ቀጥታ, ለምርጫ አንድ ቀን የቀራቸው የእስራኤሉ መሪ ኔታንያሁ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አውድመናል አሉ

ነገ ማክሰኞ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፣ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የማውደሙ ሥራ 90 በመቶው መጠናቀቁን እና የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ ኔታንያሁን ምረጡ” ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስራኤል ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት የማድረስ ዕቅድ እንደሌለ ተገለጸ

    የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣናት

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት እስራኤል ካትዝ በአገራቸው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት የመሰንዘር ዕቅድ እንደሌለ ገለጹ።

    ኢራን ላይ አዲስ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድን በተመለከተ በእስራኤል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል መባሉን “መሠረተ ቢስ” ሲሉ አጣጥለዋል።

    ቻናል 12 የተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ ማንነታቸውን ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ጠቅሶ ትናንት እሑድ እንደዘገበው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪ ኢያል ዛሚር መካከለር አለመግባባት ተፈጥሯል።

    አለመግባባቱ አዲስ ትዕዛዝን የተመለከተ እንደሆነ ቢገለጽም ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ኔታንያሁ ዘገባውን ሐሰተኛ ሲሉ አጣጥለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የዘገባው ዓላማ በምርጫው ዋዜማ የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር የሚያስተላልፈው ውሳኔ ላይ ጥርጣሬ ማጫር ነው።

    የቴሌቭዥን ጣቢያው ዘገባ እንደሚያሳየው ወታደራዊ መሪው ስብስባ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ከመፈጸማቸው በፊት ከፖለቲካ አመራሮች የሕግ ማዕቀፍን በተመለከተ መረጃ ተሰጥቷቸዋል።

    ጥያቄ የተነሳበት ትዕዛዝ ይዘትን በተመለከተ ዘገባው ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። ሆኖም ግን በወታደሮች ዘንድ ጦርነት ለፖለቲካዊ ዓላማ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

  2. ኡጋንዳ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚመለሱ ዜጎቿ ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አዘዘች

    የኡጋንዳ የጤና ሚኒስትር ክሪስ ባርዮሙንሲ
    የምስሉ መግለጫ, የኡጋንዳ የጤና ሚኒስትር ክሪስ ባርዮሙንሲ

    የኢቦላ ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የጣለቻቸውን ገደቦች እያጠበቀች ያለችው ኡጋንዳ፣ ከጎረቤት አገር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመለሱ ዜጎቿ ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ (ኳረንቲን) እንዲገቡ እንደሚደረግ አስታወቀች።

    በዴሞክራቲክ ኮንጎ ታሪክ እጅግ የከፋ የሆነው ኢቦላ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ግንቦት አንስቶ ከ4,800 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ወረርሽኙም ወደ ሌሎች አገራት ተዛምቷል።

    የኡጋንዳ ጤና ሚኒስቴር አዲሱን እርምጃ ይፋ ያደረገው፣ በአገሪቱ በኩል አቋርጠው የተጓዙ ሁለት ሰዎች በኬንያ እና በናይጄሪያ የኢቦላ ምርመራ ተደርጎላቸው በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡ ጥያቄ ካስነሳ በኋላ ነው።

    ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ከኬንያዊው የኢቦላ ታማሚ ጋር ንክኪ ስላላቸው ክትትል ሥር የነበሩ 60 ሰዎች በሙሉ ነጻ በመሆናቸው መሰናበታቸውን አስታውቋል።

    ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተጉዘው የነበሩ መንገደኞች በኡጋንዳ በኩል አቋርጠው እንዲያልፉ እንደማይፈቀድላቸው ተነግሯል።

    ሚኒስቴሩ አክሎም ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተጉዘው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኡጋንዳውያ “በራሳቸው ወጪ 21 ቀናትን ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚያሳልፉ” ገልጿል።

    ጤና ሚኒስቴሩ “በኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በሁሉም የየብስ ድንበር ማቋረጫዎች ላይ የሚደረገውን የተጓዦች ፍተሻ የተጠናከረ ሲሆን በተመረጡ የመንገድ ፍተሻ ኬላዎችም ምርመራው ይደረጋል” ብሏል።

    የኡጋንዳ የጤና ሚኒስትር ክሪስ ባርዮሙንሲ ከቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚመጡ ወሳኝ ተጓዦች ብቻ እንዲገቡ እንደሚፈቀድላቸው ተናግረዋል። እነርሱም ቢሆን “ጥብቅ የሕዝብ የጤና እርምጃዎች” እንደሚወሰድባቸው አብራርተዋል።

  3. የሰርቢያው አንጋፋ መሪ ቩቺች በተማሪዎች የአመጽ እንቅስቃሴ በመሸነፋቸው የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ነው

    ደስታ በሚገለጽበት ጎዳና ላይ በመኪና መስኮት በኩል ወጥታ በፈገግታ የምትመለከት ሴት

    ሰርቢያን ለረጅም ጊዜ የመሩት አሌክሳንደር ቩቺች የተማሪዎችን የተቃውሞ ንቅናቄ ተከትሎ በድንገተኛ የፓርላማ ምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ።

