ቀጥታ, በአማራ እና ኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ድምጽ መስጠት መቋረጡን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አስታወቁ

በአማራ እና በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች ድምጽ መስጠት ከተጀመረ በኋላ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መቋረጡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በፀጥታ ምክንያት ያልተከፈቱ 143 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር የተቋረጠባቸው ቦታዎች እንዳለ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ድምጽ መስጠቱ ቀጥሏል

    ማለዳ 12 ሰዓት በይፋ የተጀመረው የሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ መቀጠሉን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

    ከትግራይ ክልል ውጭ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ በሚካሄደው ድምጽ አሰጣጥ መራጮች ለሕዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች እንደራሴዎቻቸውን ይመርጣሉ።

    ዛሬ ምሽት ከሚያበቃው የድምጽ መስጠት ሂደት በኋላ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ውጤት ይፋ የሚደረግ ሲሆን በተከታታይ በሚኖሩት ቀናት በተለያዩ ደረጃዎች አጠቃላዩ ውጤት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚገለጽ ይሆናል።

    መራጮች በሶማሊ ክልል

    የፎቶው ባለመብት, nebe

    የምስሉ መግለጫ, መራጮች በሶማሊ ክልል
    መራጮች በአማራ ክልል

    የፎቶው ባለመብት, nebe

    የምስሉ መግለጫ, መራጮች በአማራ ክልል
    መራጮች በአዲስ አበባ

    የፎቶው ባለመብት, nebe

    የምስሉ መግለጫ, መራጮች በአዲስ አበባ
    ምርጫ በሐረሪ ክልል

    የፎቶው ባለመብት, nebe

    የምስሉ መግለጫ, መራጮች በሐረሪ ክልል
    ምርጫ በአዲስ አበባ

    የፎቶው ባለመብት, nebe

    የምስሉ መግለጫ, መራጮች በአዲስ አበባ
  2. በአማራ እና ኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ድምጽ መስጠት መቋረጡን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አስታወቁ

    የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ

    የፎቶው ባለመብት, etv

    የምስሉ መግለጫ, የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ

    በአማራ እና በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች ድምጽ መስጠት ከተጀመረ በኋላ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መቋረጡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

    የምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ዛሬ ከማለዳው12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ያለውን ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመላው አገሪቱ ካሉ የምርጫ ጣቢያዎች 50,188ቱ በሰዓቱ 12 ሰዓት ላይ ድምጽ አሰጣጥ መጀመሩን ተናግረዋል።

    ነገር ግን 695 የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ አለመከፈታቸውን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ገልጸው፤ እነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች በ30 ደቂቃ እና በአንድ ሰዓት ዘግይተው መከፈታቸውን አብራርተዋል።

    በፀጥታ ምክንያት ያልተከፈቱ 143 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር የተቋረጠባቸው ቦታዎች እንዳሉ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።

    የምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በስምንት የምርጫ ክልሎች ምርጫ እንደማይካሄድባቸው አስታውቆ ነበር።

    የቦርዱ ሰብሳቢ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ መካሄድ ባልተቻለባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ምርጫው እንዳይካሄድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማገዳቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።

    በ39ሺህ 723 የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች እስካሁን ድረስ ተገኝተው መታዘባቸውን የተናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተመራጮች ያቀርቧቸው ወኪሎች በ41 ሺህ 798 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተገኝተዋል ብለዋል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች በመላ አገሪቱ ወጥተው ድምጻቸውን እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ሜላት ወርቅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መራጮች ሰልፍ ላይ የቆዩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እና በሌሎች ክልሎች ማጋጠሙን ተናግረዋል።

    ይህ የተከሰተው በተለይ የዲጂታል ምዝገባ በተካሄደባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ረዥም የሆኑ ሰልፎች በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች መታየታቸው ተገልጿል።

    ይህ የታየው በዲጂታል ወይም በራሳቸው በሞባይል ወይም በድረገጽ የተመዘገቡ መራጮች ላይ መሆኑን ያመለከቱት ሰብሳቢዋ፣ የተፈጠረውን ሰልፍ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

    ከ350 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች በመላ አገሪቱ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸው፣ በቤንሻንጉል ክልል በዘልማም እና ሰልዳ የምርጫ ክልሎች በኔትወርክ ችግር የስልክ ግንኙነት የተቸገርንባቸው መረጃ በወቅቱ ለማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

