የኢራን መንግሥትን የኢንተርኔት እገዳ ለማለፍ የስታርሊንክ ቴክኖሎጂን ወደ አገሪቱ የሚያስገባው ድብቅ መረብ

"አንድ እንኳ ተጨማሪ ሰው ኢንተርኔት ማግኘት ቢችል ተሳክቷል ብዬ አስባለሁ፤ ደግሞም ዋጋ አለው" ይላል ሳሃንድ።
ኢራናዊው ግለሰብ ከአገሪቱ ውጪ በሆነ ስፍራ ከቢቢሲ ጋር በሚነጋገርበት ሰዓት ጭንቀቱ ፊቱ ላይ ይታይ ነበር። ሳሃንድ ኢራን ውስጥ ሕገ ወጥ የሆነውን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን በስውር አገር ውስጥ የሚያስገባ ድብቅ መረብ አካል ነው።
በዚህ ዘገባ ስሙ የተቀየረው ሳሃንድ፤ በአገር ውስጥ ባሉት የቤተሰቡ አባላት እና ሌሎች የሚያውቃቸው ሰዎች ላይ ጉዳት ይደርሳል በሚል ይሰጋል። "በኢራን አገዛዝ ከታወቅሁ ኢራን ውስጥ የማገኛቸውን ሰዎች ዋጋ ሊያስከፍሏቸው ይችላሉ" ይላል።
የኢራን መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት አገር አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጦች ረጅሙ የሆነውን እገዳ ተግባራዊ በማድረጉ አገሪቱ ላለፉት ሁለት ወራት የዲጂታል ጨለማ ውጧታል።
የአሁኑ የኢንተርኔት መቋረጥ የጀመረው አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ነው። ኢንተርኔቱ የተቋረጠው ለአንድ ወር ከዘለቀ እገዳ በኋላ በከፊል በተመለሰ በወሩ ነው።
የኢራን መንግሥት አገር አቀፍ ደረጃ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማፈን እርምጃ በወሰደበት ወቅት ጥር ላይ ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር። በዚህ የመንግሥት እርምጃ ከ6,500 በላይ ተቃዋሚዎች እንደተገደሉ እና 53,000 እንደታሰሩ አሜሪካ የሚገኘው የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል 'ሂራና' ዘግቧል።
የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው በጦርነቱ ወቅት ኢንተርኔት የተዘጋው ከደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን በማድረግ ክትትል፣ ስለላ እና የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል እንዳሰቡ ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ሳሃንድ ወደ ኢራን የሚልካቸው ጠፍጣፋዎቹ ነጭ የስታርሊንክ ዲቫይሶች እገዳውን ማለፍ የሚያስችሉ አስተማማኝ መሣሪያዎች ናቸው። ዲቫይሶቹ ባለቤትነቴ የባለሀብቱ ኤሎን መስክ በሆነው ስፔስ ኤክስ ኩባንያ ወደ ጠፈር ከተላኩ በርካታ ሳተላይቶች ጋር በመገናኘት ተጠቃሚዎች በኢራን መንግሥት ከፍተና ቁጥጥር ከሚደረግበት የቤት ውስጥ ኢንተርኔት ውጪ በሆነ መንገድ ኢንተርኔት እንዲያገኙ ያስችላል።
ሳሃንድ እንደሚገልጸው አንዱን መሣሪያ በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እርሱ እና ጓዶቹ መሣሪያዎቹን ገዝተው ወደ ኢራን የሚያስገቡት "በድንበር በኩል" ነው። ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም "እጅግ ውስብስብ ኦፕሬሽን" እንደሆነ ጠቅሷል።
ከጥር አንስቶ በርካታ የስታርሊንክ ዲቫይሶችን መላኩን የሚናገረው ሳሃንድ፤ "ተጨማሪ መሣሪያዎችን በድብቅ ለማስገባት ሌሎች መንገዶችን እየፈለግን ነው" ብሏል።
'ዊትነስ' የተባለው የተባለው የሰብአዊ መብቶች ድርጅት እስከ ጥር ድረሰ ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢራን ውስጥ ቢያንስ 50,000 የሚሆኑ የስታርሊንክ ዲቫይሶች እንደሚገኙ ይገመታል። ከዚያ በኋላ ባሉት ወራት ይህ ቁጥር ጨምሮ ሊሆን እንደሚችል አክቲቪስቶች ይናገራሉ።
