ቤላሩስ የዩክሬን አየር መከላከያ ሚሳኤልን መትቼ ጣልኩ አለች

የሚሳኤል ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቤላሩስ የዩክሬን አምባሳደርን አስጠርታ በግዛቷ ውስጥ የገባውን የዩክሬን አየር መከላከያ ሚሳኤል መትታ መጣሏን አስታወቀች።

የሩሲያ ጠንካራ አጋር የሆነችው ቤላሩስ መትታ ስለጣለችው ሚሳኤል ዩክሬን ጥብቅ ምርመራ እንድታደርግ አሳስባለች።

የቤላሩስ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሳኤል ስብርባሪ በቤላሩስ ግዛት በሚገኝ የእርሻ ቦታ ላይ ወድቆ አሳይቷል።

የዩክሬን ጦር ቃል አቀባይ ክስተቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “የአየር መከላከል ውጤት ነው” ብለዋል።

ኤስ-300 ሮኬት ተመትቶ ከወደቀ በኋላ በቤላሩስ የዩክሬን አምባሳደር ሚንስክ በሚገኘው የውጭ ጉዳይ ሚንስሬር ተጠርተዋል።

“ቤላሩሳውያን ይህን ክስተት እጅግ አደገኛ እንደሆነ ይመለከቱታል” ሲሉ የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ መሰል ክስተት ዳግም እንዳይከሰት ሮኬቱ የተተኮሰበንት ሁኔታ ዩክሬን ጥልቅ ምርመራ እንድታደርግ አሳስበዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚንስቴር በበኩሉ የአገሪቱን የአየር ክልል የመጠበቅ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን አስታውሶ ክስተቱን በተመለከተ “ለአሸባሪው የሩሲያ መንግሥት” ድጋፍ ከሌለው አገር የሚወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ምርመራ ማድረግ ይችላል ብሏል።

ቤላሩስ ብረስት በተባለ ክልሏ ከዩክሬን 15 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የድንበር ቦታ ሚሳኤሉ መውደቁን አስታውቃለች።

የሞስኮ አጋር የሆነችው ሚንስክ፤ ከ10 ወራት ገደማ በፊት ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ስትፈጽም ግዛቷን እንድትጠቀም ፈቅዳ ነበር።

በቅርብ ቀናት የዩክሬን ባለስልጣናት ሩሲያ በቤላሩስ በኩል አዲስ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ነው እያሉ ነው። ባለስልጣናቱ ይህን ይበሉ እንጂ ምዕራባውያን ግን ለዚህ ምንም ማስረጃ የለም ብለዋል።

ይህ የዩክሬን አየር መከላከያ ሚሳኤል በቤላሩስ ተመትቶ የመውደቁ ዜና የተሰማው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው የአየር ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት ነው።

ሞስኮ ትናንት ሐሙስ ዩክሬን ከተሞች ወደሆኑት ኪዬቭ፣ ካርኪቭ፣ ላቪቭ እና ኦዴሳ በርካታ ሚሳኤሎቸን ተኮሳለች።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሚሳኤል ጥቃቱን ተከትሎ በዚህ ቀዝቃዛማ ወቅት በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል ብለዋል።