የእስራኤል ፖሊስ በዌስት ባንክ በዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አዋለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ጋዜጠኞች እና በአውሮፓ ዲፕሎማቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በዌስት ባንክ ከሚኖሩ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች መካከል ናቸው።
ስማቸው ያልተገለጸው በተለያየ አካባቢ የተያዙት ግለሰቦች በአመጽ፣ የተከለከለ ወታደራዊ ቀጠናን በመጣስ እና በሕገ ወጥ ግንባታ ተጠርጥረዋል።
አርብ ዕለት ጭምብል የለበሱ የእስራኤል ሰፋሪዎች ሄይዲ ሌቪን የተባለች የዋሽንግተን ፖስት የፎቶ ጋዜጠኛ ደብደው ከባድ ጉዳት እንዳደረሱባት ተገልጿል።
በዕለቱ ጋዜጠኛዋ አቡ ፋላህ በተሰኘ የፍልስጤም መንደር ውስጥ የወይራ ምርት ሲሰበሰብ የሚያሳይ ዘገባ እየሠራች ነበር።
በማግሥቱ ደግሞ ከቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሄዱ ዲፕሎማቶች ጭምብል ባጠለቁ ሰፋሪዎች ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቢ የተጠርጣሪዎቹን መታሰር አድንቀዋል።
አምባሳደሩ በኤክስ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት “[ጋዜጠኛ] ሄይዲ ሌቪን ላይ ከፍተኛ ጥቃት እና ድብደባ የፈጸሙትን ለማግኘት እንዲሁም ለመቅጣት አዎንታዊ እርምጃ ነው” ብለዋል።
በዌስት ባንክ በሚገኙ የእስራኤል ሰፋሪዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በዚህ ዓመት ከምንጊዜውም በላይ እንደጨመሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ለፍልስጤማውያን የዕለት ተዕለት ኑሮ ወሳኝ የሆነው የወይራ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት በተለይ በዚህ ዓመት ጥቃቱ ጨምሯል።
የእስራኤል የሰብአዊ መብት ቡድን “የሽዲን” እሑድ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት 20 ቀናት ብቻ በቀጥታ ከወይራ ምርት መሰብሰብ ጋር የተያያዙ 269 የአመጽ ድርጊቶችን መዝግቧል።
ከእነዚህ ውስጥ 98ቱ የወይራ ምርት መሰብሰብ ሥራ ላይ የነበሩ ፍልስጤማውያን ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ምርቶቻቸውን ማውደም እና መስረቅ እንደሚገኝበት ገልጿል።