    “የመጨረሻውን ውጤት እስካሁን ባይደርሰንም በምርጫው መሸነፋችን ግን ግልጽ ነው” ሲሉ የቀኝ ዘመሙ ሕዝበኛ መሪ እሁድ ምሽት ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል።

    የሰርቢያ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ተሳትፎ እንደነበረ አመልክተዋል።

    ቩቺች ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰርቢያ በርካታ አካባቢዎች ሰዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል።

    ቩቺች ድንገተኛ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት በኖቪ ሳድ ከተማ የባቡር ጣቢያ ጣሪያ ወድቆ 16 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ለሁለት ዓመታት የቀጠሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከተካሄዱ በኋላ ነው።

    የባቡር ጣቢያው አደጋ በሰርቢያ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና እና የቸልተኝነት ምልክት ተደርጎ በመታየቱ ነው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።

    የሰርቢያ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ መሪው ቩቺች፣ ለሁለት የፕሬዚደንትነት ዘመናት ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር የማይችሉ በመሆኑ፣ እአአ ከ2017 ጀምሮ ወደለቀቁት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመመለስ ዓላማ ነበራቸው።

    የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተመሰረተው እና ምርጫውን ያሸነፈው የ’ስቱደንት ሊስት’ መሪ ኢሊያ ስርዳኖቪች “ነጻ መንግሥት ይመሰረታል” ሲሉ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግረዋል።

    በመላው ሰርቢያ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚ መራጮችን ያሰባሰበው የፀረ ሙስና ንቅናቄ “አገሪቱን ከግፍና ከጭቆ እና አገዛዝ ነጻ ያወጣል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

    በቤልግሬድ ስላቪያ አደባባይ የተሰበሰቡ በርካታ የ“ስቱደንት ሊስት” ደጋፊዎችን የሚያሳይ ፎቶ
  4. ሁቲዎች በሳዑዲ አየር ማረፊያ እና ነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹ

    በሪያድ የሚገኘው አየር መንገድ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም 13 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር
    የምስሉ መግለጫ, በሪያድ የሚገኘው አየር መንገድ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም 13 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር

    የየመን ሁቲዎች ዛሬ ሰኞ የሪያድ አየር ማረፊያ እና በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    በየመን የሚገኘው እና በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በበኩሉ ሁቲዎች ዛሬ ጠዋት ወደ ሪያድ የተተኮሰን ሚሳዔል ማክሸፉን እና በየመን ሰንዓ ውስጥ ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል።

    ሁቲዎች በሳዑዲ መዲና የሚገኘውን የኪንግ ካሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ባሊስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን እና ጥቃቱ “ዒላማውንም በትክክል መምታቱን” የቡድኑ ቃል አቀባይ ከሁቲ ጋር ግንኙነት ላለው አል ማሲራህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

    ሁቲዎች አየር ማረፊያው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹት በጥቅምት መጀመሪያ በተፈጸመበት እና 13 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት ምክንያት ያቆመውን አገልግሎት ትናንት እሁድ በከፊል መጀመሩን ባስታወቀ ማግሥት ነው።

    ታጣቂ ቡድኑ ከአየር መንገዱ በተጨማሪ በአገሪቱ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎችን በድሮን መምታቱን ገልጿል። ሳዑዲ በአየር ማረፊያው ላይም ሆነ በነዳጅ ማውጫዎች ላይ ተፈጽመዋል ስለተባሉን ጥቃቶች እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የሳዑዲ ሲቪል መከላከያ በዋና ከተማው ሪያድ ውስጥ አደጋ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይም ስጋቱ ማለፉን አስታውቋል።

    ሁቲዎች ጥቃት ማድረሳቸውን ያስታወቁት በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን መዲና ሰንዓ የሚገኙ ሁለት የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን ካስታወቀ በኋላ ነው። ከእነዚህ ማስወንጨፊያዎች አንዱ ጥምር ጦር እንዳከሸፈው የገለጸውን እና ወደ ሪያድ የተተኮሰውን ባለስቲክ ሚሳዔል ለማስወንጨፍ ጥቅም ላይ የዋለ እንደነበር ተገልጿል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ሳዑዲ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማጠናከራቸውን ተከትሎ አሜሪካ በአገሪቱ የሚገኙ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ ባልደረቦች እና ቤተሰቦቻቸው ከሳዑዲ እንዲወጡ ማዘዟ ይታወሳል።

  5. ጋቦን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ አነሳች

    በሞባይል ላይ የሚታዩ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች

    በማዕከላዊ አፍሪካ የምትገኘው ጋቦን ሰፊ ተቃውሞ እና ትችት አስከትሎባት የነበረውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጣለችውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ ማንሳቷን አስታወቀች።

    መንግሥት በበይነ መረብ የሚለቀቁ ይዘቶች ግጭትን እያባባሱ እና በአገሪቱ ውስጥ ክፍፍልን እያስፋፉ ነው በሚል ነበር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ እገዳውን የጣለው።

