ቀጥታ, አሜሪካ ቴህራን ላይ አዲስ ጥቃት ስትከፍት፤ ኤምሬትስ ኢራን በመርከቦቿ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት አወገዘች

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢራን ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦቼ ላይ ከባድ ጥቃት ፈፅማለች ስትል ኢራንን ከሰሰች። "አሳፋሪ" ስትል በገለፀችው በዚህ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጻለች። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ መተላለፊያ የመዝጋት እቅዷ አካል አድርገው ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ የሳዑዲው ልዑል በሁቲዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታቸውን ሰጡ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተጨባብጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን በሁቲ ታጣቂዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ይሁንታቸውን መስጠታቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘገበ።

    ሳዑዲ ሰኞ ዕለት በሰነዓ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን ይህንን ተከትሎ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች እአአ ከ2022 ወዲህ ትልቅ ነው የተባለ የአጸፋ እርምጃ ወስደዋል።

    ይህም ለአራት ዓመታት ዘልቆ የቆየውን ይፋዊ ያልሆነ የሰላም ስምምነት ያፈረሰ መሆኑ ተገልጿል።

    የሳዑዲው ልዑል አስቀድመው ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት አገራቸው ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር ባለው መጠነ ሰፊ ግጭት ዙሪያ ስጋት እንደገባት እና የአሜሪካን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንደምትፈልግ መጠየቃቸው ተገልጿል።

    ሳዑዲ አረቢያ ይህንን ጠየቀችው ባለፈው ሳምንት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሐሙስ ዕለት በዋሺንግተን የሳዑዲ አምባሳደር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተገናኝተዋል።

    ከአንድ ቀን በኋላም ሩቢዮ የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሳል ቢን ፋርሃንን ጋር ተነጋግረዋል።

    አርብ ዕለት ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሳዑዲው ልዑል ጋር በስልክ ተወያይተዋል ተብሏል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሳዑዲው ልዑል በሁቲ ላይ የሚፈጸም ወታደራዊ እርምጃን አሜሪካ እንድትደግፍ ትራምፕን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

    ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ቢጠየቅም በቀጥታ ምላሽ አልሰጠም።

    በዋሺንግተን የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲም በዘገባው ላይ ያለው ነገር የለም።

    በሳዑዲ እና በሁቲ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ የተጀመረው ከአስር ቀን በፊት የኢራን አውሮፕላን ሁቲዎች በሚቆጣጠሩት ሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ ነው።

    አውሮፕላኑ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነስርዓትን ላይ ለመገኘት የሚሄዱ የልዑካን ቡድንን ጭኖ መመለሱ ተገልጿል።

    ሳዑዲ አረቢያ ከአስር ዓመት በፊት ከኢራን ወደ ሰነዓ የሚደረግ በረራን አግዳለች።

    ሰኞ ዕለት የኢራን አውሮፕላን የልዑካን ቡድንኑን ይዞ ሲመለስ ሳዑዲ የሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያን ደብድባለች።

    አውሮፕላኑ አቅጣጫውን ቀይሮ በአል ሁዳይዳህ ለማረፍ ተገድዷል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ የጦር መሣሪያዎችን፣ የሚሳዔል ክፍሎችን እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ጭኗል ሲሉ ከስሰዋል።

    ሁቲዎች የሳዑዲ ጥቃትን ተከትሎ በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ወደሚገኘው አብሃ አውሮፕላን ማረፊያ ባሌስቲክ ሚሳዔል አስወንጭፈዋል።

  2. አሜሪካ አዲስ ጥቃት ስትከፍት፤ ኤምሬትስ ኢራን በመርከቦቿ ላይ የፈፀመችውን ጥቃት አወገዘች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያሉ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢራን ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦቼ ላይ ከባድ ጥቃት ፈፅማለች ስትል ኢራንን ከሰሰች።

    " አሳፋሪ" ስትል በገለፀችው በዚህ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጻለች።

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ መተላለፊያ የመዝጋት እቅዷ አካል አድርገው ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

    ይህም ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።

    የአሜሪካ ጥቃቶች ለሦስተኛ ቀን የቀጠሉ ሲሆን ፕሬዚደንት ትራምፕ ኢራን ‘በከባዱ’ እንደተመታች ተናግረዋል።

    የሁለቱ አገራት ጥቃት ተባብሶ ቀጥሏል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትራምፕ መተለላፊያው ላይ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ ቴህራን የወሽመጡ “ጠባቂ” ሆና ትቀጥለላች ሲሉ ትራምፕ የተጠቀሙትን ቃል በመጠቀም ምላሽ ሰጥተዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር ያለው ውዝግብ የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማስቆም ያለውን ጥረት አመንምኖታል።

