ቀጥታ, ትራምፕ ሆርሙዝን ለማስከፈት የጀመሩትን ዘመቻ ካቆሙ በኋላ ኢራን “ፍትሃዊ” የሆነ ስምምነት እንደምትፈልግ አስታወቀች

ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ካልሆነ በስተቀር እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ። ማክሰኞ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ንግግር “ትልቅ መሻሻል” እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። ቤይጂንግ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “በድርድሩ ሕጋዊ መብቶቻችን እና ጥቅሞቻችንን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ቻይና በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም እንዲከፈት ጠየቀች

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እና የኢራኑ አባስ አራጋቺ

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከኢራኑ አቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት የሆርሙዝ ወሽመጥ “በተቻለ ፍጥነት” ዳግም እንዲከፈት ጠየቁ።

    ረቡዕ ዕለት በቤይጂንግ የተገናኙት ባለሥልጣኖቹ በሁለትዮች ጉዳዮች በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ቤይጂንግ የሄዱት ከዶናልድ ትራምፐ ይፋዊ ጉብኝት አንድ ሳምንት ቀድመው ነው።

    ዋንግ ዪ "ቻይና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አስቸኳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ታምናለች፣ ግጭት ዳግም መቀስቀስ አስፈላጊ አይደለም" ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    “የባህር ወሽመጡን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መደበኛ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ረገድ የጋራ ስጋት አለው፤ ቻይናም የሚመለከታቸው አካላት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚመጣው ጠንካራ ጥሪ በተቻለ ፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ ታደርጋለች።

    ቤይጂንግ በተደጋጋሚ አሜሪካ እና ኢራን እንዲደራደሩ ጥሪ የምታቀርብ ሲሆን ረቡዕ ዕለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ደግመዋል።

    ዋንግ አክለውም ቤይጂንግ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ላለማምረት ያላትን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን የቻይና የመንግሥት ሚዲያ ዘግበዋል።

  2. አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ያስቆማል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ሊፈራረሙ ነው- ሮይተርስ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የፓኪስታን ምንጮችን ጠቅሶ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል አንድ ገጽ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መቃረባቸውን ዘገበ።

    በስም ያልተጠቀሱት ምንጮቹ ለሮይተርስ “በቅርቡ እናፈራርማለን፤ በጣመ ተቃርበናል” ሲሉ ተናግረዋል።

    አክሲዮስ በበኩሉ ዋይት ሐውስ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስቸል ሰነድ ላይ ለመፈራረም መቃረቡን እንደሚያምን ዘግቧል።

    ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ማናገሩን እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተሰጣቸው ሁለት ሌሎች ምንጮችን የጠቀስው መገናኛ ብዙኃኑ የመግባቢያ ሰነዱን ሊፈረም መሆን አረጋግጠዋል።

    ባለ አንድ ገጽ ነው የተባለው የመግባቢያ ሰነድ ስለ ኒውክሌር ድርድር ማዕቀፍን እንደሚያስቀምጥ ተጠቅሷል።

    ከእነዚህም መካከል የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ፣ የማዕቀብ መነሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ ምንም እክል መርከቦች እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ በሰነዱ ላይ መካተታቸው ተዘግቧል።

    በሁለቱ አገራት ንግግር ውስጥ የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት ሳያግባቧቸው የቆዩ ጉዳዮች ናቸው።

    አክሲዮስ ምንጮችን ጠቅሶ በርካቶቹ በሰነዱ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የመጨረሻ ስምምነት እንዳልተደረሰባቸው ዘግቧል።

    ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውሰጥ ከቴህራን ምላሽ ለማግኘት እየጠበቀች ሲሆን እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት የተደረሰበት ነገር አለመኖሩን ምንጮችን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘግቧል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሐውስን እንዲሁም ከኢራን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

  3. የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በ26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል

    የታይላንድን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ ጥቃት ከደረሰባቸው መከካል አንደኛው ነው

    የፎቶው ባለመብት, Royal Thai Navy

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ 26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ደርሰዋል ሲል የዩኬ የባህር ትራንስፖርት ንግድ ተቋም (ዩኬኤምቲኦ) ገለጸ።

    ከየካቲት 21 ጀምሮ በባህረ ሰላጤው፣ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ እና አካባቢው 46 ክስተቶች እንደደረሱት አሳውቋል።

    ከእነዚህ ውስጥ 26ቱ ጥቃቶች ሲሆኑ 18ቱ ደግሞ "አጠራጣሪ እንቅስቃሴ" እንደነበሩ እና ሁለት የጠለፋ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ሪፖርት ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የፈረንሳይ የመርከብ ተቋም የሆነው ሲኤምኤ ሲጂኤም ዛሬ ጠዋት እንደገለጸው ሳን አንቶኒዮ የተባለው መርከብ ማክሰኞ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ሲያቋርጥ የጥቃት ዒላማ ሆኖ በመርከቡ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በጥቃቱ የተጎዱት የመርከቡ ሠራተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውን እና የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል።

    ተቋሙ አክሎም "ሲኤምኤ ሲጂኤም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ከመርከበኞቹ ጎን ይቆማል” ብሏል።

