በአማራ ክልል የተፈናቃይ መጠለያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 18 ሰዎች ሲገደሉ ከ30 በላይ ሰዎች ቆሰሉ

በድሮን የተመቱ መጠለያ ሸራዎች
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በተጠለሉበት 'ጃሪ ቁጥር 2' የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት "ሕጻናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ" 18 ሰዎች መገደላቸውን ሦስት የካምፑ ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጉዳት የደረሰባቸው "ስምንት ሕጻናት እና 10 ሴቶችን" ጨምሮ በአጠቃላይ 36 ሰዎች ወደ ሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አንድ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እንደሚያስረዱት፣ የድሮን ጥቃቱ የደረሰው ሐሙስ ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም. ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ ላይ ነው።

በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የሚገኘው ይህ ካምፕ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ የተጠለሉበት ነው።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች በቅርብ ርቀት ባሉ አካባቢዎች ላይ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ውጊያ የሚያደርጉበት ቢሆንም ጥቃት በደረሰበት ዕለት ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳልነበረ ሦስት የካምፑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለበርካታ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነው የድሮን ጥቃት ቢያንስ አራት ጊዜ መፈጸሙን ሁለት ተፈናቃዮች ተናግረዋል። የድሮኑ ጥቃት ያረፈው ካምፑ ውስጥ በሚገኙት ከሸራ በተሠሩ የተፈናቃዮች መጠለያዎች ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱን በተመለከተ ለመከላከያ ሠራዊት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው ያደረገው የስልክ ጥሪ እና በፅሑፍ መልዕክት ያቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም። ከደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ተፈናቃይ ጥቃቶቹ የደረሱት "በ15 እና በ20 ደቂቃ ልዩነት" መሆኑን ገልጸው፣ "አምስት ድሮን ተጣለ። አምስቱም ሁላ ሸራ ቤት ላይ አረፈ፤ ቤቱም ተቃጠለ፣ ሰዎችም ተቃጠሉ፣ ሞቱ" ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ጥቃቱ የደረሰው "አይዲፒ [ካምፕ] ውስጥ ነው፣ ያው እንዳለ ሸራ ላይ ማለት ነው። ካምፑ ላይ ነው። ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ነው" በማለት አስረድተዋል።

"አራት ጊዜ ሲጥል ዝም ብሎ እያዟዟረ ካምፑ ላይ ነው [የወደቀው]" የሚሉት ሦስተኛው ተፈናቃይ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ከሸራ የተሠሩ መጠለያዎች "በጣም ብዛት" እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በድሮን ወደተመቱ መጠለያ ሸራዎች የሚሄዱ ሁለት ሰዎች

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በእነዚህ ጥቃቶች ጉዳት የደረሰባቸው ቢያንስ 16 ተፈናቃዮች እዚያው ካምፕ ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል። ወደ ሕክምና ተቋም ከተወሰዱት ውስጥ ደግሞ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሞቱት ተፈናቃዮች መካከል ጥቂት የማይባሉት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ሁለት ነዋሪዎች ገልጸዋል። አንድ ተፈናቃይ፣ "ሕጻናትም አሉ፣ የወለደች አራስ አለች፣ እርጉዝም አለች፣ እንደዚሁ በቃ ብዙ ደካሞችም አሉ" ብለዋል።

አንድ ነዋሪ "ሦስት ነፍሰ ጡር ሞቷል፣ ሦስት ተማሪ ሞቷል፣ አዛውንት ቤታቸው ተቀምጠው ምንም ነገር፣ በሰፈራቸው ምንም ነገር የማይጤስ፣ ምንም ነገር እንደው ንጹሃን ዜጋ [ነው የሞተው]" በማለት ዘርዝረዋል። ተገድለዋል ካሏቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች መካከል ሁለቱን በስም የጠቀሱት እኚህ ነዋሪ፣ ከእነዚህ ሴቶች አንዷ "የአምስት ዓመት ልጇ አብሮ ሞቷል" ብለዋል።

እንደ ሦስቱ ነዋሪዎች ገለጻ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ነዋሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሕክምና ምንጭ ጉዳት የደረሰባቸው 36 ሰዎች ስምንት ሰዓት አካባቢ ወደ ሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

እንደ ምንጩ ገለጻ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ ስምንቱ ከሦስት ዓመት ጀምሮ ያሉ ሕጻናት ናቸው። 10 ያህሉ ተጎጂዎች ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን አክለዋል።

"አንድ ሆስፒታል ሲደርስ ሞቶ የመጣ ሰው አለ። አንድ ደግሞ ወደ ደሴ [አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል] ሪፈር ተብሎ [ሲሄድ] የሞተ አለ" ሲሉ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አብራርተዋል።

ከሸራ የተሰሩ መጠለያዎች

እንደ ምንጩ ገለጻ፣ ከመጡት ሰዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 12 ሰዎች ወደ ደሴ ከተማ ተልከዋል። ለተጨማሪ ሕክምና የተላኩት ተጎጂዎች "በጣም የበዛ ደም መፍሰስ፣ የጭንቅላት ምት እና የአጥንት ስብራት" እንዳጋጠማቸውም አስረድተዋል።

ሌሎች 11 ሰዎች አሁንም ሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኙ እና ሌሎች "ቀለል ያለ ጉዳት" ያስተናገዱ ነዋሪዎች ሕክምና አግኝተው መውጣታቸውን ገልጸዋል።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ስፍራ ሕይወታቸው ያለፈ 16 ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት ትናንት ሐሙስ እዚያው "ካምፑ ውስጥ በአንድ ጉድጓድ" መፈጸሙን ሦስቱ ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ፣ "[ከካምፕ] ወደ ውጭ መውጣት ስለማይቻል በኬንዳ እያፈንን፣ በኬንዳ [ሸራ] እየጠቀለልን ነው [ቀብራቸው የተፈጸመው]፤ እጃቸው ለብቻ፣ እግራቸው ለብቻ ስለወዳደቀ ማለት ነው" ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ "ይህን ሁሉ ሰው በሜዳ ላይ አሳድሮ ሬሳ" የሚጠብቅ ሰው ባለመኖሩ በቶሎ እና በአንድ ላይ ቀብር እንዲፈጸም መደረጉን ጠቅሰዋል።

የትናንቱን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ተፈናቃዮች ካምፑን ጥለው መውጣታቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱን በተመለከተ ከመንግሥት አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ሙከራዎች አልተሳኩም። ከታጣቂዎች ጋር በሚደረጉ ግጭቶች ሰው አልባ ድሮኖችን ጥቅም ላይ የሚያውለው መንግሥት ከዚህ ቀደም ንጹኃን ላይ ጥቃት ይደርሳል መባሉን በተደጋጋሚ አስተባብሏል።