በኢንዶኔዥያ መርከብ ተገልብጦ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 130 የሚሆኑት ደብዛቸው ጠፋ

የፎቶው ባለመብት, ndonesian Navy
በኢንዶኔዥያ ጃቫ ባሕር ላይ አንድ አነስተኛ መርከብ ተገልብጦ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 130 የሚሆኑት ደብዛቸው መጥፋቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
እስካሁን ሌሎች 107 ሰዎችን መታደግ ተችሏል።
መርከቡ ቅዳሜ ዕለት ከሱራባያ ወደ ደቡባዊ ካሊማንታን ከተማ ባንጃርማሲን እየተጓዘ ሳለ ነበር አደጋው የደረሰው።
በአደጋው ሥፍራ መርከቦች እና ሄሊኮፕተር የተሰማሩ ሲሆን 280 የነፍስ አድን ሠራተኞች የሕይወት አድን ጥረት እያደረጉ ነው።
በአካባቢው ያለው መጥፎ የአየር ሁኔታ የጠፉ ሰዎችን የመፈለግ ጥረቱን አዳጋች እንዳደረገው ተገልጿል።
በጃቫ ባሕር ላይ ያሉ ሁሉም ጀልባዎች የሆነ አጠራጣሪ ምልክት ካዩ እንዲያሳውቁ ተነግሯቸዋል።
መርከቡ 213 መንገደኞችን እና 30 ሠራተኞችን አሳፍሮ እንደነበር ተነግሯል።
እንደ የባሕር ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ከሆነ መርከቡ ከሱርባያ የተነሳው ቅዳሜ ጠዋት 4፡33 ሰዓት ላይ ሲሆን በባንጃርማሲን እሁድ 8፡00 ሰዓት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
በኢንዶኔዥያ ከ17 ሺህ በላይ ደሴቶች ያሉ ሲሆን መርከቦች የተለመዱ የመጓጓዣ መንገዶች ናቸው።
የባሕር ትራንስፖርት አደጋም ያልተለመደ አይደለም። የመንግሥት መረጃ እንደሚያሳየው ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2026 ባሉት ዓመታት 111 የመርከብ አደጋዎች አጋጥመዋል።
ሐምሌ ወር ላይ በምዕራባዊ ፖላሲ ደሴት አንድ መርከብ ሰጥማ 58 ሰዎች ከአደጋው ሲተርፉ፣ ሦስት ሰዎች ሞተዋል፤ ሌሎች 14 ሰዎች ደግሞ እስካሁን የገቡበት አልታወቀም።
ባለፈው ወርም አንድ መርከብ በማዱራ ደሴት በእሳት ተያይዞ አምስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Donny Muslim / BBC

