ፈረንሳይ የእስራኤል ፋይናንስ ሚኒስትር ወደ አገሯ እንዳይገቡ አገደች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ ማክሰኞ ዕለት ቀኝ አክራሪው የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳ ጋዛን “ዳግም ቅኝ የመግዛት” አጀንዳን ያራምዳሉ ስትል ኮነነች።
የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማዕቀቡ የተጣለው ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር መሆኑን ገልጸው በፍልስጤማውያን ሰፋሪዎች ላይ በሚደርስ ጫና የተነሳ እገዳው መጣሉን ገልጸዋል።
ፈረንሳይ ማዕቀቡን የጣለችው ከብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ኖርዌይ እና ኒው ዚላንድ ጋር በመተባባር ነው።
“የሰፈራ እንቅስቃሴዎችን እና በዌስት ባንክ ግጭትን በማቀጣጠል ረገድ ተጠያቂ የሚሆኑ” አካላት ላይ ማዕቀቡ መጣሉን የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ሚኒስትሩ፣ ስሞትሪች “ዌስት ባንክን ወደ እስራኤል መጠቅለልን በይፋ ይደግፋሉ፣ በዌስት ባንክ ተጨማሪ ሰፈራዎች እንዲካሄዱ በይፋ ይንቀሳቀሳሉ” ሲሉ ኮንነዋቸዋል።
አክለውም “ጋዛን ዳግም ቅኝ መግዛት፣ የፍልስጤም ባለሥልጣን ኢኮኖሚያዊ ድቀት እንዲገጥመው፣ እንዲሁም በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ጎጂ ተግባራትን “ በመፈጸም ከስሰዋቸዋል።
ስሞትሪች ወደ ፈረንሳይ እንዳይገቡ ከተከለከሉ የእስራኤል ባለሥልጣናት መካከል ሁለተኛው ናቸው።
ከአዚህ ቀደም የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ግቪር ወደ ፈረንሳይ እንዳይገቡ ታግደዋል።
ፈረንሳይ አራት የሰፋሪዎች ድርጅት መሪዎችን እና 21 አመጸኛ ሰፋሪዎችን ላይ እገዳ ትላለች።




