  4. ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች

    ኮንቴህነር የጫነች መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ካልሆነ በስተቀር እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።

    ማክሰኞ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ንግግር “ትልቅ መሻሻል” እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

    ቤጂንግ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “በድርድሩ ሕጋዊ መብቶቻችን እና ጥቅሞቻችንን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    አባስ አራግቺ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ “ፍትሃዊ እና የተሟላ ስምምነትን ብቻ” እንቀበላለን ማለታቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።

    አራግቺ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ንግግር ለመደገፍ በሚል በሆርሙዝ ወሽመጥ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጀብ ጀምረውት የነበረውን ዘመቻ ስለማቆማቸው ያሉት ነገር የለም።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ለመርከቦች እንቅስቀቃሴ ዝግ ሆኗል።

    በዚህም የተነሳ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።

    ትራምፕ በትናንትናው ዕለት “በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ እየቀጠለ ሳለ ፕሮጀክት ፍሪደም. . . ስምምነቱ ይጠናቀቅ እና ይፈረም እንደሆነ ለማየት ለአጭር ጊዜ እንዲቆም በጋራ ተስማምተናል” ብለዋል።

    የትራምፕን የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ ተከትሎ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ1.2 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በበርሜል 108.6 ዶላር መሸጥ ጀምሯል።

    ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢራን በሆርሙዝ ላይ የሚደረግን እንቅስቃሴ ልትቆጣጠር አይፈቀድላትም ሲሉ ተናግረዋል።

  5. የቻይና እና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቤይጂንግ ተገናኝተው ተወያዩ

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራኑ አቻቸው ጋር

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት የኢራኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺን ተቀብለው ማነጋገራቸው ዢንዋ ዘገበ።

    አራግቺ አገራቸው ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመርያቸው ነው።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቤይጂንግ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከመምጣታቸው ጥቂት ቀን ቀደም ብሎ ነው።

    የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዢንዋ አራግቺ በቤዢንግ የተገኙት በቻይና መንግሥት ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።

    አራጋቺ ቻይና ከገቡ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለጊዜው መቆሙን ሲያስታውቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በሁለትዮሽ ጉዳዮች በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚወያዩ ተናግረዋል።

    ሁለቱ ሚኒስቴሮች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሦስት ጊዜ በስልክ የተወያዩ ሲሆን ቤጂንግ በተደጋጋሚ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲሆን ሲጠይቁ ቆይተዋል።

    ከጦርነቱ በፊት 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚያልፈው በወሽመጡ በኩል ነበር።

    ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ በእጅጉ ተስተጓጉሏል።

    ቻይና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ እና ጋዝ ከሚገዙ አገራት ግንባር ቀደሟ ናት።

  6. ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስላካሄዱት ‘ፕሮጀክት ፍሪደም” ምን እናውቃለን?

    በወሽመጡ ላይ የቆሙ ጀልባዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙትን መርከቦች አጅበው ለማስወጣት ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው ማቆማቸውን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ዘመቻው ሰብዓዊ አላማ እንዳለው “ሰዎችን ነጻ ማውጣት፣ ኩባንያዎችን እና ምንም ጥፋት የሌለባቸውን አገራት ነጻ ማውጣት ማለት ው” ሲሉ ተናግረው ነበር።

    ኢራን መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ የሚችሉት በእርሷ ፈቃድ ብቻ መሆኑን ተናግራለች።

    ትራምፕ ይህንን ዘመቻ ይፋ አድርገው የነበረው እሁድ ዕለት ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢራን ጦር ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከረ የአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ መተኮሱን ሲናገር አሜሪካ በበኩሏ አነስተኛ ጀልባዎችን መትታ ማስመጧን ተናግራለች።

    አሜሪካ ይህንን ዘመቻ ይፋ ካደረገች ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ ለማየት በሚል ዘመቻው ለአጭር ጊዜ እንደሚቆም ተናግረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ የተዘጋው እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ቴህራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ነው።

    ቴህራን የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።

    አሜሪካ 22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን ትናገራለች።

    እነዚህ ባህረተኞች የ87 አገራት ዜጎች መሆናቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ተናግረዋል።

    ሰኞ ዕለት ሴንትኮም የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መሰማራቱን ገልጾ ነበር።

    ኢራን የአሜሪካ ዘመቻ ከመጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብላ ማስጠንቀቂያ በማውጣት ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከሩ የአሜሪካ መርከቦች ላይ ሁለት ሚሳዔሎችን መተኮሷን ተናግራለች።

    ሴንትኮም የኢራንን መግለጫ ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል። አክሎም ኢራን ወደ ጦር መርከብ እና የአሜሪካ ባንዲራ ወደምታውለበልብ የንግድ መርከብ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን መተኮሷን እንዲሁም አነስተኛ ጀልባዎች በመጠቀም ጥቃት ለመፈጸም መሞከሯን ተናግሯል።

    ዩኤኢ ከኢራን በተተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቃለች።

    በጥቃቱም የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ መመታቱን ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቃች።