ቢቢሲ፤ ስታርሊንክ ኢራን ውስጥ ያሉትን ተጠቃሚዎች በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ለስፔስ ኤክስ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።
የኢራን መንግሥት፤ የስታርሊንክ መሣሪያዎችን መጠቀም፣ መግዛት ወይም መሸጥ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስር እንደሚያስቀጣ የሚደነግግ ሕግ በአውሮፓውያኑ 2025 አጽድቋል። ከ10 በላይ ዲቫይሶችን ሲያሰራጩ ወይም አገር ውስጥ አስገብተው የተገኙ ሰዎች ላይ ደግሞ እስሩ እስከ 10 ዓመት ይደርሳል።
የስታርሊንክ መሣሪያዎችን ሲገዙ እና እና ሲሸጡ የተያዙ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ባለፈው ወር "የሳተላይት ኢንተርኔት መሣሪያዎችን ወደ አገር ማስገባታቸው" ምክንያት አራት ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የውጭ ዜጎች ናቸው።
ከታሰሩት ሰዎች መካከል የተወሰኑት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት እና ለጠላት መረጃ ማቀበል የሚሉ ክሶችም ቀርበውባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images/LightRocket via Getty Images
ይሁን እንጂ 'ናስኔት' ተብሎ የሚጠራውን የቴሌግራም ቻናል ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የኢንተርኔት መገናኛ መሣሪያዎቹ ኢራን ውስጥ ለገበያ መቅረብ ቀጥለዋል። ከኢራን ውጪ ሆኖ 'ናስኔት' ውስጥ የሰሳተፍ አንድ በጎ ፈቃደኛ ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በግምት 5,000 ገደባ የስታርሊንክ ዲቫይሶች መሸጣቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ኢራን መረጃን የመቆጣጠር የረጅም ጊዜ ታሪክ አላት። የአገሪቱ መንግሥት በራሱ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ፀረ አሜሪካ እና ፀረ እስራኤል ትርክቶችን ያስፋፋል። ተቃዋሚዎች ላይ የሚወሰዱ አፋኝ እርምጃች እንዳይዘገቡም ያግዳል።
ጥር ላይ በተካሄደው ተቃውሞ ወቅት ግን ኢንተርኔት ተዘግቶ እንኳ ዘገባዎች እንዲሁም ከፍርድ ውጨ የሆኑ ግድያዎችን፣ እስሮችን እና ድብደባዎችን የሚያሳዩ የቪዲዮ ማስረጃዎች ወጥተዋል። የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እንደሚናገሩት አብዛኛው መረጃ የወጣው በስታርሊንክ አማካኝነት ማኅበራዊ ሚዲያ በሚጠቀሙ ሰዎች እንደሆነ ይታመናል።
በአሁኑ ሰዓት ኢራን ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚገኘው የተለያዩ "ደረጃዎች" ባሉት ስርዓት ነው። ሁሉም ኢራናውያን እንደ ባንክ መጠቀም፣ የታክሲ አገልግሎት ማግኘት እንዲሁም የምግብ 'ዴሊቨሪ" ያሉ አገልግሎቶችን መጠቀም የሚያስችላቸው የአገር ውስጥ ኢንተርኔት አገልግሎት ያገኛሉ። ይህ ኢንተርኔት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ ነው።
ኢንተርኔት ከመቋረጡ በፊት ኢራናውያን ከዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መድረኮችን መጠቀም ይችሉ ነበር። ነገር ግን እንደ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም፣ ዩቲዩብ እና ዋትስአፕ ያሉ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾች ታግደዋል። በአገር ውስጥ ኔትዎርክን አማካኝነት እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾች ለመጠቀም የሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛ ነው።
