ኢትዮጵያ አባይ እና ቀይ ባሕርን በተመለከተ አራት አገራት ላወጡት የጋራ መግለጫ ምላሽ ሰጠች

ከአባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዙ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካ ትርክቶች እና በኃይል እርምጃዎች ሊቀየሩ እንደማይችሉ ኢትዮጵያ አስታወቀች።
ኢትዮጵያ ይህን ያለችው ግብፅ እና በአገሪቱ የተሰባሰቡ ሦስት የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በቀይ ባሕር እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የጋራ መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው።
የግብፅ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን መሪዎች የኤል አላሚን ስምምነት ሲሉ በገለጹት መግለጫቸው ላይ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም አንጻር የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑትን ግብፅ እና ሱዳንን የሚጎዳ የተናጠል ድርጊትን ውድቅ አድርገዋል።
በተጨማሪም የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ቁጥጥር በቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኙ አገራት ብቸኛ ኃላፊነት ስር የሚወድቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን የአራቱ አገራት መግለጫ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ስም ግን አልተጠቀሰበትም።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ሁለቱን የውሃ አካላት በሚመለከት የሚደረጉ ውይይቶች አገሪቱን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አሳስባለች።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአራቱን ተቀናቃኝ አገራት ስም እና አገራቱ ያወጡትን የጋራ መግለጫ ሳይጠቅስ ባወጣው አጸፋዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ መነሻ መሆኗን እና ወንዙ ለናይል ወንዝ 85 በመቶውን የውኃ መጠን እንደሚያበረክት አስታውሷል።
በመሆኑም በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም እና አስተዳደር ዙሪያ የሚደረጉ ማናቸውም ውይይቶች “እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች ያገናዘቡ መሆን አለባቸው” ሲል አሳስቧል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋርም መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ ትስስር ያላት መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
የፖለቲካ ድንበሮች በጊዜ ሂደት ቢቀያየሩም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት የጠበቀ ቁርኝት የቀጠለ መሆኑን የጠቀሰው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ አገሪቱ ከባሕር ዳርቻው የምትርቀው በ48 ኪሎ ሜትሮች ብቻ መሆኑን አስገንዝቧል።
በመሆኑም በቀጣናዊ የባሕር ላይ ጉዳዮች እና የደኅንነት መዋቅር ላይ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት “የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅሞች እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ዘላቂ ትስስር ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት” ሲል አቋሙን ገልጿል።
ሚኒስቴሩ፣ እነዚህ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች “በፖለቲካዊ ትርክቶች፣ በማስገደድ እርምጃዎች ወይም በማተራመስ ድርጊቶች ሊቀየሩ አይችሉም” ብሏል።
አክሎም “በተላላኪዎችአማካይነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ወይም የጥቃት ድርጊቶች” መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንደማይቀይሩ እንዲሁም “ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ሕጋዊ ጥቅም፣ ሚና እና ኃላፊነት ሊያሳንሱት እንደማይችሉ” በአጽኦት ገልጿል።
ኢትዮጵያ ሰላማዊ ግንኙነትን፣ የጋራ መከባበርን እና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደምትቀጥል ጠቅሶ፣ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት አንድነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆኗንም አስታውቋል።
ሁሉም የቀጣናው ተዋናዮች የጋራ ፈተናዎችን ከግጭት ይልቅ በውይይት መፍታት እንዳለባቸው አሳስቧል።




