
የፎቶው ባለመብት, US Central Command
ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን “ክፉኛ” እንደበድባታለን ማለታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ጥቃት በመፈጸሙ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ
እርምጃ ወሰደች።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ጦርነቱን ለማቆም የሚያስችል “ስምምነትን ለመቀበል ብዙ
ጊዜ ፈጀች” ካሉ በኋላ ለተከታታይ ሁለት ቀናት “ራስን የመከላከል ጥቃቶችን” መፈጸሙን አስታውቋል።
በምላሹ ኢራን በባሕሬን፣ ኩዌት የሚገኙ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች።
እነዚህ ጦር ሰፈሮች ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ የወሰደችባቸው ናቸው።
ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ የሚያደርጉት መታኮስ በሚያዚያ ወር የተደረሰውን የተኩስ አቁም አደጋ ላይ ጥሎታል።
አሜሪካ የቴህራን የአየር መከላከያዎችን፣ ራዳሮችን እና ሌሎች ተቋማት ላይ ድብደባ ከፈጸመች በኋላ በአገሪቱ ደቡባዊ
ክፍል በሆርሙዝ አቅራቢያ አካባቢ ፍንዳታ ተሰምቷል።
የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ ሁለት የነዳጅ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢራን መገናኛ
ብዙኃን ዘግበዋል።
ስለ ጥቃቱ ወዲያውኑ ማረጋጋጫ የሰጠ አካል የለም።
ይህ የተከሰተው የኢራን መገናኛ ብዙኃን የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለማንኛውም ዓይነት መርከብ ሙሉ በሙሉ ዝግ መሆኑን” ካስታወቁ
በኋላ ነው።
ሴንትኮም ግን “የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እያለፉ ነው” ሲል መግለጫ ሰጥቷል።
በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ከደረሰ እና መስመሩ ሙሉ በሙሉ ዳግም ከተዘጋ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
በእስያ ገበያ ዛሬ ማለዳ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በበርሜል የ2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 95 ዶላር መሸጥ ጀምራል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መካከለኛው ምሥራቅ “ወደ ማይወጣው ቀውስ ውስጥ እየገባ ነው” ሲሉ
አስጠንቅቀው በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ግጭቶች “የተኩስ አቁሙ የተኩሱን መጠን መቀነስ ብቻ ላይ አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስላል” ብለዋል።
“የተኩስ መጠኑን መቀነስ ወደ ሙሉ ጦርነት እንዲሻገር ማድረግ የለብንም። ሁሉም ወገኖች ወደ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መምጣት
አለባቸው። ተጨማሪ ጥቃት አያስፈልግም። ከዚህ በኋላ ምንም ሰበብ አያስፈልግም” ሲሉ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።