ቀጥታ, ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁም ካልተጣሰ በስተቀር ጥቃት እንደማይሰነዝሩ አስታወቁ

ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል። ባለፈው ሚያዝያ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጭት ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት ጥቃት መሰንዘር እንደሚያቆሙ ይፋ አድርገዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ የጦር ሄሊኮፕተር በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ተከሰከሰ

    የአሜሪካ ሄሊኮፕተር በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ መከስከሱን፤ ሆኖም አብራሪዎቹ መትረፋቸውን ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ አብራሪዎቹ ደኅና ናቸው፤ በጥሩ ሁኔታም ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።

    ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ሄሊኮፕተሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የተከሰከሰው ሰኞ ሲሆን አብራሪዎቹን መታደግ ተችሏል።

    የአደጋው ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።

    ሆኖም ትራምፕ ክስተቱን በተመለከተ ዛሬ ሪፖርት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

    በተጨማሪም ፕሬዚደንቱ ከኢራን ጋር እየተካሄደ ያለው የሰላም ስምምነት “የመጨረሻው ደረጃ” ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

    ቀደም ብሎ በተባበሩት መንግሥታት የኢራኑ አምባሳደር የሆኑት አሚር ሳኢድ ኢራቫኒ በስምምነት ለማጠናቀቅ ከአሜሪካ ጋር እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች መቀጠላቸውን ተናግረው ነበር።

  2. አሜሪካ ኢራንን በተመለከተ ከእስራኤል የተለየ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ፕሬዚደንቷ ተናገሩ

    አሜሪካ እና እስራኤል የጋራ ፍላጎት ቢኖራቸውም ዋሽንግተን ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት ዶናልድ ትራምፕ ለአገራቸው ጥሩ ይሆናል ባሉት ሃሳብ እንደሚመራ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚደንት ጄዲ ቫንስ ሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ተናገሩ።

    “እስራኤል እና አሜሪካ ብዙ የጋራ ፍላጎት አላቸው” ያሉት ምክትል ፕሬዚደንቱ፤ ነገር ግን “ፍላጎቶቻችን የሚለያዩበት ሁኔታዎችም አሉ” ብለዋል።

    ኢራንን በተመለከተ አሜሪካ ያላት ፖሊሲ ዋነኛ ግብ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ማረጋገጥ እንደሆነም ቫንስ አስታውሰዋል።

    ምክትል ፕሬዚደንቱ “ ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ አስፈላጊ የሆነ ሁኔታን ፈጥረናል ብለው ፕሬዚደንቱ ያምናሉ፤ ትክክል ናቸው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የኢራን ኒውክሌርን ጉዳይ በተመለከተ የረዥም ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንችላለን” ብለዋል።

    “አሁን እስራኤል ይህንን ልትወደው ወይም ላትወደው ትችላለች፤ ሆኖም በመሠረታዊነት ይህ የአሜሪካ ፍላጎት እንደሆነ እናስባለን”

    ምክትል ፕሬዚደንቱ ጄዲ ቫንስ ጨምረውም ዋሽንግተን ይህንን ግቧን ለማሳካት ሥራዋን ትቀጥላለች፤ ምክንያቱም የአሜሪካው ፕሬዚደንት የተመረጡት ይህንን ለማሳካት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

  3. አሜሪካ እና ኢራን ለስምምነት “የመጨረሻው ጥረት” ላይ እንደሆኑ ትራምፕ ተናገሩ

    አሜሪካ እና ኢራን የስምምነት “የመጨረሻው ጥረት” ላይ እንደሆኑ እና ስምምነቱ “በማንኛውም መንገድ፣ ቅርጽ ወይም ሁኔታ የኒውክሌር መሣሪያን እንደማይፈቅድ” ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ካደረጉ በኋላ በነበሩ የተለያዩ የግጭቱ ምዕራፎች ወቅት ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸውን የሚጠቁም አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።

    በጄኤፍኬ አውሮፕላን ማረፊያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ “በጣም ድንቅ ይሆናል” ብለዋል።

    ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንደማይኖራት በድጋሚ ያስረገጡት ትራምፕ፤ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ “በአፋጣኝ እንደሚከፈት” ጠቁመዋል።

    “በሁለት ወይም በሦስት ቀናት ውስጥ” የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት እንደሚችልም ተናግረዋል።

    ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው ሌላቸው ላይ ጥቃት ማድረስ ለማቆም መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

