
የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምስሉ መግለጫ, የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነት (በስተግራ) እና የፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ (በስተቀኝ) ቅዳሜ ወደ ኢዝላማባድ እንዲሚጓዙ ተገልጿልየኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ትናንት
ምሽት ፓኪስታን የደረሱ ሲሆን የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደርም ሁለት ተደራዳሪዎቹን ወደ ዋና ከተማዋ ኢዝላማባድ እንደሚልክ ገልጿል።
እንደ ዋይት ሐውስ ገለጻ የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ
ስቲቭ ዊትኮፍ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር ቅዳሜ ወደ ኢዝላማባድ የሚበርሩት ኢራን “በአካል” መነጋገር ስለፈለገች ነው።
ንግግሩ ውጤታማ የሚሆን ከሆነ የተደራዳሪው ቡድን
መሪ የሆኑት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ወደ ፓኪስታን ለመጓዝ “ዝግጁ” መሆናቸውን የዋይት ሐውስ ፕሬስ ኃላፊ ካሮሊን
ሌቪት ተናግረዋል።
በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የወጣው
መረጃ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር አርብ ምሽት ኢዝላማባድ መድረሳቸውን የገለጹት
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ፤ ሚኒስሩ “ከፓኪስታን ከፍተኛ አመራሮች ጋር” እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።
አክለውም “በኢራን እና አሜሪካ መካከል
እንዲካሄድ የታቀደ ስብሰባ የለም። የኢራን ምልከታዎች ለፓኪስታን ይቀርባሉ” ሲሉ የቴህራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ተደራዳሪዎች ጋር
በቀጥታ እንደማይነጋገሩ አመልክተዋል።
አርብ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ የነበራቸው የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ሌቪት
እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተደራዳሪዎቻቸውን ወደ ኢዝላማባድ የላኩት “ኢራናውያኑን ለመስማት” ነው። ትራምፕ “ሁሌም ለዲፕሎማሲ
ዕድል ለመስጠት ፈቃደኛ” መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“በእርግጠኝነት ባለፉት ሁለት ቀናት ከኢራን
ወገን በኩል የተወሰነ መሻሻል ተመልክተናል” ብለዋል።
በኢዝላማባድ የሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ግን የውጭ
ጉዳይ ሚኒስትሩ አራግቺ በፓኪስታን ጉዟቸው ያቀዱት “የሁለትዮሽ ጉዳዮችን ለመገምገም” እና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን ለመወያየት እንደሆነ
ገልጿል። አራግቺ ከፓኪስታን በተጨማሪ ወደ ኦማን እና ሩሲያ እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።
ከዚህ አስቀድሞ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትርምፕ
ባለሥልጣናቶቻቸው ኢራን ውስጥ “አሁን ኃላፊነት ላይ ካሉት ሰዎች ጋር” እየተደራደሩ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ኢራን “መደራደሪያ አቅርባለች፤ እንመለከተዋለን”
ብለዋል፤ ቀርቧል ስላሉት የድርድር ነጥቦች ግን ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል።