የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ታጣቂዎች “እጃቸውን እንዲሰጡ” አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በናይጄሪያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች “እጃቸውን እንዲሰጡ ካልሆነ ግን አገሪቷ ባላት ኃይል ሁሉ እንደሚመቱ” ፕሬዝዳንት ቦላ አሕመድ ቲኑቡ አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በአገሪቷ የሚከበረውን ‘የዲሞክራሲ ቀን’ በማስመልከት በብሔራዊ መገኛኛ ብዙኃን ባስተላለፉ መልዕክት ነው።
በመልዕክታቸው በቅርቡ የተፈፀመው የተማሪዎች እገታ የዚህ ዓመቱን በዓል እንዳደበዘዘው ተናግረዋል።
ሆኖም የአገሪቷ ፀጥታ ጉዳይ ከመንግሥት እጅ አለመውጣቱን ገልጸዋል።
"ዲሞክራሲ ያለ ደኅንነት ተጨባጭ አይደለም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ከ50 ሺህ በላይ አዳዲስ የፖሊስ መኮንኖችን፣ ለመከላከያ እና ለፀጥታ 4 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት መመደባቸውን አስታውቀዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ ወታደራዊ ምልመላዎችም እንዲካሄዱ ተወስኗል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጦራቸው ባለፈው ዓመት ብቻ 13 ሺህ "ሽብርተኞችን" መግደሉን እና በታጣቂዎቹ ምክንያት የሚደርስ የንጹኃን ሞትም ከአውሮፓውያኑ 2015 ወዲህ በ81 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።
ከ124 ሺህ በላይ ተዋጊዎች እና ቤተሰቦቻቸው መሣሪያቸውን ማውረዳቸውንም አክለዋል።
ሆኖም ተንታኞች በታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቷ ግዛቶች ነዋሪዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
ወደ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎችም እየተዛመቱ ነው ብለዋል።






