    ትራምፕ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ካነጋገሩ በኋላ ኢራን ላይ ጥቃት ማድረስ ለማቆም መስማማታቸውን ተናግረዋል።

    “ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ገደማ አይተነኳኮሱም” ሲሉም አክለዋል።

  4. ኢራን እና እስራኤል የተኩስ አቁም ካልተጣሰ በስተቀር ጥቃት እንደማይሰናዘሩ አስታወቁ

    ኢራን እና እስራኤል አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል።

    ባለፈው ሚያዝያ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጭት ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት ጥቃት መሰንዘር እንደሚያቆሙ ይፋ አድርገዋል።

    ሆኖም ግን የተኩስ አቁም የሚጣስ ከሆነ ጥቃት ማድረስ እንደሚጀምሩ ኢራንም እስራኤልም አስጠንቅቀዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው “ለአሁኑ” ጥቃት ከመሰንዘር እንደምትቆጠብ ጠቅሰው፤ ከኢራን እና ሄዝቦላህ ጋር የሚደረገው ትግል ግን “አላከተመም” ብለዋል።

    የኢራን ጦርም ለእስራኤል “የሚያም የአጸፋ ምላሽ” ከሰጠ በኋላ ጥቃት ማድረስ ማቆሙን አስታውቋል።

    ነገር ግን እስራኤል ጥቃት የምታደርስ ከሆነ “የከፋ እርምጃ” እንደሚወስድ ጦሩ አክሏል።

    እስራኤል በቤሩት ላይ ጥቃት በማድረሷ ኢራን እሑድ ዕለት እስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች። እስራኤልም በምላሹ ትናንት ሰኞ የኢራን ወታደራዊ መቀመጫዎች ላይ ጥቃት አድርሳለች።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር “ከትዕዛዛቸው እንዳልወጡ” ተናግረዋል።

  5. የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢራን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለጊዜው ማቆማቸውን አስታወቁ

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጥቃት “ለአሁን” መግታታቸውን ባደረጉት ንግግር አስታወቁ።

    በቴሌቪዥን በተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የእስራኤል ሠራዊት በወሰዳቸው እርምጃዎች ኢራን እና ሄዝቦላህ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከማቸውን አመልክተዋል።

    ኢራን እሁድ ሌሊት በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን የሚሳዔል ጥቃት ተከትሎ በአጸፋው የቴህራንን ወታደራዊ ዒላማዎች መምታቷ ተዘግቧል።

    ይህ የእስራኤል ጥቃት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጠያቂነት እንደሚቆም ከተነገረ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረድጉት ንግግር ላይ ጥቃታቸውን ለጊዜው እንዲቆም ማድረጋቸውን ነገር ግን ውጊያው ገና አለማብቃቱን ገልጸዋል።

    ለኢራን ጥቃት ምላሽ በመሰጠቱ "አሁን ተኩሱ ተገትቷል” ሲሉ ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

    ነገር ግን “ኢራን በድጋሚ ስህተት በመፈጸም ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ በከፍተኛ ኃይል ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እስራኤል እራሷን ለመከላከል ሙሉ መብት ያላት ሲሆን፣ ይህንንም አስፈላጊ አስከሆነ ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንጠቀምበታለን” ብለዋል።

    ኔታኒያሁ በተጨማሪም በኢራን እና በእስራኤል መካከል የጥቃት መመላለስ መከሰቱን ተከትሎ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

  6. “የመጨረሻው ግብ ሊሳካ ስለሆነ” ሁሉም ወገኖች ከጥቃት እንዲቆጠቡ ፓኪስታን አሳሰበች

    ኢራን እና አሜሪካን የምታሸማግለው የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባዝ ሻሪፍ ሰላም እንዲሰፍን “ሁሉም ወገኖች” ከጥቃት እንዲቆጠቡ አሳሰቡ።

    “በተለይም የመጨረሻው ግብ ሊሳካ በመሆኑ” ሁሉም ወገኖች ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጠይቀዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ የሆነው ኻታም አል-አንቢያ፤ እስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያቆም ቢያስታውቅም፤ በደቡብ ሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን “ከዚህ ቀደም ከነበረው በባሰ ሁኔታ ምላሽ ትሰጣለች” ሲል አስጠንቅቋል።

    እስራኤልም በኢራን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥያቄ መሠረት እንደምታቆም የእስራኤል ቴሌቪዥን ዘግቧል።

    የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው “በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተባባሰው ጥቃት የደካማ ተኩስ አቁም አደገኛነትን ያሳያል” ብለዋል።

