አሜሪካ የሶማሊያ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ማዕቀብ እንደምትጥል አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሶማሊያ መሪዎች የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን እንዲያከብሩና ተጨማሪ መዘግየት እንዳይኖር አስጠንቅቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምርጫው የሚዘገይ ከሆነ የቪዛ ገደቦችን ጨምሮ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችን እንደሚጥል አስታውቋል።
አገሪቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልታደርገው ባቀደችው አዲሱን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የካቲት 18፣ 2014 ዓ.ም ምርጫ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት አሜሪካ አስታውቃለች።
ሶማሊያ አዲሱ የምርጫ ቀን የወሰነችው በሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የክልል አስተዳደር መሪዎች መካከል ለተወሰኑ ቀናት በሞቃዲሾ ሲደረጉ የነበሩ ስብሰባዎችን ተከትሎ ነው።
"ሁሉም የሶማሊያ የፌደራልና የክልል መሪዎች የተስማማችሁበትን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እንድታከብሩ እና የአሰራር ሂደቱን እንድታስተካክሉ እንጠይቃለን" በማለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አትቷል።
ለህዝብ ተወካዮች የሚደረገው ምርጫ መካሄድ የነበረበት በህዳር ወር ተጀምሮ እስከ ታህሳስ አጋማሽ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም በነበሩ እሰጣገባዎች ምክንያት ዘግይቷል።
ከ275 የታችኛው ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ጥቂቶች ብቻ ናቸው የተሞሉት።