    ይህ እርምጃ ወደ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ጋቦን ውስጥ መነጋገሪያ ሆኗ ቆይቷል። በአገሪቱ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ኢንስታግራም በተለይ በወጣቶች ዘንድ ለንግድም ሆነ ለመዝናኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ነበሩ።

    እገዳው ከተጣለ በኋላ በርካቶቹ የአገሪቱ ዜጎች ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ቪፒኤን የተባለውን በተዘዋዋሪ አገልግሎቱን የማግኛ መንገድን መጠቀም ጀምረው ነበር።

    እገዳው የተጣለው የጋቦን ፕሬዝዳንት ብሪስ ኦሊጊ ንጉኤማ ከተመረጡ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ ተቃውሞ ካጋጠመ በኋላ ነበር።

    በወቅቱ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ እና አመቺ ያልሆነ የሥራ ሁኔታን እንደምክንያት በማቅረብ አድማ አድርገው ነበር።

    የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በመንግሥት የተጣለው የማኅበራዊ ሚዲያው እገዳ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ወቅሰው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ንጉዌማ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ነበር ያሸነፉት። ምርጫው የተካሄደው ፕሬዝዳንቱ የመሩት መፈንቅለ መንግሥት ከሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝን ካበቃ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር።

    በወቅቱ ንጉዌማ በነዳጅ እና በደን ሀብት የበለጸገችውን ትንሿ ጋቦንን ለማሻሻል ቃል ገብተው ነበር።

  6. ለምርጫ አንድ ቀን የቀራቸው የእስራኤሉ መሪ ኔታንያሁ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አውድመናል አሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ

    ነገ ማክሰኞ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፣ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የማውደሙ ሥራ 90 በመቶው መጠናቀቁን እና የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ ኔታንያሁን ምረጡ” ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ለሦስት ዓመት ከዘለቀው የቀጣናው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ማክሰኞ የሚካሄደው የእስራኤል ምርጫ እጅግ ተጠባቂ ሆኗል። አርብ ዕለት የወጣ የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳ እንዳመለከተው ከሆነ በአገሪቱ መንግሥት የመሠረተው ጥምረት እና ዋነኛ ተቃዋሚዎችን የያዘው ቡድን አንገት ለአንገት ተናንቀዋል።

    ከግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ ሲሆን፤ በውጭ አገራት የነበሩ 70 ሺህ ገደማ የአገሪቱ ዜጎች ለዚሁ ምርጫ ሲሉ ወደ እስራኤል ገብተዋል።

    ምርጫ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ትናንት እሁድ ለእስራኤሉ ቻናል 14 የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ኔታንያሁ፣ የምርጫ ተቀናቃኞቻቸው የኢራንን ኒውክሌር የማውደምን ሥራ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    "እኛ የሥራውን 90 በመቶ አጠናቅቀናል፤ 10 በመቶ ብቻ ቀርቷል። ይህንን ማን ሊያደርገው ይችላል? አይዘንኮት እና የሙስሊም ወንድማማቾች? በፍጹም፣ ይህንን ማድረግ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ” ብለዋል።

    ከቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋዲ አይዘንኮት ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው የመጨረሻ ቀናት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ጉዳይ በድጋሚ የቅስቀሳቸው ዋነኛ አጀንዳ አድርገውታል።

    ኔታኒያሁ በትናንትናው ዕለትም በቴል አቪቭ ላይ የኒውክሌር ፍንዳታ ሲደርስ የሚያሳይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምሥል በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። ከምሥሉ ጋርም ኢራን ለእስራኤል “የኅልውና ስጋት” መሆኗን የሚገልጽ የአንድ ቀኝ ዘመም እስራኤላዊ የፖለቲካ ተንታኝ ጽሑፍን አያይዘዋል።

    ተፎካካሪያቸው ጋዲ በበኩላቸው፣ ኔታንያሁ የመራጮችን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ከኢራን የሚመነጭን ስጋት መጠቀሚያ እያደረጉ ነው ሲሉ ከስሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢራን ጋር ለተደረገው ጦርነት ራሳቸው ያስቀመጧቸውን ግቦች ማሳካል አለመቻላቸውንም ተናግረዋል።

    በዚህ ተጠባቂ ምርጫ ከኔታንያሁ ጎን የተሰለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም በበኩላቸው በድጋሚ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። አሜሪካ እና እስራኤል ካለፈው ዓመት የካቲት አንስቶ ኢራን ላይ በጋራ ያካሄዷቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎች ያስታወሱት ትራምፕ፣ “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ” እስራኤላውያን መራጮች ለኔታንያሁ ድምፃቸውን ስጡ ሲሉ ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ እርሳቸው እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው እና በተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎች የጋራ ድሎችን እንደተቀዳጁ ገልጸዋል።

    በ2017 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል የኒውክሌር ተቋማት ላይ በፈጸሙት ድብደባ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።