በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፍልስጤማውያን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሁለት ታጣቂዎች በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ በከፈቱት ተኩስ ጥቃት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።
ተጨማሪ ሦስት እስራኤላውያንን አቁስለዋል የተባሉት ታጣቂዎች እንደተገደሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ተኩስ የተከፈተው የኬብሮን ከተማ መግቢያ ላይ በሚገኝ ወታደራዊ የፍተሻ ኬላ ላይ ነው።
ይህንን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ የአገሪቱ ጦሩ ከዛሬ አርብ ጀምሮ ሙሉ ዌስት ባንክ ላይ ሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ለመጣል እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው። “ፅንፈኛ አይሁዳውን ሰፋሪዎች” ዓመታዊውን የወይራ ምርት ስብሰባ በሚያካሂዱ ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ነበር። የእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድም አራት ቀናት ቀርተውታል።
ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ላይ በእስራኤል ወታደሮች እና በታጣቂዎቹ መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር አሳይቷል።
የእስራኤል ጦር፣ በታጣቂዎቹ ተሽከርካሪ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥይት ማግኘቱን አስታውቋል።
ታጣቂዎቹ በአቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም አስበው እንደነበር፣ ነገር ግን የፍተሻ ኬላ ሲያጋጥማቸው እዚያው ተኩስ ለመክፈት ወስነዋል ተብሎ እንደሚታመን እስራኤል ጦር ገልጿል።
ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ የደኅነነት ካሜራ ቪዲዮ ላይ ደግሞ ሁለት ታጣቂዎች ሽጉጥ እና ጠመንጃ የሚመስሉ መሣሪያዎችን ይዘው ከመኪና ሲወርዱ እንዲሁም ኬላው ላይ በነበሩ ወታደሮች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ እና የአጸፋ ምላሽ ሲሰጣቸው ታይቷል።
ዛሬ ከሰዓት ላይ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ቦታ የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ መንግሥታቸው በዌስት ባንክ “ከፍተኛ እርምጃ” ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀኝ አክራሪው የሆነው ጥምር መንግሥት አጋራቸው የሆኑት ቤዛሌል ስሞትሪች “እንደ ጋዛ ወይም ሊባኖስ አይነት” ዘመቻ ዌስት ባንክ ውስጥ እንዲጀመር ጠይቀዋል።
የቀኝ አክራሪው የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ደግሞ እስራኤል የፍልስጤም አስተዳደርን እንድታፈርስ ጥሪ አቅርበዋል።




















