በናይጄሪያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት ፈጽመው ምእመናን በገደሉ ላይ ሞት ተፈረደ

ተከሳሾች በፍርድ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከተከሰሱት አምስት ሰዎች አራቱ ሞት ተፈርዶባቸዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የናይጄሪያ ፍርድ ቤት ከአራት ዓመት በፊት በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በሚገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት በፈጸሙ አራት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔ አሳለፈ።

በቅዱስ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ በጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ አጥቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ 42 ምእመናን ተገድለው ከ100 በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በዋና ከተማዋ አቡጃ የተሰየመው ፍርድ ቤት ሰኢድሪስ አብዱልማሊክ፣ አል ቃሲም ኢድሪስ፣ ጃሙ አብዱል ማሊክ እና አብዱልሃሊም ኢድሪስ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የሽብርተኛ ቡድን አባል በመሆናቸው የ20 ዓመታት እስር ደርሶባቸዋል።

በናይጄሪያ ውስጥ የሞት ቅጣት ተግባራዊ የሚሆነው በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲጸድቅ ነው። ለበርካታ ዓመታት ተግባራዊ የሆነ የሞት ቅጣት የለም።

ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ኤሜካ ንዊቴ በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ማስረጃ በችሎቱ "በመስቀለኛ ጥያቄ ወቅት ጥርጣሬ ውስጥ ያልገቡ እና ተቃውሞ ያልቀረበባቸው ናቸው" ብለዋል።

ከፍተኛ ትኩረት የሳበው ይህ የፍርድ ሂደት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መታየት ከተጀመረ በኋላ በፍጥነት እንዲሰማ እና እልባት እንዲያገኝ መታዘዙን ዳኛው ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ሁለቱን አጥቂዎች የሚያውቁ ምስክሮችን ጨምሮ ጥቃቱ ሲፈጸም የዐይን እማኝ የነበሩ ሰዎችን በማቅረብ ክሱን በማያጠራጥር ሁኔታ ማስረዳቸታውን ዳኛው ገልጸዋል።

"ስለዚህም ፍርድ ቤቱ ከአንድ አስከ አራተኛ የቀረቡት ተከሳሾች በቀረቡባቸው ዘጠኝ ክሶች ጥፋተኛ ሆነው አግኝቷቸዋል" ብለዋል።

በምስክርነት ቀርበው ቃላቸውን ከሰጡት መካከል ጥቃት ፈጻሚዎቹ ባፈነዱት ድማሚት ምክንያት አንድ እግሯ የተቆረጠ እና አንድ ዐይኗ የጠፋ ሴት ትገኝበታለች።

ሞት በተፈረደባቸው ተከሳሾች ላይ የቀረቡባቸው ዘጠኝ ክሶች የሽብር ቡድን አባል መሆን እና ግድያን ማቀድ እና መፈጸምን ያካትታል።

ጉዳዩን የያዙት ዐቃቤ ሕግ አዮዴጄ አዴዲፔ ከብይኑ በኋላ "በጭካኔ ለተገደሉት ሰዎች ፍትሕ ተሰጥቷል" በማለት በውሳኔው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሞት የተፈረደባቸው ተከሳሾች ጠበቆች ግን ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቀዋል።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት ተካሳሾቹ በእስር ላይ ሳሉ ድብደባን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ስቃይ ይፈጸምባቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

በሂደቱ አንድ ተከሳሽ ጥቃቱን በገንዘብ በመደገፍ እና ገንዘብ በማስተላለፍ ቢከሰስም በቂ ማስረጃ ስላልተገኘበት ከእስር ተለቅቆ በነጻ ተሰናብቷል።

የፀጥታ ስጋት እየጨመረባት በመጣው በናይጄሪያ በርካታ ሰዎች ከተገደሉበት ከዚህ የቤተክርስቲያን ጥቃት በኋላ በርካታ ጥቃቶች በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ተፈጽመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናይጄሪያ ክርስቲያን ሕዝቧን ከጂሃዲስት ቡድኖች ጥቃት መጠበቅ አልቻለችም ሲሉ ወቅሰዋታል።

ባለፈው ታኅሣሥ ወር በፈረንጆች የገና ዕለት በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጄሪያ የሚገኙ ሁለት የጂሃዲስት ቡድን ካምፖች ላይ ጥተት ፈጽማ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ካልቀመ እርምጃዋን እንደምትቀጥል አሰጠንቅቃ ነበር።