    በወሽመጡ በዩኤኢ አቅራቢያ የቆመ የደቡብ ኮሪያ የጭነት መርከብም ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሴንቲኮም አሜሪካ ሂሊኮፕተሮችን ስድስት አነስተኛ ኢራን ጀልባዎች መትተው ማስመጣቸውን አሰታውቋል። ኢራን ግን እህንን አስተባብላለች።

    ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ አገዛዙን ፈቃድ በማይጠየቁ ላይ “ወሳኝ እርምጃ እወሰዳለሁ” ስትል አስጠንቅቃለች።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በሰጡት መግለጫ ላይ የተኩስ አቁሙ አለመክሸፉን ተናግረዋል።

  7. ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” አሉ

    ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ዓላማዎቿን በማሳካቷ በኢራን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ “መጠናቀቁን” ገለጹ።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነበር።

    ሩቢዮ በዋይት ሐውስ በሰጡት በዚህ መግለጫ “ኦፕሬሽን ኢፒክ ፉሪ ተጠናቅቋል። የዘመቻውን ዓላማዎቻችንን አሳክተናል፤ . . . የሰላም መንገድን እንመርጣለን። ፕሬዚዳንቱ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሩቢዮ አሜሪካ ሰኞ ዕለት አዲስ የጀመረችው ዘመቻ ዓላማ የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።

    ይህ አነስተኛ መጠን ያለው ዘመቻ ከመጀመርያው ወታደራዊ ዘመቻ የተለየ መሆኑን በመግለጽ አሜሪካ “ካልተተኮሰባት በስተቀር” ወታደራዊ ምላሽ እንደማትሰጥ ተናግረዋል።

    አሜሪካ በኢራን ኣለይ ጦርነት የከፈተችበት አንዱ ምክንያት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታመርት ለመከላከል ነው።

    አሜሪካ የኢራንን በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገ 408 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ማውጣት እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ማስደረግ እስካሁን ድረሰ አልቻለችም።

    በሆርሙዝ ወሽመት ባንዳራ አባስወደብ አቅራቢያ ቆሙ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Amirhosein Khorgooi/ISNA/WANA (West Asia News Agency) via REUTERS

    ሩቢዮ በመግለጫቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ መንቀቀሳቀስ ላልቻሉ መርከቦች መንገዱን ለማስከፈት የተጀመረው ዘመቻ ከ87 አገራት የተውጣጡ የ23ሺህ ሰዎችን ሰቆቃ የሚያስቆም ነው ብለዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ባለው ግጭት ምክንያት እስካሁን ድረስ 10 ባህረተኞች መሞታቸውን ተናግረዋል።

    “ተነጥለው ነው ያሉት፤ እየተራቡ ነው፥ ተጋላጭ ናቸው። ቢያንስ 10 ባህረተኞች በዚህ የተነሳ ሞተዋል፤ ሲቪል ባህረተኞች” ብለዋል።

    ሩቢዮ ሞቱ ስላልዋቸው ባህረተኞች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሩቢዮ ከበርካታ መርከቦች ጋር የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋርጦ ስለመውጣት በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

    ሩቢዮ አሁን ጊዜው ቴህራን “የሁኔታውን እውነታ የምትቀበልበት ነው” በማለት የአሜሪካ ልዑካን የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር የዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መፈለጋቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።

    ሩቢዮ አክለውም መፍትሄው ኢራን “የሆነ ስፍራ የደበቀችውን የኒውክሌር ቁስ ይመለከታል” ሲሉ ተናግረዋል

    "ፕሬዚዳንቱ የድርድር ሂደቱ አካል የበለጸገው [ዩራኒየም] ብቻ ሳይሆን የሆነ ስፍራ የቀበሩትን ቆፍረው ማውጣት ከቻሉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ነው " ብለዋል።

    ሩቢዮ በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ውይይት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    “ይህ በጣም ውስብስብ ነው፤ በጣም ቴክኒካዊ ነው። ነገር ግን እነሱ ለመደራደር ፍቃደኛ ስለሆኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እና እነዚያን ንግግሮች ጠቃሚ ለማድረግ በግንባር ቀደምትነት ሊያደርጉት ስለሚችሉት መጠን በጣም ግልፅየሆነ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊኖረን ይገባል" ብለዋል።

  8. ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት የኢራን ጦር አቅምን አጣጥለው ቴህራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት” ነበረባት ግን ያንን ለማድረግ የቴህራን ባለሥልጣናት ትምክህት ይዟቸዋል አሉ።

    ትራምፕ በኦቫል ኦቪስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የኢራን ጦር ደካማ መሆኑን እና "የመጫወቻ ጠመንጃዎች" ይጠቀማሉ ሲሉ ተሳልቀዋል።

    ኢራን በአደባባይ የምትለው ሌላ ቢሆንም በምስጢር ግን ከስምምነት መድረስ ትፈልጋለች ሲሉም ተናግረዋል።

    “ጨዋታ ይጫወታሉ። ነገር ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። ጦሩ ሙሉ በሙሉ ከወደመበት ማን የማይፈልግ አለ” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ምንም አማራጭ የላትም” በማለት የቴህራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ሲነጋገሩ እና ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ የተለያየ ነገር ይናገራሉ ሲሉ ተችዋቸዋል።