    ሆኖም ትራምፕ አሁንም ቢሆን ስምምነት ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል።

    ውጥረቱ በቀጠለበት በዚህ ወቅትም ነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢራን ክሩዝ ሚሳኤሎች ሁለት የአገሪቷን ታንከሮች ዒላማ ማድረጋቸውን የገለፀችው።

    በጥቃቱ አንድ ሕንዳዊ የመርከበኞች ቡድን አባል ሲገደል፣ ስምንት መቁሰላቸውን እና የአራቱ ከባድ ጉዳት መሆኑን ጠቅሳለች።

    ከተጎዱት መካከል ስድስቱ ሕንዳውያን ሲሆኑ ሁለቱ ዩክሬናዊያን እንደሆኑ የኤምሬስትስ መከላከያ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    “ሚኒስቴሩ ይህንን ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ስምምነቶችን በግልጽ የጣሰውን እና በቀጣናው መረጋጋት እና ፀጥታ ላይ ስጋት የደቀነ ጥቃት ያወግዛል” ብሏል።

  3. ትራምፕ በኢራን ወደቦች ላይ በድጋሚ እገዳ ጣሉ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ በድጋሚ በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ እንደምትጥል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

    በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ገጻቸው “የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ነው፤ ኢራን አለችም አላለችም ተከፍቶ ይቆያል። ኢራን ላይ በድጋሚ እገዳ ይጣላል” ብለዋል።

    እገዳው የኢራን መርከቦች “እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ” እንደሚያደርግ እና ለሌሎች አገራት ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ፍትሐዊ እና ክፍት” ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

    “ከዚህ በኋላ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ጠባቂ ናት” ያሉት ትራምፕ፤ ሁሉም የንግድ መርከቦች 20% ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል።

    ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ እንዲቻል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን እንደሚውል አክለዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደምም በኢራን ወደቦች ላይ እገዳ ጥለው እንደነበር ይታወሳል።

    ኢራን ከነዳጅ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለመገደብ በሚል የወደብ እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳ ተጥሎ ቆይቷል።

    የተባበሩት መንግሥታት የማሪታይም ተቋም እንደሚለው የትኛውም አገር ዓለም አቀፍ መተላለፊያን የመቆጣጠር ሕጋዊ መብት የለውም።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ እገዳው ተነስቶ ነበር።

    አሁን ትራምፕ በድጋሚ እገዳውን ጥለው 20% ክፍያ እንደሚኖርም ተናግረዋል።

  4. “አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር ጣልቃ እንድትገባ አንፈቅድም”- ኢራን

    የጦሩ ቃል አቀባይ

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ፤ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር “ጣልቃ እንድትገባ እንደማይፈቅድ” አስታወቀ።

    የኢራን ጦር “የአሜሪካ ተደጋጋሚ የጀብደኝነት እንቅስቃሴ የቀጣናውን ደኅንነት ክፉኛ አውኳል” ማለቱን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትቆጣጠር “አልፈቀድንም፤ አንፈቅድምም” ሲልም የኢራን ጦር አክሏል።

    ከአሜሪካ “ሽፍታ ጦር” የተቃጡ ረብሻዎችን እንደሚቆጣጠር አስታውቋል።

    ከአሜሪካ ጋር የሚደረግ ትብብር የኢራንን ሉዓላዊነት የሚጥስ “የጦርነት ድርጊት” ተደርጎ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል።

    “ጦርነቱ ከተባባሰ ቀጣናውን ያዳርሳል” ማለቱም ተዘግቧል።

  5. ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንቆጣጠረዋለን” በማለት ዛቱ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነቱን “መጣሷን” ጠቅሰው አገራቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን “እንደምትቆጣጠር” ገለጹ።

    ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የሆርሙዝ ወሽመጥን እንቆጣጠረዋለን። ምንም ነገር የላቸውም” ብለዋል።

    ትናንት ምሽት አሜሪካ ኢራንን “ክፉኛ መደብደቧን” ተናግረዋል።

    “ይዘናቸዋል፤ እያሳደድናቸው ነው። አብዛኞቹ መሣሪያዎቻቸው ወድመዋል” ሲሉም አክለዋል።

    በዩናይትድ ኪንግደም የኢራን ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጊዜያዊ መተላለፊያ እንዳዘጋጀ አስታውቋል።