    “ከወንድሞቻችን እና ከአጋሮቻችን ጋር በቀናነት እና በጥንቃቄ በመተባበር በዲፕሎማሲ ሰላም ለማምጣት እየሠራን ነው። በተለይም የመጨረሻው ግብ ሊሳካ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች ተቆጥበው ለሰላም ዕድል እንዲሰጡ እናሳስባለን” ሲሉም አክለዋል።

    ፓኪስታን ኢራን እና አሜሪካን በማሸማገል ዋነኛዋ አገር ናት። ያለፈው ሚያዝያ በኢስላማባድ የሁለቱን አገራት ልዑካን እንዲወያዩ አድርጋለች። በዚያው ወር ተጨማሪ ውይይቶች ለማካሄድ ብትሞክርም አልተሳካም።

  7. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴን በመገደቧ በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ ተጣለባት

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ “የባሕር ላይ እንቅስቃሴን በመገደቧ” የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ማዕቀብ እንደጣሉባት የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ አስታወቁ።

    በኤክስ ገጻቸው “መካከለኛው ምሥራቅ በሰላም ንግግሮች እና በስሱ የተኩስ አቁሞች አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛል” ብለዋል።

    “የቴህራን ድሮኖች በሆርሙዝ ወሽመጥ የባሕር እንቅስቃሴን አደጋ ውስጥ መጣላቸውን ቀጥለዋል። የኢራን ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው ሚኒስትሮች በግልጽ ተናግረዋል” ሲሉም አክለዋል።

    ለዚህም ምላሽ እንዲሆን የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ዛሬ ሰኞ በብራሰልስ ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት ኢራን ላይ ማዕቀብ መጣሉን የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ተናግረዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት እንደ ሆርሙዝ ወሽመጥ ያሉ ቁልፍ የሆኑ ዓለም አቀፍ መተላለፊያዎችን በተመለከተ ውሳኔ የሚያሳልፍበት የሕግ ማዕቀፍ ሲተገበር የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑን ኃላፊዋ አክለዋል።

  8. እስራኤል በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ‘በትራምፕ ጠያቂነት’ እንደምታቆም ተዘገበ

    እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥያቄ መሠረት እንደምታቆም የእስራኤል ቴሌቪዥን ዘገበ።

    የእስራኤሉ ቻናል 12 ኒውስ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ የእስራኤል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው “በትራምፕ ጠያቂነት” ጥቃቱ እንደሚቆም አመልክተዋል።

    ዘገባው ጨምሮም ሄዝቦላህ ጥቃቱን የሚቀጥል ከሆነ በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የምትፈጽመውን ወታደራዊ ጥቃት የምትቀጥል መሆኑን ገልጿል።

    ምንም እንኳን ዝርዝር መረጃ ባይወጣም የአሜሪካ እና የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በሁለቱ መሪዎች መካከል ዛሬ የስልክ ውይይት መደረጉን ዘግበዋል።

    ባለፈው ሳምንት ትራምፕ እና ኔታኒያሁ ባደረጉት የስልክ ምልልስ ላይ እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በምትፈጽመው ጥቃት ምክንያት ትራምፕ ጠንከር ያሉ ቃላት መጠቀማቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።

  9. የኢራን ጦር በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያቆም አስታወቀ

    የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ የሆነው ካሀታም አል-አንቢያ፤ እስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደሚያቆም ይፋ አደረገ።

    ዕዙ ባወጣው መግለጫ “የጦር ኃይሎቻችን የሚያካሂዱት ዘመቻ መቆሙን እናሳውቃለን” ብሏል።

    ነገር ግን በደቡብ ሊባኖስ የሚፈጸመው ጥቃት የሚቀጥል ከሆነ ኢራን “ከዚህ ቀደም ከነበረው በባሰ ሁኔታ ምላሽ ትሰጣለች” ሲል አስጠንቅቋል።

    እስራኤል በደቡባዊ ቤይሩት ላይ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው ትናንት እሑድ ሲሆን፤ የእስራኤል ጦርም በኢራን ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    የቴህራን ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ትናንት ምሽት በሰጡት ማስጠንቀቂያ ኢራን የተኩስ አቁሙ በመጣሱ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝተዋል።

    በሊባኖስ እና በእስራኤል መካከል ተደርሶ የነበረውን የተኩስ አቁም፤ ኢራን ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር የተደረሰው አጠቃላይ የተኩስ አቁም አካል አድርጋ ትወስደዋለች።