በርካታ ኢራናውያን ይህንን እገዳ ለማለፍ ሲሉ ያሉበትን ቦታ ቀይሮ ከድረ ገጾቹ የሚያገናኛቸውን 'ቪፒኤን' ይጠቀማሉ። 'ቪፒኤን'ንም ግን ክፍያ ስላለው ወጪያቸው ከፍ ማለቱ አልቀረም።
አሁን ኢንተርኔት ከተዘጋ በኋላ "ነጭ ሲም ካርድ" በሚባለው መንገድ ያልተቋረጠ የኤንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙት የተመረጡ ጥቂት ባለሥልጣናት እና እንደ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤሎን መስክ ስታርሊንክ ኢራን ውስጥ እንዲሰራ እንደሚያደርግ ያስታወቀው በአውሮፓውያኑ 2022 የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ኢንተርኔት ሲዘጋ ነበር። በወቅቱ ተቃውሞ ያስነሳው ማሻ አሚኒ የተባለች ኢራናዊ በመንግሥት እጅ ያለች መሞቷ ነበር።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ በተለይም ኢንተርኔት በሚዘጋባቸው ወቅቶች የስታርሊንክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ጨምሯል።
አሁን የኢራን ባለሥልጣናት የስታርሊንክ ዲቫይሶችን ለመያዝ የሚያደርጉት ክትትል መጥበቁን ተከትሎ ሳሃን እና ጓዶቹ የስታርሊንክ ተጠቃሚዎች ማንነታቸው ለመደበቅ ቪፒኤን እንዲጠቀሙ እየመከሩ ነው። በአገሪቱ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ግን በርካታ ኢራናውያን ይህንን ለማድረግ የሚያችል አቅም የላቸውም።
ሳሃንድ እንደሚናገረው እርሱ የሚሳተፍበት ስታርሊንክ ዲቫይሶችን የመግዛት እና በድብቅ የማስገባት ሥራ የሚደገፈው ውጭ አገር ባሉ ኢራናውያን ነው። ለዚህ ተግባራቸው ከየትኛውም አገር መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንደማይቀበሉም ይናገራል።
የስታርሊንክ ዲቫይሶቹ የሚላኩት ኢንተርኔቱን ተጠቅመው በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጃ ያሰራጫሉ ተብለው ለሚታመኑ ሰዎች ነው።
ሳሃንድ፤ "ሰዎች በአገር ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ነገር እንዳለ ለማጋራት ኢንተርኔት ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ መሣሪያዎች በእርግጥም ለውጥ ለማምጣት በሚፈልጉ ሰዎች እጅ መግባት አለባቸው ብለን እናምናለን" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የዲጂታል መብቶች ተሟጋች ቡድን ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ቢያንስ 100 የሚሆኑ ሰዎች የስታርሊንክ ዲቫይሶችን ይዘው በመገኘታቸው ታስረዋል።
ሳሃንድም በበኩሉ መሣሪያውን በመጠቀማቸው ወይም በመያዛቸው የታሰሩ ሰዎችን እንደሚያውቅ ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ግን እርሱ በሚሳተፍበት ኦፕሬሽን ዲቫይሱን እንዳላገኙ ይናገራል።
ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች አንዲት አሜሪካ-ኢራናዊትም አገሪቱ ውስጥ የስታርሊንክ ሲቫይስ ይዞ የተገኘ አንድ የቤተሰቧ አባል በስለላ ወንጀል ተከስሶ መታሰሩን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ቢቢሲ፤ ኢራን ውስጥ ኢንተርኔት የሚፈቀደው ለምን ለጥቂት ሰዎች ብቻ እንደሆነ እንዲሁም እና ስታርሊንክን የሚጠቀሙ ሰዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ለምን ከፍተኛ እንደሆነ በለንደን የሚገኘውን የኢራን ኤምባሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
የኢራን መንግሥት ኢንተርኔት መዘጋቱ የተወሰኑ ንግዶችን ክፉኛ እንደጎዳ አምኗል። አንድ ሚኒስትር ኢንተርኔት በመዘጋቱ የኢራን ኢኮኖሚ በየቀኑ ቢያንስ 35 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያጣ ጥር ላይ ተናግረዋል።
በቅርቡ ይፋ የተደረገው "ኢንተርኔት ፕሮ" የተሰኘው አገልግሎት የተመረጡ የንግድ አይነቶች በተወሰነ መከኩ ወደ ዓለም አቀፍ ኢንተርኔት እንዲገናኙ ያስችላል። ኢራን ውስጥ ላለ አንድ ኩባንያው የሚሰራ አንድ ግለሰብ በዚህ አሰራር ኢንተርኔት ማግኘቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
የመንግሥት ቃል አቀባይዋ ፋጤሜህ ሞሃጄራኒ እንደሚናገሩት የዚህ አገልግሎት ዓላማ "በቀውሱ ወቅት የንግድ ግንኙነቶች እንዳይቋረጡ ማድረግ" ነው። የአገሪቱ መንግሥት "የመረጃ ግንኙነት ኢፍትሐዊነትን ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወም" የሚናገሩት ቃል አቀባይዋ፤ ሁኔታዎች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ "የኢንተርኔት ሁኔታውም ይቀየራል" ብለዋል።
እሁድ ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም. ከሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስቀድሞ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት 'አክሰስ ናው' የተባለው የዲጂታል መብቶች ተሟጋች ቡድን ቀጠናዊ ዳይሬክተር ማርዋ ፋታፍታ እንደሚገልጹት "ግንኙነትን ሙሉ በሙሉ የማቋረጥ እርምጃ ምንም አይነት ምክንያት ሊቀርብ የማይችልበት ግልጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት" ነው።
'አብዶራህማን ቦሩማንድ ሴንተር ፎር ሂውማን ራይትስ' የተሰኘው የሰብአዊ መብቶች ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሮያ ቦሩማንድ እንደሚናገሩት፤ ኢራን ውስጥ ያለው የመረጃ ክፍተት "ተቃዋሚዎች እንደ አመጸኞች ወይም እንደ የውጭ አገር ወኪሎች የሚፈረጁበት የምንግሥት መገናኛ ብዙኃን ትርክት" ብቻ እንዲያሰራጭ ያደርጋል።
የኢንተርኔት መዘጋት "የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ተቃዋሚዎች ጨምሮ [የመንግሥት አፈና] ተጎጂዎች እና መረጃ ያላቸው ምንጮች እንዲታፈኑ ያደርጋል" ሲሉ ተጽዕኖውን ያስረዳሉ።
የስታርሊንክ ዲቫይሶችን ወደ ኢራን የሚያስገባው ሳሃንድም እንዲነሳሳ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ይኸው መሆኑን ይገልጻል።
"የኢራን አገዛዝ ኢንተርኔት በሚዘጋበት ወቅት መግደል እንደሚችል አሳይቷል። ኢራናውያን በአገር ውስጥ ያለውን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ኢንተርኔት ማግኘታቸው እጅግ ወሳኝ ነው" ይላል።
የስታርሊንክ ዲቫይሶችን ወደ ኢራን ለማስገባት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች "ሊደርስባቸው ለስሚችለው አደጋ እንደሚያውቁ" የሚገልጸው ሳሃንድ፤ ቢሆንም ግን "በሆነ መንገድ ጣልቃ መግባት እና ማገዝ እንዳለብን ይሰማናል" ብሏል።














