ቀጥታ, ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ

የሁለቱ አገራት የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በአፋጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው፤ ካልሆነ አንዳች ነገራቸው እንኳ አይተርፍም” ብለው ዝተዋል። በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ዋናው ነገር ጊዜ ነው” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኒውክሌር ጣቢያ አቅራቢያ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እሑድ ዕለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዋ አቅራቢያ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት እሳት እንዲነሳ ማድረጉን አስታወቀች።

    ክስተቱን “አደገኛ [የግጭት] መባባስ” ስትል የጠራችው ኤምሬቶች፤ ባለሥልጣናት ጥቃቱ ከየት እንደተፈጸመ እየመረመሩ መሆኑን ገልጻለች።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ድሮኖች ወደ ኤምሬቶች ግዛት የገቡት “በምዕራብ የድንበር አቅጣጫ" በኩል ነው።

    ሁለቱ ድሮኖች እንደተጠለፉ እና ሦስተኛው ግን በአቡ ዳቢ የሚገኘው የባራካህ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ "ከውስጣዊው ቅጥር ግቢ ይዞታ ውጭ" የሚገኝ የኤሌክትሪክ ጄነሬተርን እንደመታ ተገልጿል። እሳቱም የተነሳው በዚሁ ምክንያት ነው ተብሏል።

    በጥቃቱ ጉዳት አለመድረሱን የሚናገሩት ባለሥልጣናቱ፤ በአካባቢው የራዲዮሎጂካል ደኅንነት ደረጃ ላይም ተጽዕኖ አለማሳደሩን ገልጸዋል።

    የኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክስተቱን "ተቀባይነት የሌለው የጥቃት ድርጊት" በማለት ጠርቶታል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለማንኛውም ጠበኛ ድርጊት ምላሽ የመስጠት መብት እንዳላት አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ "ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ተቋማትን ዒላማ ማድረግ ግልጽ የዓለም አቀፍ ሕግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነት እና የሰብአዊ ሕግ መርሆዎች ጥሰት ነው" ብሏል።

    የኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ "የአገሪቱን ደኅንነት ለማዳከም የሚደረጉ ማናቸውንም ሙከራዎች በጽናት እንደሚጋፈጥ" አስታውቋል።

    የአገሪቱ ባለሥልጣናት ድሮኑ ከየት እንደተተኮሰ እስካሁን አልገለጹም። ከዚህ ቀደም ግን ኤምሬቶች ከጦርነቱ መነሳት ወዲህ በነዳጅ እና በኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶቿ ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጀርባ ኢራን እንዳለች በመግለጽ በተደጋጋሚ ከስሳለች።

    የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ በክስተቱ “ከፍተኛ ስጋት” እንደገባቸው ተናግረዋል።

    ዋና ዳይሬክተሩ በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የኤክስ ገጽ በወጣው መግለጫቸው፤ "የኒውክሌር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

  2. ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ጊዜው እየተገባደደ ነው” ሲሉ ኢራንን አስጠነቀቁ።

    የሁለቱ አገራት የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ሲሆን፤ ትራምፕ “በአፋጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው፤ ካልሆነ አንዳች ነገራቸው እንኳ አይተርፍም” ብለው ዝተዋል። በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ “ዋናው ነገር ጊዜ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ትናንት እሑድ በስልክ መነጋገራቸውን ተከትሎ ነው።

    ቴህራን ጦርነቱን ለማቆም ያቀረበችው የሰላም ዕቅድ ላይ አሜሪካ ከስምምነት መድረስ አለመቻሏን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ዋሽንግተን የሰላም ዕቅዱ ተቀባይነት እንዲኖረው ጥረት ካላደረገች ውጤት እንደማይገኝ የኢራኑ መህር የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ያሳለፍነው ሳምንት ትራምፕ የሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም “በቋፍ ላይ ነው” ሲሉ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ መሆኑን ገልጸዋል።

    የኢራን የሰላም ዕቅድ “ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለው ትራምፕ ቢያጣጥሉም፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጊ “ምክንያታዊ እና ለጋስ” ነጥቦች እንዳቀረቡ ተናግረዋል።