  10. ትራምፕ እስራኤል እና ኢራን አሁኑኑ ‘መታኮስ’ ማቆም አለባቸው አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እና ኢራን አሁኑኑ ’መታኮስ’ ማቆም አለባቸው አሉ።

    ፕሬዚዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ አገራቱ እርስ በእርሳቸው መታኮስ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

    እስራኤል የአጸፋ ምላሽ ከመስጠቷ ቀድም ብሎ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢራን ላይ የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ አስጠንቅቀው ነበር።

    እስራኤል ትናንት በቤይሩት ላይ የፈጸመችውን ድብደባ ተከትሎ ኢራን ወደ ሰሜን እስራኤል ሚሳዔል አስወንጭፋለች።

    ይህንን ተከትሎ እስራኤል በመካከለኛው እና ምዕራብ ኢራን በሚገኙ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።

    በቴህራን በርካታ ፍንዳታዎች መሰማታቸው ከተገለጸ በኋላ የኢራን አየር መካላከያ በቴህራን ላይ እየበረረ የነበረ ድሮንን መትቶ መጣሉን ሜኸር የዜና ወኪል አስታውቋል።

    የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ለእስራኤል ጥቃት አሜሪካ ኃላፊነት ትወስዳለች ሲሉ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል።

    ባጋይ በመግለጫቸው የእስራኤል አቋም ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚቃረን በመጥቀስ “በድርድሩ ላይ ጥላውን ያጠላል” ብለዋል።

  11. ኢራን እና አሜሪካ መልዕክት መለዋወጥ “አላቋረጡም” - የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር መልዕክት መለዋወጥ “አለማቋረጧን” ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህንን ቢሉም የመልዕክት ልውውጡ እስከ ትናንት ድረስ መቀጠል አለመቀጠሉን አላረጋገጡም።

    አክለውም የፓኪስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሺን ናቅቪ ከሁለት ቀን በፊት ቴህራን የመጡት “ንግግሮች እንዲቀጥሉ ለማገዝ እና ከድርድር ጋር ያሉ ጉዳዮችን ለመነጋገር” ነው ብለዋል።

    ፓኪስታን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በሚደረገው ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች።

    ናቅቪ ወደ ቴህራን የሄዱት ከፓኪስታኑ መሪ ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ የተላከ ደብዳቤ ይዘው ነበር።

    አንዳንድ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከሳምንት በፊት እስራኤል በሊባኖስ የምታደርገውን ድብደባ በመቃወም ቴህራን ከዋሺንግተን ጋር የመልዕክት ልውውጧን አቋርጣለች በሚል ዘግበው ነበር።

    ቴህራን አና ዋሺንግትን የተኩስ አቁም ካደረጉ እአአ ከሚያዚያ 8 ጀምሮ የመልዕክት ልውውጥ እያደረጉ መሆናቸው ሲገልጽ ቆይቷል።

    ሚያዚያ 11 እና 12 የሁለቱ አገራት ልዑካን በኢዝላማባድ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

  12. ሁቲ እስራኤል በቀይ ባሕር ላይ የምታደርገውን እንቅስቀሴ "ማገዱን" አስታወቀ

    በኢራን የሚደገፈው የየመን ታጣቂ ቡድን ሁቲ እስራኤል በቀይ ባሕር ላይ የምታደርገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ማገዱን አስታወቀ።

    ቡድኑ የእስራኤል መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ ከሆነ ጥቃት እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል።

    ከዚህ ቀደም ሁቲዎች የእስራኤል መርከቦች በቀይ ባህር ላይ ሲንቀሳቀሱ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

    የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬአ በሰጡት መግለጫ የሁቲ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን መተኮሳቸውን ገልጸዋል።

  13. የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሜክሲኮ ገባ

    በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሜክሲኮ መግባቱ ተገለጸ።

    ቡድኑ ከቪዛ እና በአሜሪካ ከሚገኙ ስታዲየሞችን ከመጠቀም ጋር በተነሳ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር።

    የኢራን ሦስቱም ጨዋታዎች የሚካሄዱት በአሜሪካ ቢሆንም፣ ተጫዋቾቹ እና የድጋፍ ሰጪዎች በጨዋታው ዕለት አሜሪካ ገብተው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