    በእነሞር እና ኤነር አንድ የምርጫ ክልል የምርጫ ክልል አስፋጻሚ ባልደረባ የክትትል ሥራ ለመሥራት በሞተር ሳይክል ሲሄድ በደረሰበት አደጋ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።

  3. በምርጫ 2018 ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፉት ሦስቱ አዳዲስ ክልሎች

    ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኤርቦሬ ምርጫ ጣቢያ

    የፎቶው ባለመብት, NEBE

    የምስሉ መግለጫ, ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኤርቦሬ ምርጫ ጣቢያ

    በሕዝበ ውሳኔ መሠረት ራሳቸውን ችለው እንደ ክልል የተደራጁ ሦስት ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ እያካሄዱ ነው።

    ከቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር ወጥተው እንደ አዲስ የተዋቀሩት ክልሎች ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ናቸው።

    ክልሎቹ በመመሥረቻ ጉባኤያቸው ምክር ቤቶችን ያቋቋሙ ሲሆን፤ ዘንድሮ ለሚካሄደው ምርጫ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ጨምረዋል።

    በዚህም መሠረት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 105 የምክር ቤት መቀመጫዎች የነበሩት ሲሆን፤ 70 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ጨምሮ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለ175 መቀመጫዎች ምርጫ ይካሄዳል።

    በሕዝበ ውሳኔ በርካታ የዞን መዋቅሮች ተነጥለውት ብቻውን የቀረው እና በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ መሠረት ስሙን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚል የቀየረው ክልል 95 የምክር ቤት አባላት ቁጥር ጨምሯል። በዚህም የምክር ቤቱን የመቀመጫ ብዛት 229 አድርሷል። ይህም በምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት የአገሪቱ አራተኛ ትልቅ ክልል ያደርገዋል።

    ከሲዳማ በመቀጠል 11ኛ ክልል ሆኖ ፌደሬሽኑን የተቀላቀለው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ከነበረው 52 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች 119 መቀመጫዎችን ጨምሮ ለሰባተኛው ምርጫ ቀርቧል።

    ይህም ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው ምርጫ 2018 የመቀመጫ ጭማሪ ተደረጓቦቻዋል ብሎ ይፋ ካደረጋቸው አዲስ አበባ እና ስድስት ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ የምክር ቤት አባላት ቁጥር የጨመረ ክልል ነው።

  4. መራጮች ወደ 11 ሺህ ከሚጠጉ ዕጩዎች መካከል ድምጽ ይሰጣሉ

    ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሀዲያ ሀሙስ ገበያ ምርጫ ጣቢያ

    የፎቶው ባለመብት, NEBE

    ዛሬ እየተካሄደው ባለው ምርጫ ለመምረጥ የተመዘገቡ ሰዎች ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት በዕጩነት ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል ለሚመርጡት ድምጽ ይሰጣሉ።

    ምርጫው በሚካሄድባቸው ክልሎች ውስጥ 42 ፓርቲዎች እና 73 የግል ተወዳዳሪዎች ለተለያዩ ምክር ቤቶች ዕጩዎችን አቅርበዋል።

    በዚህ ምርጫ በአጠቃላይ 2,198 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 8,736 ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫዎች በዕጩነት ቀርበው ይወዳደራሉ።

    በዚህም በምርጫው የሚወዳደሩት አጠቃላይ ዕጩዎች ቁጥር 10,934 ዕጩዎች መሆናቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል።

    ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች ከፍተኛውን ዕጩዎች ያቀረቡት ሦስት ፓርቲዎች ናቸው። በዚህም ገዢው ብልጽግና 2,950 ዕጩዎችን በማቅረብ ቀዳሚ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1,256 እና ሦስተኛው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 1,032 አቅርበዋል።

    ሌሎች ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎችም በተለያየ ቁጥር ለተለያዩ ምክር ቤቶች መቀመጫ ለማግኘት ዕጩዎችን በምርጫው ላይ እንዲወዳደሩ አቅርበዋል።

  5. የተረጋጋጠ የምርጫው ውጤት መቼ ይፋ ይሆናል?