    “ምንም አማራጭ የላትም፤ ኖሯትም አያውቅም” በማለት የኢራን ጦር መሸነፉን ዳግም ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራቸው አንፈቅድም” ሲሉ አስተየየታቸውን ሰጥተዋል።

    አሜሪካ “ኢራንን ክፉኛ ደቁሳታለች” ያሉት ትራምፕ “በጠመንጃ ብቻ ጥቂት ጀልባዎችን መቀነስ ችለናል” ብለዋል።

    ሰኞ ዕለት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበሩ የኢራን ጀልባዎችን መምታቷን አስታውቃለች።

    ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ በኢራን በመዘጋቱ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንደሚያስወጡ የተናገሩት ትራምፕ፤ “ሰባት ትንሽ ጀልባዎችም ወይም እነሱ ‘ፈጣን’ ጀልባ የሚሏቸውን መትተናል። የቀሯቸው እነሱ ብቻ ነበሩ” ብለዋል።

    ትራምፕ በኦቫል ኢፊስ በሰጡት መግለጫ ኢራን በጦርነቱ መጀመርያ ወቅት 159 መርከቦች እንደነበሯት ገልጸው “ያሏቸው እያንዳንዱ መርከብ ከባሕር ወለል በታች ነው የሚገኙት’ ሲሉ ተናግረዋል።

    በባሕር ኃይላቸው ምንም ዓይነት መርከብ የላቸውም ያሉት ትራምፕ ከዚያ ይልቅ ስምንት “ትንሽ ጀልባዎች” ነበሩ እነርሱም “ሁሉም ወድመዋል” ብለዋል።

    አክለውም “ከእኛ ታላቅ ባሕር ኃይል ጋር ለመገዳደር ትንንሽ ጀልባ እየፈለጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያሉ የኢራን ጀልባዎች

    የፎቶው ባለመብት, REUTERS

    ኢራን የተኩስ አቁሙን ጣሰች የሚባለው ምን ስታደርግ ነው ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ “ስለምነግራችሁ ታውቁታላችሁ” በማለት መልሰዋል።

    “በጣም አስፈላጊው ነገር ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው ያውቃሉ” ብለዋል።

    ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” ያሉት ትራምፕ “ይህ መደበኛ ውጊያ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ አቁመውት ነበር” ብለዋል።

    አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ማገዷን በተመለከተም ሲናገሩ አንድም መርከብ ማለፍ እንዳልቻለ አብራርተዋል።

    አንድ መርከብ ለማለፍ ሲሞክር ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ የአሜሪካ ጦር “በአንድ ተኩስ ሞተሩን መትቶታል” ብለዋል።

    ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር “ትልልቅ ስምምነቶችን” እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

    በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቻይና በሚጓዙበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋርም መልካም ንግግር ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ ጣለችው እገዳ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ቴህራን “ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።

    “ጨዋታ ይጫወታሉ። የምነግራችሁ ነገር ግን ከስምምነት መድረስ ይፈልጋሉ” ብለዋል።

  9. የሆርሙዝ ወሽመጥ ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በጋራ በመሆን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት መሆኑን ተናገሩ።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ አሜሪካ “ጦርነት አትፈልግም” ያሉ ሲሆን ነገርግን ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታ እንድትቀመጥ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ አክለውም የ’ፕሮጀክት ፍሪደም’ ግብ “ገለልተኛ የሆኑ የንግድ መርከቦችን ከኢራን ጥቃት መከላከል” መሆኑን ተናግረዋል።

    ሄግሴት አክለውም ሁለት የአሜሪካን ባንዲራ የሚያውለበልቡ መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፋቸውን ገልጸው “መስመሩ ነጻ ነው” በማለት ኢራናውያን “ተዋርደዋል” ሲሉ አስታውቀዋል።

    የተኩስ አቁሙ “አልፈረሰም” ያሉት ሄግሴት ኢራን ዳግም ግጭቱን ላለመጀመር “እንድትጠነቀቅ” አሳስበዋል።

    22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, 22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

    የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በበኩላቸው ኢራን የተኩስ አቁሙ ከተጀመረ አንስቶ አስር ጊዜ ያህል የአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ከስሰዋል።

    አክለውም እነዚህ ጥቃቶች “በአሁን ሰዓት” ጦርነቱን ለመጀመር “ከመስፈርቱ በታች” ናቸው ብለዋል።

    ኬን ኢራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያለውን የዓለም አቀፉን የአቅርቦት ሰንሰለት "እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም” የወነጀሏት ሲሆን የመላው ዓለም ምጣኔ ሃብትን "አግታ ለመያዝ ጥረት አድርጋለች” ብለዋል።

    22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጄነራሉ በመግለጫቸው ላይ ተናገረዋል።

  10. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን ጋር የተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥቃት ቢቀጥልም አገራቸው ከኢራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ እና ኢራን ሰኞ ዕለት ጥቃት መፈጸማቸውን ቢቀጥሉም የተኩስ አቁሙ ባለበት መሆኑን ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁሙ “አልፈረሰም” ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ አሜሪካ ሰኞ ዕለት በወሽመጡ የጀመረችውን ዘመቻ “የተለየ፣ የተናጠል ፕሮጀክት ነው” ብለዋል።