    ኢራን 15 የቡድኑ ልዑካን አባላት እና ባለሥልጣናት ቪዛ መከልከላቸውን አስታውቃለች። እርምጃውንም በስፖርቱ ላይ የሚካሄድ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ስትል ኮንናዋለች።

    ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማለፉን ያረጋገጠው የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ አንድ ዓመት ቀድም ብሎ ነበር።

    የኢራን ቡድን ቲዋና የደረሰው በአገሬው አቆጣጠር እሁድ ማለዳ ሲሆን የልምምድ ሜዳቸውን ከአሪዞና ወደ ሜክሲኮ ያዞሩት በግንቦት ወር ላይ ነበር።

    የዘንድሮው የዓለም ዋንጫን አሜሪካ ከሜክሲኮ እና ካናዳ ጋር በመሆን በጥምረት ታዘጋጃለች።

  14. ትራምፕ፣ ኔታንያሁ ስምምነቱን ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ማንኛውም ስምምነት ኔታንያሁ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም ሲሉ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናገሩ።

    ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ “አማራጭ የለውም” ሲሉ በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ወቅት ተናግረዋል። “እኔ ነኝ ውሳኔውን የምሰጠው። እኔ ነኝ ሁሉንም ውሳኔ የምሰጠው። እርሱ [ኔታንያሁ] አይደለም ውሳኔ ሰጪው” ብለዋል።

    ትራምፕ ከአክሲዮስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ኔታንያሁ የሰላም ስምምነቱ እንዳይከሽፍ ለማድረግ ለኢራን ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ እንደሚነግሯቸው ገልጸው ነበር።

    ትራምፕ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ደግሞ የተፈጸመው ጥቃት “በስምምነቱ ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም” ብለዋል።

    አክለውም “እንዴት ሆኖ እንደሚጠናቀቅ እናያለን። ላለፉት 3000 ዓመታት 47 ዓመታት ሲሆን የነበረው ነገር ነው፤ ወይም እንደምትቆጥርበት መንገድ ይወሰናል” ብለዋል።

  15. ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ጦሯ የአጸፋ ምላሽ ሰጠ

    ኢራን በሚያዚያ ወር ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ከደረሰች ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን አስወነጨፈች። የእስራኤል ጦር የቴህራን ጥቃትን ተከትሎ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራን በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሚሳዔሎቹ “ለሳምንት የሚቀጥለው ጥቃት” የመጀመሪያ ነው ሲል አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር በቴሌግራም ገጹ ላይ "ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የእስራኤል አየር ኃይል የኢራን አሸባሪ አገዛዝ ንብረት የሆኑ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራን የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ደብድቧል" ሲል ጽፏል።

    እስራኤል በበኩሏ በሰሜናዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማክሸፏን ገለጻ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግን ያለችው የለም።

    እሁድ ዕለት እስራአል በደቡባዊ ቤይሩት የሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።

    የጦሩ ቃል አቀባይ ኢራን “ትልቅ ስህተት ሰርታለቸ” ሲሉ ተናግረዋል። ፎክስ ኒውስ በበኩሉ ትራምፕ ኢራንን “ይበቃል ወደ ድርድር ጠረጴዛው ተመለሽ” ሲሉ መናገራቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአክሲዮስ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢራን ሚሳዔሎች የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ እንደሚናግሯቸው ገልጸዋል።

    “አሁን ለቢቢ እደውልለታለሁ እና የአጸፋ ምላሸ እንዳሰጥ እነግረዋለሁ” ብለዋል። “ሁለቱም የራሳቸው ደስታን አግኝተዋል። እስራኤል አጥቅታለች እናም ኢራን አጥቅታለች። ተጨማሪ አንፈልግም።”

    “ከኢራን ጋር ወደ መጨረሻው ስምምነት ተቃርበናል። ጥሩ ስምምነት ነው የሚሆነው። አሁን እየሆነው ባለው የተነሳ ይህንን ማጣት አልፈልግም” ማለታቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።

    ትራምፕ አክለውም እስራኤል ዳግም ጥቃት ከፈጸመች ግጭቱ “ለ47 ዓመታት ወይም እንደ 3000 ዓመታቱ” ይቀጥላል ብለዋል። አክሲዮስ ትራምፕ ለኔታንያሁ መደወላቸውን ጨምሮ ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ በቴሌግራም ገጹ ላይ ሌተናል ጄነራል ኢያል ዛሚርን በመጥቀስ “ጠላትን በቁርጠኝነት ትዕዛዝ እንደተሰጠን መደብደብ አንጀምራለን” ብሏል።