    ሐመር፣ ኮልካጃ ሎጀራ ምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት

    የፎቶው ባለመብት, NEBE

    የምስሉ መግለጫ, ሐመር፣ ኮልካጃ ሎጀራ ምርጫ ጣቢያ ድምጻቸውን የሚሰጡ መራጮች

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት እስከ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም. ድረስ ይፋ እንደሚሆን ያሳያል።

    ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተረጋገጠ የምርጫው ውጤት ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2/1028 ዓ.ም. ድረስ ይፋ ይሆናል።

    የተረጋገጠው አጠቃላይ የምርጫው ውጤት ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ ውጤት በምርጫ ጣቢያዎች ከነገ ማክሰኞ ግንቦት 25/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ይፋ ይሆናል።

    ጊዜያዊ ውጤት በምርጫ ክልሎች ደረጃ ደግሞ ከግንቦት 25 እስከ ግንቦት 29/2018 ዓ.ም. ድረስ እንደሚካሄድ የጊዜ ሰሌዳው ይጠቁማል።

    የምርጫውን ውጤት ቦርዱ ከምርጫ ክልሎች የሚረከበው በደግሞ ከግንቦት 26 እስከ ሰኔ 1 ነው።

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ የማቅረቢያ ጊዜን ከምርጫው ቀን ግንቦት 24 እስከ ሰኔ 2 ድረስ መሆኑንም አመልክቷል።

  6. ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ ሲንቀሳቀሱ ክልከላ እንደገጠማቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መለያ

    የፎቶው ባለመብት, National Electoral Board of Ethiopia

    የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቦርዱ ተመዝግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን “በውስን አካባቢዎች” ሥራ እንዳቆሙ አስታወቀ።

    ትናንት እሑድ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተባለው መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎቹ የምርጫ ዝግጅቱን ለመቃኘት በምርጫ ጣቢያዎች ሲንቀሳቀሱ ከምርጫ አስፈፃሚዎች እና ከፀጥታ ኃይሎች ክልከላ እንደተደረገባቸው አስታውቋል።

    በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 “ሁለት የብልጽግና ፓርቲ ታዛቢዎች መሆናቸውን የገለጹ ግለሰቦች” ከበላይ ትዕዛዝ እስኪሰጣቸው ድረስ ክልከላ ካደረጉ በኋላ ፈቃድ ቢሰጡም ምሥል መቅረፅ ግን እንደከለከሉ ገልጿል።

    በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በአንድ የምርጫ ጣቢያ የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ክልከላ ማድረጋቸውን መገናኛ ብዙኃኑ አስታውቋል።

    በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጥበቃ ለማድረግ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት ምንም እንኳ በምርጫ ቦርድ ለዘጋቢዎቹ የተሰጠን መታወቂያ ቢመለከቱም “በስፍራው መዘገብም ሆነ ፎቶ ማንሳት ከልክለዋል” ብሏል።

    ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ ክልከላ እንደገጠመው ገልጿል።

    ቢቢሲ ምርጫውን በአገር ውስጥ ለመዘገብ ፈቃድ አልተሰጠውም።

    ቦርዱ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አካባቢዎች ለመዘገብ “ደብዳቤ” እንዲፃፍላቸው መጠየቃቸውን ጠቁሞ፤ መገናኛ ብዙኃንን ከሥራ ማስቆም “የተሳሳተ” ነው ብሏል።

    አክሎም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር መሠረት “ማንኛውም ሰው ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ሲያስፈጽም የመተባበር ግዴታ አለበት” በማለት አሳስቧል፡፡

    ቦርዱ ምርጫውን እንዲዘግቡ 68 መገናኛ ብዙኃንን እና 1,815 ጋዜጠኞችን መመዝገቡን ገልጿል። እነዚህ ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎች 200 ሜትር ንፍቀ ክበበ ውስጥ ገብተው መዘገብ የሚያስችላቸውን መለያ ባጅ መስጠቱን ተናግሯል።

  7. “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዳይካሄድ ኃይሎችን ገዝተው አሰማርተዋል" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    የፎቶው ባለመብት, FBC

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት ሰላማዊ ምርጫ እንዳይካሄድ “የገዟቸውን ኃይሎች” በስፋት ማሰማራታቸውን ገለጹ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በትውልድ ቀያቸው በሻሻ ድምፅ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ታሪካዊ ጠላቶች ያሏቸውን ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል “እምነት እንድንይዝ ሙከራ አድርገዋል” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ዲሞክራሲ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የሚሻውን፣ የሚፈልገውን ለመወሰን መካሪ፣ ገሳጭ” እንደማያስፈልገው ማለዳ ድምጹን ለመስጠት በመውጣት አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።

    የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ዛሬ ከማለዳው አስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በጅማ ዞን በሻሻ ወረዳ ተገኝተው መርጠዋል።

    በዚህ አገራዊ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ ያስታወቀ ሲሆን፣ በምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ።

    ምርጫውን ከአገር ውስጥ ታዛቢዎች ባሻገር የአፍሪካ ኅብረት እና ኢጋድ ይታዘቡታል።

  8. ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች

    ለሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ዛሬ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. መራጮች በየአካባቢያቸው ድምጽ እየሰጡ ነው። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትግራይ ክልል እና ከአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጪ ምርጫው እንደሚካሄድ አስታውቋል።

    ለዚህ ምርጫ 50.5 ሚሊዮን ሰዎች በመራጭነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ ይህም አገሪቱ ካላት አዋቂ ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛው የሚበልጥ ነው።

    የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንሚያመለክተው ለመራጭነት ከተመዘገቡት ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መካከል ሴቶች 46 በመቶ እንዲሁም ወንዶች 54 በመቶ ናቸው።

    ዘንድሮ በመራጭነት የተመዘገቡት ዜጎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከተመዘገቡት በ32 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ካለፉት ስድስት ምርጫዎችም የበለጠ ነው።

    ሥዕላዊ መግለጫ
  9. የሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ በምስል

    ሐመር ምርጫ ክልል፣ ቆላጃ አንጉዴ ምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ

    የፎቶው ባለመብት, NEBE

    የምስሉ መግለጫ, ሐመር ምርጫ ክልል፣ ቆላጃ አንጉዴ ምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ
    የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚመሩት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መጀመርን ሲታዘቡ

    የፎቶው ባለመብት, ETV

    የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚመሩት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መጀመርን ሲታዘቡ
    የኢጋድ ምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በጅማ ተገኝተው የድምጽ አሰጣጥ አጀማመሩን ሲከታተሉ

    የፎቶው ባለመብት, EBC

    የምስሉ መግለጫ, የኢጋድ ምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በጅማ ተገኝተው የድምጽ አሰጣጥ አጀማመሩን ሲከታተሉ
    በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት የተጀመረው ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ነው

    የፎቶው ባለመብት, EBC

    የምስሉ መግለጫ, በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ድምጽ የሚሰጡ መራጮች
    የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ድምፃቸውን ሲሰጡ

    የፎቶው ባለመብት, EBC

    የምስሉ መግለጫ, የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ድምፃቸውን ሲሰጡ
  10. የኢትዮጵያ ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው

    ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ መራጮች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት መምረጥ ጀምረዋል

    የፎቶው ባለመብት, FBC

    የምስሉ መግለጫ, ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ መራጮች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት መምረጥ ጀምረዋል

    ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላ አገሪቱ በሚካሄደው ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ መስጠት ተጀምሯል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በአማራ ክልል ደግሞ በተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫው በዛሬው ዕለት እንደማይካሄድ ቀደም ብሎ አስታውቋል።

    ምርጫ ቦርድ በአማራ ክልል በስምንት የምርጫ ክልሎች በዛሬው ዕለት ድምጽ እንደማይሰጥ ሲያሳውቅ ከጠቀሳቸው ቦታዎች መካከል ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ደጋ ዳሞት እና አምባሰል ይገኙበታል።

    በሰባተኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ከ 54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ቦርዱ መግለጹ አይዘነጋም። በምርጫው የሚሳተፉ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሆኑ ፓርቲዎቹ ከ10,000 በላይ እጩዎች ለማስመረጥ አስመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥም 2,080 ለፓርላማ የሚወዳደሩ ይሆናል። 8,352 እጩዎች ደግሞ ለክልል ምክርቤት ሲዎዳደሩ፤ 80 እጩዎች በግላቸው ይወዳደራሉ። 55 የአገር ውስጥ ሲቪክ ማኅበራት ምርጫውን የሚታዘቡ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የታዛቢ ቡድን አሰማርቷል።

    የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡደንን የሚመሩት ደግሞ ቀድሞው የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ስፔሲዮሳ ዋንድሬ ካዚምብዌ ናቸው።