ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማሊ ጦር በመላው አገሪቱ ታጣቂ ቡድኖች የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን አስታወቀ
በማሊ በዋና ከተማዋ ባማኮን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ታጣቂ ቡድኖች የተቀናጀ ጥቃት መክፈታቸውን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።
ቅዳሜ ጠዋት ጦሩ ባወጣው መግለጫ "ውጊያ እየተካሄደ" መሆኑን የገለጸ ሲሆን አክሎም "የመከላከያ እና የደህንንት ኃይላችን ታጣቂዎቹን ለመመከት እየተፋለሙ ይገኛል" ብሏል።
ከዋና ከተማዋ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ካቲ የጦር ሠፈር አቅራቢያ ፍንዳታዎችን እና ተኩስ መሰማቱን የዓይን ምስክሮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ወታደሮች መንገድ እንዲዘጉ ወደ ስፍራው መሠማራታቸውም ታውቋል። በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ጋኦ እና ማዕከላዊ ማሊ ሴቫሬን ጥቃት ተከፍቷል።
ከኢትዮጵያ ወደ ባማኮ የሚጓዝ አንድ ነዋሪ ከቅዳሜ ማለዳ ጀምሮ ወደ አገሪቱ የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ መሰረዛቸውን ተናግሯል።
የአገሪቱ ጦር የተቀናጀ ጥቃት ያለው አውሮፕላን ማረፊያዎችንም ስለማካተቱ የታወቀ ነገር የለም።
ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን ድረስ አልተገለጸም።
በማሊ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንዲቆዩ መክሯል። በባማኮ በሚገኘው የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሞዲቦ ኬይታ እና በካቲ አቅራቢያ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ መኖሩን በመጥቀስ ከየትኛውም ጉዞ እንዲታቀቡ አሳስቧል።
ማሊ በሚገኘው ኮናርድ አድኑር ፋውንዴሽን የሳህል ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ኡልፍ ሌይሲንግ "ከዓመታት በኋላ በጂሃዲስቶች የተፈጸመ ትልቅ የተቀናጀ ጥቃት" መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የማሊ መከላከያ በስም ያልጠቀሳቸውን "የሽብር ቡድኖች" እየተዋጋ መሆኑን ቢገልጽም በትክክል እየሆነ ያለውን ለማወቅ የሚያስችሉ ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የተመለከቱ የመረጃዎች አጣሪ ቡድኖች ጥቃቱ በጃማት ኑስራት አል ኢስማም ዋል ሙስሊሚን እና በቱራይግ አዛዋድ የነጻነት ግንባር የተፈጸሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
የአዝዋድ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ ሞሐመድ ኤልማኦላውድ ራማዳኔ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ታጣቂዎቻቸው በጋኦ እና ኪዳል የሚገኙ በርካታ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ጣልቃ እንዳይገቡም አስጠንቅቀዋል። ቢቢሲ የቃል አቀባዩን መረጃ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
ማሊ እአአ ከ2020 ጀምሮ ሥልጣንን በመፈንቅለ መንግሥት በያዙት በጄነራል አሲሚ ጎይታ ትመራለች።
ጄነራሉ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የአገሪቱን ጸጥታ ለማስጠበቅ እና ታጣቂ ቡድኖችን ለመደምሰስ ቃል ገብተው ነበር።
የወታደራዊ መንግሥቱ መሪ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙት ከቡርኪናፋሶ እና ከኒጀር ወታደሮች ጋር የትብብር ኅብረት በመመሥረት ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቀነስ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።
የማሊ ወታደራዊ መሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት የያዙትን ሥልጣን ምርጫ በማካሄድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመለሱ በመጠየቁ ምክንያት ጄነራል ጎይታ ማሊን ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር ኤኮዋስ አስወጥተዋታል።
በተመሳሳይ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀርም ከማኅበሩ ራሳቸውን አግልለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ሦስቱ ተጎራባች የምዕራብ አፍሪካ አገራት የጋራ ትብብር መሥርተው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።