ታዋቂዋ ዘፋኝ አሪያና ግራንዴ የአሜሪካ መንግሥት ሙዚቃዋን ለፀረ ስደተኞች ፖሊሲው እንዳይጠቀም ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty
ታዋቂዋ አሜሪካዊት ዘፋኝ አሪያና ግራንዴ ሙዚቃዋ የአሜሪካን የስደተኞች ፖሊሲን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እንዳይውል የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ጠየቀች።
በቲክቶክ ላይ በተጋራው ቪዲዮ ላይ የአሜሪካ የድንበር ጠባቂዎች ሰዎችን እጃቸውን በካቴና እያሰሩ ወደ እስር ቤት ሲወስዷቸው የአሪያና ግራንዴ “ጉድባይ” [ደህና ሁኑ] የሚለው ታዋቂ ዘፈን በማጀቢያነት ጥቅም ላይ ውሏል።
የቪዲዮው ማብራሪያ “ደህና ሁኑ...ፕሬዝዳንት ትራምፕ በታሪክ በደንብ የሚጠበቅ ድንበር ፈጥረዋል” ይላል።
አሪያና ግራንዴ ይህንን ቪዲዮ በተመለከተ "እባካችሁ ሙዚቃዬን ከዚህ ጭካኔ ከተሞላበት፣ ሰብአዊነት ከጎደው ክፋት ጋር አታያይዙት” ስትል ጽፋለች።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አቢጌል ጃክሰን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በሰጠችው ምላሽ “በትክክልም ጭካኔ የሞላበት፣ ሰብአዊነት የጎደለው እና ክፉው ድርጊት ሕገወጥ ስደተኞች ንጹሃን አሜሪካውያንን መጉዳታቸው ወይም መግደላቸው ነው” ብላለች።
ዋይት ሐውስ ቪዲዮውን ያጋራው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ለስደተኞች ተቆጣጣሪ ተቋማት የሚውል 70 ቢሊዮን ዶላር በጀት ካጸደቁ በኋላ ነው።
አሪያና ግራንዴ በቪዲዮው ላይ ቅሬታዋን ካሰማች በኋላ የቪዲዮው ድምጽ እንዳይሰማ ሲደረግ የእሷ አስተያየትም ጠፍቷል።
አሪያና ግራንዴ ሙዚቃቸው ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የፖለቲካ አጀንዳ ማስተዋወቂያነት እንዳይውል ከጠየቁ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመጣው የአርቲስቶች ዝርዝር ውስጥ ስሟ ተካትቷል።
በተመሳሳይ ሙዚቃዋ የስደተኛ ተቆጣጣሪዎችን ሥራ በሚያሳይ ቪዲዮ ላይ ጥቅም ላይ የዋለባት ሌላኛዋ አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ሳብሪና ካርፔንተር “እኔን እና ሙዚቃዎቼን ሰብአዊነት ለሌለው ዓላማችሁ ፈጽሞ አትጠቀሙ” ብላ ጽፋ ነበር።
አባ፣ ሴሊን ዲዮን እና ቢዮንሴ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድጋሚ ለመመረጥ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ ሙዚቃዎቻቸውን እንዳይጠቀሙ ከጠየቁ ድምጻውያን መካከል ይገኙበታል።






















