ሁለት የቻይና የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሮች ሞት ተፈረደባቸው

ሊ ሻንግፉ እአአ ከመጋቢት 2023 ጀምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሊ ሻንግፉ እአአ ከመጋቢት 2023 ጀምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሁለት የቀድሞ የቻይና መከላከያ ሚኒስትሮች በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በእግድ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ሐሙስ ዕለት የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዌይ ፌንጌ እና ሊ ሻንግፉ ለሁለት ዓመት በሚቆይ እግድ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸዋል።

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የሞት ፍርዱ ከሁለት ዓመት በኋላ ያለምንም ዓይነት የቅጣት ማቅለያ ወይም ይቅርታ ወደ እድሜ ልክ እንደሚቀየር ዢንዋ ዘግቧል።

ሁለቱም የቀድሞ ባለሥልጣናት በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የግል ሃብታቸው በሙሉ እንዲወረስ ተደርጓል።

ውሳኔው የመጣው በአገሪቱ በቅርቡ በተደረገ የጸረ ሙስና ዘመቻ በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ነው።

ዌይ እአአ ከ2018 እስከ 2013 ድረስ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ካገለገሉ በኋላ እአአ በ2023 መጋቢት ወር ላይ በሊ ተተክተዋል።

ሊ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ለአጭር ጊዜ ነው።

ለሁለት ወር ከሕዝብ ዕይታ ተሰውረው ከቆዩ በኋላ እአአ በጥቅምት ወር 2023 ከሥልጣን ተነስተዋል።

በየካቲት ወር የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ባልተለመደ መልኩ በወታደራዊ ባለሥልጣናቱ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ጠቅሰው ሌላኛው ጄነራል ዣንግ ዩዢያ መነሳትን ተናግረዋል።

ዢ በንግግራቸው ላይ ጦሩ "ሙስናን በመዋጋት ረገድ አብዮት እያካሄደ ነው" ብለው ነበር።

ፕሬዚዳንት ዢ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ በርካታ የጸረ ሙስና እርምጃዎች የወሰዱ ሲሆን ተቺዎቻቸው ግን የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማስወገድ እየተጠቀሙበት ነው በማለት ይተቿቸዋል።