    መተላለፊያው “ከቴክኒክ እና ወታደራዊ ክልከላ” ነጻ እንደሆነ ገልጿል።

    አሜሪካ ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ መተላለፊያ ነው” ብላለች።

    ከአሜሪካ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ኢራናውያን ትናንት “11 ሰዓት የወሰደ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    “የተወሰኑ ለውጦች ማድረግ አለብን” ብለው ከውይይቱ ክፍል እንደወጡ ጠቅሰውም “ሁሌም ለውጥ ያደርጋሉ፤ የሠለጠኑ ተደራዳሪዎች ናቸው፤ ጎበዝ ግን አይደሉም። ለእኔ ምንም ይዘው አልመጡም” ሲሉም አክለዋል።

  6. ዩኬ ለኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ድጋፍ መስጠትን አገደች

    ሻባና ማሕሙድ

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ለዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ደኅንነት አስጊ ተብሎ እንደሚፈረጅ የአገር ውስጥ ጉዳይ ጸሐፊዋ ሻባና ማሕሙድ ተናገሩ።

    ለዩኬ ምክር ቤት በጽሑፍ ባቀረቡት መግለጫ መሠረት ስለ እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አወንታዊ አስተያየት ከመስጠት አንስቶ ድጋፍ እስከማድረግ ድረስ ያሉ ድርጊቶች እስከ 14 ዓመት እስራት የሚያስቀጡ ይሆናሉ።

    የኢራን ደጋፊ የሆነው ወታደራዊ ቡድን ‘ኢስላሚክ ሙቭመንት ኦፍ ኮምፓኒየንስ ኦፍ ዘ ራይት’ እንዲሁም የሩሲያ ወታደራዊ ስለላ ተቋም ክንፍ የሆነው ‘ዘ ቮሉንተር ኮርፕስ ኦፍ ራሽያስ ጂአርዩ’ ላይም እገዳ ተጥሏል።

    ለፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማት በሚሰጣቸው አዲስ ሥልጣን አማካኝነት የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ በእነዚህ ቡድኖች የሚፈጸም ጥቃት እንዲሁም ስለላን መከላከል እንደሚቻል ተገልጿል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በዩናይትድ ኪንግደም የአይሁድ እና እስራኤላዊ ማኅበረሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ሰባት ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታመናል።

  7. በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር መቀነሱ ተገለጸ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።

    የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው ድረ ገጽ 'ማሪን ትራፊክ' እንደሚጠቁመው ከትናንት እሑድ ምሽት ጀምሮ አንዳችም የንግድ መርከብ በወሽመጡ አላለፈም።

    ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ስምንት መርከቦች አልፈዋል።

    ኢራን የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ አሜሪካ “በርካታ” የቴህራን ወታደራዊ ዒላማዎችን እንደመታች አስታውቃለች።

    በተለያዩ የኢራን አካባቢዎች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ጦር የቴህራንን የአየር መቃወሚያ፣ የባሕር መቆጣጠሪያ፣ ሚሳዔሎች እንዲሁም አነስተኛ ጀልባዎችን መምታቱን ገልጿል።

    ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በዮርዳኖች፣ ባህሬን፣ ኩዌት እና ኦማን ላይ ጥቃት አድርሳለች።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች መተላለፍ ማቆማቸው በአውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያስከትል ተዘግቧል።

    የአውሮፓ ኅብረት የኢነርጂ ግብረ ኃይል ዛሬ ያደረገውን ውይይት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አሁን ላይ ያለው ክምችት “የተረጋጋ” መሆኑን ጠቅሷል።

    ሆኖም ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት በመስተጓጎሉ የአውሮፓ አገራት ለነዳጅ እጥረት እንደሚጋለጡ ተመልክቷል።

  8. አውሮፓ ያላት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ያነሰ መሆኑ ተዘገበ

    አውሮፕላን ላእ ነዳጅ የሚቀዳ ቦቴ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአውሮፓ አገራት የአውሮፕላን ነዳጅ ክምችት ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    አውሮፓ ለአውሮፕላን የምትጠቀምበትን ነዳጅ እያስገባች ያለችው ከአሜሪካ እና እስያ ሲሆን ይህም ያላት ክምችት እንዲሳሳ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።

    በመካከለኛ ምሥራቅ ዳግም ያገረሸው ግጭት አውሮፓ የአውሮፕላን ነዳጅ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ዳግመኛ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።