    ኢራን ዳግም ግጭቱን ላለመጀመር “እንድትጠነቀቅ” አሳስበው “አሁን የተኩስ አቁሙ ባለበት” መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በበኩላቸው ኢራን ዘጠኝ ጊዜ የንግድ መርከቦች ላይ መተኮሷን ተናግረዋል።

    ቴህራን ሁለት የጭነት መርከቦችን መቆጣጠሯን የገለጹት ጄነራሉ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረ ጀምሮ 10 ጊዜ የአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ወንጅለዋታል።

    ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን ኢራን ላይ ሙሉ በሙሉ ጥቃት ለመጀመር አሁን ጊዜው አይደለም ያሉት ሲሆን፣ የቴህራን ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች እና አነስተኛ ጀልባዎች በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ ጦር ላይ የፈጸሙት ጥቃትን መመከታቸውን ተናግረዋል።

    22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

  11. በኢራን ጥቃት የተፈጸመበት የኤምሬትስ የነዳጅ ማዕከል ምን ያህል ወሳኝ ነው?

    ከነዳጅ ማጠራቀሚያ ላይ የሚታይ ጥቁር ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመበት ፉጃይራህ ባለፈው መጋቢት ከተፈጸመበት ጥቃት በኋላ በዚህ መልኩ በእሳት ተያይዞ ታይቷል

    ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ ስትፈጽም ለቆየችው ጥቃት ዋነኛ ዒላማ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፉጃይራህ የተባለው ዋነኛው የነዳጅ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዞን በቴህራን መመታቱን አስታውቃለች።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ላለፉት ሳምንታት የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ የተፈጸመውን ጥቃት አደራዳሪዋ ፓኪስታንን ጨምሮ በርካታ አገራት እና የአረብ ሊግ አውግዘውታል።

    ከዚህ ቀደምም ጥቃት የተፈጸመበት ፉጃይራህ የተባለው የነዳጅ ምርት ማዕከል የጥቃት ዒላማ እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው? ስለዞኑ ምን የሚታወቅ ነገር አለ?

    ፉጃይራህ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን በኤምሬትስ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ከወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ በስተደቡብ ይገኛል። ዞኑ ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ቦታ ላይ ያለ ነው።

    ፉጃይራህ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ማዕከላት መካከል አንዱ ነው። በዚህም ወደ 70 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ነዳጅ ማከማቸት የሚችል አቅም አለው።

    የማከማቻው ነዳጅ የመያዝ አቅም በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ በአንድ ቀን ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውለው ነዳጅ ውስጥ ሦስት አራተኛውን ያህል ያከማቻል።

    ይህም ማለት ዓለማችን በቀን 100 ሚሊዮን በርሜል በላይ የምትጠቀም ሲሆን፣ ፉጃይራህ ላይ የሚከማቸው ደግሞ 70 ሚሊዮን በርሜል የሚሆን ነው።

    ምንም እንኳን በጦርነቱ የተነሳ የሆርሙዝ ወሽመጥ ቢዘጋም ከአቡ ዳቢ የነዳጅ ማውጫዎች ከሚነሳው ደፍድፍ ነዳጅ የተወሰነው በቧንቧ አማካይነት በፉጃይራህ በኩል በመርከቦች በኩል ወደ ዓለም ገበያ እየቀረበ ይገኛል።

  12. እስራኤል በሊባኖስ 17 ሰዎችን በገደለች ማግሥት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አወጣች

    የቀብር ስነ ስርዓት

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የሊባኖስ ተኩስ አቁም ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ሞት ከታየባቸው ቀናት አንዱ በሆኖ በተመዘገበው በትናንትናው ዕለት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ አንስቶ በተፈጸሙ ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ብዛት 110 መድረሱን የሊባኖሱ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

    ሚኒስቴሩ ቁጥር ንጹኃን እና ተዋጊዎችን ለይቶ አላስቀመጠም። ይሁን እንጂ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሁለት ሕጻናት ሲሆኑ፣ 14 ሕጻናትም ተጎድተዋል።

    ጥቃት የምትፈጽመው በሺዓ እስላማዊው ቡድን ሄዝቦላህ ላይ መሆኑን የምትናገረው እስራኤል በበኩሏ፤ በደቡባዊ ሊባኖስ ሁለት ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

    የእስራኤል ጦር “ሄዝቦላህ በሚፈጽመው የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት” ምክንያት በቡድኑ ላይ “በኃይል ለመንቀሳቀስ መገደዱን” ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ይህንን ትዕዛዝ ከማስተላለፉ አስቀድሞ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽሟል የሚል ክስ አሰምቶ ነበር። ሄዝቦላህ ስለ ክሱ አስተያየት አልሰጠም።

    ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ 17 ወታደሮች እንደተገደሉባት የምትናገረው እስራኤል፤ ሄዝቦላህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች እና ድሮኖችን እንዳስወነጨፈ በመጥቀስ ትከስሳለች።

    ሄዝቦላህ፤ እስራኤል እና ሊባኖስ የደረሱበት የተኩስ አቁም ስምምነት ፈራሚ አካል አይደለም።እስራኤል ለስምምነቱ የምትገዛ ከሆነ ግን ተኩስ አቁሙን እንደሚቀበል ጠቆሞ ነበር።

