፍጥነት መለየት ይችላሉ።