ጣሊያን የተገልጋዮችን ፎቶ ያለ ፈቃዳቸው ተጠቅሟል ስትል በሜታ ላይ የ887 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጣለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጣሊያን የአንድሮይድ ስልክ ተገልጋዮችን ፎቶዎች ያለ ፈቃዳቸው ተጠቅሟል ስትል በግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ላይ የ887 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጣለች።

የአገሪቱ የመረጃ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ሜታ በፌስቡክ መተግበሪያው ላይ ባለው ሞዴል አማካኝነት የግለሰቦችን ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ማግኘት እንደሚችል 20 ሚሊዮን ለሚሆኑ የዘመናዊ ስልክ ተጠቃሚዎች በተገቢው ሁኔታ አላሳወቀም ሲል ከስሷል።

ባለሥልጣኑ ሜታ ይህንን በፌስቡክ መተግበሪያው ላይ ያለ ሞዴል 'በዲፎልት' እንዳይሰራ ለማድረግ እና ለብቻ የተጠቃሚዎችን ፈቃድ እንዲጠይቅ የሚያደርግ ዘዴ እንዲያስቀምጥ የ60 ቀናት ቀነ ገደብ ሰጥቷል።

ቅጣቱ የጣሊያን ባለሥልጣናት በግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ላይ ከጣሉት ትላልቅ ቅጣቶች መካከል አንዱ ነው።

የሜታ ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ለማለት ማቀዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክሱ ተጠቃሚዎች ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን ከፎቶ ማኅደራቸው (ጋለሪ) በመውሰድ እንዲያጋሩት አስተያየት ከሚሰጠው የፌስቡክ ሞዴል (ፊቸር) ጋር የሚገናኝ ነው።

ፌስቡክ በመተግበሪያው አማካኝነት የተጠቃሚዎችን ፎቶዎች ከፎቶ ማኅደራቸው ለመውሰድ ቢጠይቅም ሂደቱን ለመቀጠል ለተጠቃሚዎች በግልጽ አላሳወቀም ብለዋል ተቆጣጣሪዎቹ።

ይህም ፌስቡክ በተጠቃሚዎች የፎቶ ማኅደር ውስጥ ያሉ ፎቶዎች ላይ በመመስረት ሊያጋሩት የሚችሉትን ልጥፍ ማመልከቱን የጣሊያን የመረጃ ተቆጣጣሪዎች ገልጸዋል።

በመሆኑም ባለሥልጣኑ በዚህ የተጎዱ በርካታ ተጠቃሚዎችን፣ አሁንም መተግበሪያውን ባላደሱ (አፕዴት ባላደረጉ) ላይ ችግሩ የቀጠለ መሆኑን እንዲሁም ለመተግበሪያው ፈቃዳቸውን የሰጡትን ከግምት በማስገባት ቅጣቱን መጣሉን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ሜታ "ትብብር አለማሳየቱን" ባለሥልጣኑ ጠቅሷል።

ሜታ "ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ እውነታውን በገመገመበት፣ ሕጉን በተገበረበት መንገድ እና የቅጣቱ ተመጣጣኝነት ላይ እንደማይስማማ" ለቢቢሲ ገልጿል።

አክሎም "ይህ ተጠቃሚዎች ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በፌስቡክ ለማጋራት የሚረዳ ቀጥተኛ የሆነ ሞዴል ነው። ከመስራቱ በፊት ሰዎች በሚጠቀሙበት መሣሪያ ላይ ፈቃድ መስጠት አለባቸው። ካልፈለጉም በማንኛውም ጊዜ ሴቲንግ ላይ ገብተው መለወጥ ወይም ፈቃዳቸውን አለመስጠት ይችላሉ" ሲል አስረድቷል።

ኢንስታግራምን እና ዋትስአፕን ጭምር የሚያስተዳድረው ሜታ ባለፈው ወርም ከቢዝነስ አሰራሩ ጋር በተያያዘ በታሪኩ ከፍተኛው ቅጣት ተጥሎበታል።

በኒው ሜክሲኮ የአሜሪካ ዳኛ ኩባንያው የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃዎች የሚጠብቅበትን መንገድ በተመለከተ ለዓመታት ለሕዝብ በመዋሸቱ የ25 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።