    የእስራኤል ጦር በስምምነቱ መሠረት “የታቀዱ፣ አይቀሬ ወይም ቀጣይ ጥቃቶችን” መፈጸም እንደተፈቀደለት ይናገራል። የሊባኖስ ባለሥልጣናት ስምምነቱ በዚህ መልኩ መተርጎሙን የሚቃወሙ ሲሆን፣ እስራኤል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁሙን ጥሳለች የሚል ክስ ያቀርባሉ።

  13. ዓለም አቀፉ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ባለቤቶች ማኅበር የአሜሪካ እጀባ ዕቅድ “ከፍተኛ ለውጥ አያመጣም” አለ

    የጭነት መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, West Asia News Agency via REUTERS

    ዓለም አቀፉ የገለልተኛ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ባለቤቶች ማኅበር ‘ኢንተርታንኮ’፤ አሜሪካ ይፋ ያደረገችው የንግድ መርከቦችን አጅቦ በሆርሙዝ ወሽመጥ የማሳለፍ ዕቅድ "በከፍተኛ ሁኔታ የሚለውጠው ነገር የለም” አለ።

    ‘ሜርስክ’ የተሰኘው ግዙፍ የሎጂስቲክ ኩባንያ አንድ መርከቡ በአሜሪካ ጦር ታጅቦ ሰኞ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ማለፉን አስታውቋል። ከቢቢሲ ‘ቱዴይ’ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንተርታንኮ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቲም ዊልኪንስ፤ የመርከቡ ማለፍ እገዳውን በማቃለል ረገድ ያለው ተጽዕኖ “ውቅያኖስ ውስጥ እንዳለ ጠብታ ነው” ብለዋል።

    ዊልኪንስ “በጣም ጠባብ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በቅርብ እጀባ ተደርጎለት ያለፈው አንድ መርከብ ነው” ብለዋል። የመርከቡ ማለፍ መውጫ ላጡት የተቀሩት መርከቦች “ምንም ነገር ላይ ከፍተኛ ለውጥ አያመጣም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ገለልተኛ የነዳጅ ጫኝ ባለቤቶችን የሚወክለውን ማኅበር የሚመሩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አክለውም፤ “ተግባራዊ እየሆነ ያለ ቅርጽ ያለው ወይም የተቀናጀ ሥርዓት የለም። ስለዚህ አባላቶቻችን እየጠየቁ ያሉት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ነው፤ እነዚህን ጉዞዎች የሚያስጀምረው ማነው?” ብለዋል።

    “መርከቦቹን ወክሎ ከባለሥልጣናቱ ጋር የሚነጋገረው ማነው? ወሳኙ ጉዳይ ደግሞ በጉዞው ወቅት መርከቦቹ ከኢራን ኃይሎች ችግር ቢያጋጥማቸው የተያዘው ዕቅድ ምንድነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።

  14. ትራምፕ ኢራን የአሜሪካ መርከቦችን ካጠቃች "ከምድረ ገጽ ትጠፋለች" ሲሉ ዛቱ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን እንደዛተችው በአሜሪካ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፈጸመች ‘ከምድረ ገጽ ትጠፋለች’ ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር ሰኞ ዕለት ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ አሜሪካ ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ በሚል በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚተላለፉ መርከቦችን ለመጠበቅ በምትወስደው እርምጃ ወቅት በመርከቦቿ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ “ኢራን ከምድረ ገጽ ትጠፋለች” ሲሉ ዝተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም በድርድሩ ሂደት ኢራን “የበለጠ ልፍስፍስ” እየሆነች እንደሆነ እና የአገራቸው ሠራዊትም ከኢራን የተሻለ ወታደራዊ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

    ይህ የትራምፕ ቃለ ምልልስ የተሰማው የአሜሪካ ኃይሎች የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት እየወሰዱት ባለው እርምጃ ሰባት የኢራን “ትንንሽ ጀልባዎችን” መምታታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ካስታወቁ በኋላ ነው።

    በተጨማሪም አሜሪካ የኢራንን ድሮኖች እና ሚሳዔሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጦርነቱ ምክንያት በሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፍ ላልቻሉት የንግድ መርከቦቻቸው መንገድ መንገድ እንዲያስከፍቱ “በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት” ቀረበልኝ ባሉት ጥያቄ መሠረት ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ የተባለ ዘመቻ ከሰኞ ጀምሮ እያካሄዱ ነው።

    በዚህም የአሜሪካ ኃይሎች የመርከቦቹን ደኅንነት ለመጠበቅ ሆርሙዝ ላይ በመሰማራት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ነገር ግን ኢራን ይህንን የአሜሪካ እርምጃ በመቃወም የአሜሪካ ባሕር ኃይል መርከቦችን እንደምትመታ እየዛተች ነው።

  15. አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲሉ የኢራን ከፍተኛ ተደራዳሪ ገለጹ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ አሜሪካ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ያለውን የመርከብ እንቅስቃሴ እና የኢነርጂ ደኅንነት አደጋ ላይ ጥላለች ሲሉ ገለጹ።