    በተለይ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ የበለጠ ተጎጂ የሆኑ አገራት ናቸው።

    የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመት፤ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በመቀስቀሱ ተዘግቶ ቆይቷል።

    ወሽመጡ በሰኔ ወር ላይ በከፊል ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ዳግም ያገረሸው ግጭት የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    በሐምሌ ወር ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም አሜሪከ እና ኢራን ዳግም መታኮስ በመጀመራቸው የመርከቦች እንቅስቃሴን ገድቧል።

    የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ ያለው ነዳጅ መመናመኑን ገልጾ ሁኔታው በነሐሴ ወር የበለጠ ሊባባስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።

    በየካቲት መጨረሻ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ጦርነት እስኪጀመር ድረስ የአውሮፓ አገራት ግማሽ የሚሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ ያገኙ የነበረው ከመካከለኛ ምሥራቅ አገራት ነበር።

    ተንታኞች የአፍሪካ አገራት መጋቢት ላይ የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተንብየው ነበር።

    ቢሆንም ከናይጄሪያ የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ እዲሁም ሕንድ እና ኦማን ማስገባት በመጀመራቸው እጥረቱ ተቃልሏል።

    በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ አገራት ከካናዳ ነዳጅ መግዛት መጀመራቸው ተሰምቷል።

    አሜሪካ እና ናይጄሪያ ወደ አውሮፓ ነዳጅ የሚልኩ ዋነኞቹ አገራት ናቸው። ነገር ግን ኩዌት፣ ካናዳ፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮሪያ የአውሮፕላን ነዳጅ ያቀርባሉ።

  9. ኢራን “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ሆርሙዝን በተመለከተ ከኦማን ጋር ስምምነት ላይ አለመድረሷን ገለጸች

    መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን እና ኦማን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ያደረጉት “በአሜሪካ ጫና” ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ቴህራን አስታወቀች።

    በኢራን እና አሜሪካ ጦርነት እንዲሁም ድርድር የክርክር ማዕከል የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከዓለም ነዳጅ እና ጋዝ ምርት ውስጥ 20 በመቶ ገደማው ይተላለፍበት የነበረ የወሳኝ የባሕር መስመር ነው። ከጦርነቱ ወዲህ በወሽመጡ ላይ ያላትን ቁጥጥር ያጠናከረችው ኢራን፤ በሆርሙዝ ሌላኛው ጫፍ ከአሁን በኋላ ከምትገኘው ኦማን ጋር በመነጋገር እንደምታስተዳድረው ስትናገር ቆይታለች።

    የኢራን እና ኦማን ባለሥልጣናት ትናንት ቅዳሜ ዕለት የባሕር መስመሩን ትራፊክ አስተዳደር በተመለከተ መወያየታቸው ተገልጾ ነበር።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ ዛሬ ሰኞ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በኦማን ዋና ከተማ በተካሄደው ውይይት ስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቀዋል። ቃል አቀባዩ፤ “ቅዳሜ ዕለት ሙስካት ውስጥ የተደረገው ንግግር [ከአሜሪካ ጋር በተፈረመው] የመግባቢያ ስምምነት አንቀጽ 5 ላይ በሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር” ብለዋል።

    አክለውም፤ “አሜሪካ ግልጽ እና ድብቅ በኦማን ላይ ባሳደረችው ጫና ምክንያት መከናወን የነበረበት ነገር ባለመሳካቱ እና ባለመፈጸሙ እናዝናለን" ሲሉ ዋሽንግተንን ተጠያቂ አድርገዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኢራን ሆርሙዝ በድጋሚ መዘጋቱን ካስታወቀች በኋላ ከትናንት ምሽት አንስቶ እስካሁን ምንም መርከብ በወሽመጡ እንዳላለፈ ‘ማሪን ትራፊክ’ ከተሰኘው የመርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ አሳይቷል።

    ኢራን የአሜሪካ ጦር በሚያደርገው “ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ” ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በሆርሙዝ በኩል ጉዞ ማድረግ “የማይቻል” መሆኑን በትናንትናው ዕለት ገልጻ ነበር።

    አሜሪካ በበኩሏ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ክፍት ነው በሚል አቋሟ ጸንታለች። የአሜሪካ ማዕከላዊ እዛ በወጣው መግለጫ ሆርሙዝ ክፍት እንደሆነ እንዲሁም ጦሩ የመርከብ ጉዞ ነጻነትን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

  10. የአሜሪካ ጦር ኢራንን መደብደቡን ሲቀጥል፤ ቴህራን የባሕረ ሰላጤው አገራትን ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አስፋፋች

    የአሜሪካ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, centcom

    አሜሪካ እሁድ ሌሊት ኢራን ውስጥ በፈጸመችው ድብደባ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን ለማጥቃት ጥቅም ላይ ይውላል ያለችውን የሚሳዔል ክምችት መምታቷን አስታወቀች።

    ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጠው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በፈጸማቸው የአጸፋ ጥቃቶችን በርካታ ዒላማዎችን ማውደሙን ገልጿል።

    ካለፈው ሳምንት ወዲህ በድጋሚ ያገረሸው የአሜሪካ እና ኢራን ግጭት፤ ወደ ሌላ ሳምንት ተሸጋግሯል። ቅዳሜ ዕለት አሜሪካ በመላው ኢራን የሚገኙ ከ140 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታውቃ ነበር። እንደ አሜሪካ ገለጻ ይህ ጥቃት የተፈጸመው የኢራን ኃይሎች በሆርሙዝ ወሽመጥ ይጓዙ የነበሩ መርከቦችን በማጥቃታቸው ነው።

    መርከቦቹ በትክክለኛው የጉዞ መስመር ላይ እንዳልነበሩ የገለጸችው ኢራን በአንጻሩ፤ ከእሁድ ዕለት አንስቶ በድጋሚ እስኪገለጽ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን አስታውቃለች። በተጨማሪም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በትናንትናው ዕለት በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና አጋሮቿ ጋር ጥቃት አድርሷል።

    በዚህ መልኩ ከፍ ወዳለ ደረጃ የደረሰው የሁለቱ አገራት ግጭት፤ ትናንት ሌሊትም ቀጥሏል። የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) እሁድ ሌሊት ኢራን ላይ በከፈተው አዲስ ዙር ጥቃት የቴህራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥቃት የማድረስ አቅም ይቀንሳል ያለውን ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ኃይሎች ኢራንን አየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ የባህር ዳርቻ የራዳር ማዕከላትን፣ የሚሳዔል እና የድሮን አቅሞችን እንዲሁም አነስተኛ የጦር መርከቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ገልጿል። በዚህ ወደታራዊ ዘመቻ ላይ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች፣ የባህር ኃይል መርከቦች እንዲሁም ለዚህ ዘመቻ ለመጀመሪያ ጊዜ የባሕር ኃይል አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ዘርዝሯል።

    ማዕከላዊ ዕዙ ባወጣው መግለጫ፤ “ሆርሙዝ ወሽመጥ ለዓለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ ነው። ኢራን አትቆጣጠረውም” ብሏል። የአሜሪካ ኃይሎች “የንግድ መርከቦችን የጉዞ ነጻነት ለማረጋገጥ ዝግጁ” መሆናቸውንም አክሏል።

    በተመሳሳይ መግለጫ ያወጣው ኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩሉ የአሜሪካ ጦር ይዞታዎችን ይዘዋል በተባሉ በቀጣናው አገራት ላይ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል። ባህሬን፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ጥቃት የተፈጸመባቸው አገራት እንደሆኑ ተጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ፤ "ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው ፕሪንስ ሀሰን የአየር ኃይል ጦር ሰፈር በርካታ ትላልቅ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና የነዳጅ ታንከሮች በሚሳዔል እንዲሁም ድሮን ጥቃቶች በእሳት ጋይተዋል" ብሏል።

    እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት ለአሜሪካ ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት መሆኑን የገለጸው አብዮታዊ ዘቡ፤ ባሕሬን ውስጥ ደግሞ “ወሳኝ የአሜሪካ ጦር የሄሊኮፕተር ጥገና ማዕከላትን፣ የፒ8 የኤሌክትሮኒክስ የጦር አውሮፕላን ማቆሚያዎችን እንዲሁም የድሮን ዕዝ እና ቁጥጥር ማዕከልን” መምታቱን ገልጿል።

    ለአብዮታዊ ዘቡ ቅርበት ያላቸው የዜና ወኪሎች ኩዌት ውስጥ ፍንዳታ መሰማቱን የዘገቡ ሲሆን፤ አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ ፍንዳታው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግሯል።

    እንደ የተጀመረው ጥቃት አሜሪካ እና ኢራን ተፈራርመውት የነበረውን የጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ውስጥ ጥሎታል። ይህ ስምምነት ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እንዲሁም ግጭቱ በቋሚነት እንዲቆም የማድረግ ዓላማ ነበረው።

    ይሁን እንጂ አደራዳሪዎች ስምምነቱን በድጋሚ ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።