    ባለፈው ወር ከአሜሪካ ጋር በተደረገው ንግግር ወቅት ከፍተኛ ተደራዳሪ የነበሩት የአሜሪካ አፈ ጉባዔው መሐመድ ባጊር ጋሊባፍ ዛሬ ጠዋት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሜሪካን "የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ" እና በባሕር ወሽመጡ ላይ "እገዳ" በመጣል ከሰዋል።

    ይህንን ያሉት ዶናልድ ትራምፕን "የነፃነት ፕሮጀክት" ሰኞ ዕለት መጀመሩን ከገለጹ በኋላ ነው። "አሁን ያለው ሁኔታ አይቀጥልም” ያሉ ሲሆን፣ ኢራን "እስካሁን አልጀመረችም" በማለት አፈ ጉባኤው ጽሁፋቸውን ደምድመዋል።

  16. በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የደረሰው አዲስ ጉዳት ውስን እንደሆነ የአሜሪካ የስለላ መረጃ አመለከተ

    የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይም በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ተፈጽሞባቸው ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይም በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት ተፈጽሞባቸው ነበር

    ሁለት ወር ባለፈው ጦርነት የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የደረሰው አዲስ ጉዳት ውስን በመሆኑ ቴህራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ለመገንባት የሚያስፈልጋት ጊዜ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ መሆኑን የአሜሪካ የስለላ መረጃ ማሳየቱን ሮይተርስ ዘገበ።

    ዜና ወኪሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሦስት ምንጮች ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ቦንብ እንዳትሠራ ለማስቆም ሲሉ የካቲት ላይ የከፈቱት ጦርነት በቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ያንን ያህል ለውጥ አላመጣም።

    አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነቱን የጀመሩት መደበኛ ወታደራዊ ዒላማዎችን በማጥቃት ቢሆንም ኋላ ላይ እስራኤል በርከት ያሉ ወሳኝ የኒውክሌር ተቋማትን መትታለች።

    ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቃቶች የኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ትታጠቅበታለች ተብሎ የሚታሰበው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ጉልህ ለውጥ ባለማምጣታቸው፤ የቴህራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ማውደም ወይም ያላትን የበለጸገ ዩራኒየም ክምችት ማስወጣት በአማራጭነት ተቀምጠዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ናታንዝ፣ ፎርዶው እና ኢስፋሃን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽመው ነበር። ሮይተርስ የጠቀሰው የአሜሪካ የስለላ መረጃ እንደሚያሳየው እነዚህ ጥቃቶች ኢራንን የኒውክሌር መሣሪያ ለመታጠቅ የሚያስፈልጋት ጊዜ የገፉት ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ብቻ ነው።

    በባለፈው ዓመት ጥቃት ሥራ ላይ የነበሩት ሦስት የማበልጸጊያ ተቋማት ቢመቱም፤ የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም 440 ኪሎ ግራም የሚደርሰው የኢራን 60 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም የት እንደሚገኝ ማረጋገጥ አልቻለም።

    ግማሽ ያህሉ በኢስፋሃን የኒውክሌር ምርምር ተቋም የምድር ስር ይገኛል ተብሎ እንደሚታመን ዜና ወኪሉ ጠቅሷል።

    የአሜሪካ እና ኢራን ባካሄዱት ድርድር ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ካደረጓቸው ጉዳዮች ዋነኛው የቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንድትታጠቅ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

    የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል እንደሆነ የምትገልጸው ኢራን በበኩሏ ዩራኒየም የማበልጸግ መብቷ እውቅና እንዲሰጠው የሚጠይቅ የስምምነት ሃሳብ ማቅረቧ ተዘግቧል።

  17. አሜሪካ በሰባት የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች

    ጀልባ ላይ ተጫኑ የኢራን ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበሩ ሰባት የኢራን “ፈጣን ጀልባዎች” ላይ ጥቃት መፈጸሟን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ በኢራን በመዘጋቱ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንደሚያስወጡ የተናገሩት ትራምፕ፤ “ሰባት ትንሽ ጀልባዎችም ወይም እነሱ ‘ፈጣን’ ጀልባ የሚሏቸውን መትተናል። የቀሯቸው እነሱ ብቻ ነበሩ” ብለዋል። የአሜሪካ ጦር እንደገለጸው ጀልባዎቹ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ሄሊኮፕተሮችን በመጠቀም ነው።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዛ (ሴንትኮም) ባወጣው መግለጫ “ዛሬ የንግድ መርከቦች ላይ አደጋ የጣሉትን የኢራንን አነስተኛ ጀልባዎች ለማስወገድ ሲ ሃውክ እና የአሜሪካ ጦር ኤኤች-64 አፓች ሄሊኮፕተሮች ጥቅም ላይ ውለዋል” ብሏል።

    ፕሬዝዳንቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ኢራን የደቡብ ኮሪያ መርከብን ጨምሮ ከግጭቱ ጋር “ግንኙነት በሌላቸው አገራት ላይ ተኩሳለች” ሲሉ ከስሰዋል።

    የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ትናንት እንዳስታወቀም ‘ኤችኤምኤም ናሙ’ የተሰኘ የአገሪቱ የጭነት መርከብ ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ጥቃት እንደሆነ በተጠረጠረ” ክስተት ጉዳት ደርሶበታል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቅራቢያ ቆሞ የነበረው ይህ መርከብ 24 ሠራተኞችን ይዞ እንደነበር የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል። በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተነገረም።

    ይህንን ጉዳይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ምናልባት ደቡብ ኮሪያ የምትመጣበት እና ተልዕኮውን የምትቀላቀልበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ግን የትራምፕ ተፈጽሟን ያሉትን የጀልባዎች ጥቃት አስተባብለዋል። አንድ ወታደራዊ ምንጭን የጠቀሰው ኢራኑ ታስኒም ዜና ወኪል እንደዘገባው ከሆነ ጥቃት የደረሰባቸው ሁለት የጭነት መርከቦች ናቸው። በዚህም አምስት ንጹኃን ተገድለዋል ብሏል።

    ጥቃት ተፈጽሟል ከመባሉ አስቀድሞ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አውዳሚ መርከብ እና ሁለት የአሜሪካን ባንዲራ የሚያውለበልቡ የንግድ መርከቦች በወሽመጡ ማለፋቸውን ዋሽንግተን አስታውቃ ነበር።

    ይህንን ገለጻ “ሙሉ በሙሉ ሐሰተኛ” ስትል የጠራቸውን ኢራን በበኩሏ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሷን ገልጻለች፤ የአሜሪካ ጦር ይህንን አስተባብሏል።

    ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት ‘መርስክ’ የተሰኘው የመርከብ ኩባንያ እንደገለጸው የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ያነገቡ እና ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት አንስቶ በባሕረ ሰላጤው ቆመው የነበሩ መርከቦቹ በወሽመጡ ማለፋቸውን አስታውቋል።

    ኩባንያው “በአሜሪካ ወታደራዊ ጥበቃ ስር ሆኖ መርከብ የማስወጣት ዕድል እንደቀረበለት” ገልጿል። “ይህንን ተከትሎም መርከቡ በአሜሪካ ጦር ታጅቦ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወጥቷል” ብሏል።

  18. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን የድሮን ጥቃት ተፈጸመበት

    ፉጃኢራህ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን መጋቢት ላይም ጥቃት ደርሶበት ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ፉጃኢራህ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን መጋቢት ላይም ጥቃት ደርሶበት ነበር

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቁልፍ የነዳጅ ወደብ በሆነው ፉጃኢራህ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች “መጠነኛ ጉዳት” እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የኢምሬቶች ትልቁ ወደብ እና የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ የሆነው ፉጃኢራህ፤ በኢራን ድሮን ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ከፍተኛ እሳት መከሰቱን ተገልጿል።

    በደረሰው ጥቃት የተጎዱት የሕንድ ዜግነት ያላቸው ሦስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል። የከተማው የመገናኛ ብዙኃን ቢሮ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው የደረሰው ጉዳት “መጠነኛ” የሚባል ነው።

    ፉጃኢራህ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዞን መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻዎች አንዱ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነት ከመደረሱ በፊትም በኢራን ጥቃት ተፈጽሞበት ነበር።

    ስፍራው መመታቱ የተሰማው፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን ከገለጸ በኋላ ነው። አራተኛው ሚሳዔል ባሕር ላይ እንደወደቀ ተገልጿል።

    እስካሁን ድረስ ኢራን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠችም።

  19. ኢራን መርከቦች በሆርሙዝ በኩል አልፈዋል የሚለው የአሜሪካ ገለጻ “ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው” አለች

    የኢራን ወታደሮች ጀልባ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች ስለማለፋቸው የሰጠው ገለጻ “ፍጹም ውሸት” ነው ሲል አጣጣለ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ፤ ሁለት የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማን የሚያውለበልቡ የንግድ መርከቦች “በተሳካ ሁኔታ በሆርሙዝ ወሽመጥ ማለፋቸውን” ገልጾ ነበር።

    በኢራን መገናኛ ብዙኃን የወጣው የአብዮታዊ ዘቡ መግለጫ ግን “በቅርብ ሰዓታት አንድም የንግድ ወይም ነዳጅ ጫኝ መርከብ” በሆርሙዝ ወሽመጥ አላለፈም ብሏል።

    የአሜሪካን መግለጫ “መሠረተ ቢስ እና ሙሉ በሙሉ ሐሰት” ሲል የጠራው የኢራን አብዮታዊ ዘብ፤ ከባሕር ኃይሉ ትዕዛዝ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ “ከፍተኛ አደጋ እንደሚገጥመው” አስጠንቅቋል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የአሜሪካን ገለጻ እውነተኛነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው። የባሕር ጉዞ መከታተያ የሆነው ‘ማሪን ትራፊክ’ ድረ ገጽ ከአሜሪካ ገለጻ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመርከብ ጉዞ መደረጉን አያሳይም።

    ይሁን እንጂ መርከቦች አቅጣጫ ጠቋሚያቸውን አጥፍተው ጉዞ ሊያደርጉ ስለሚችል ትክክለኛ ቦታቸው ሳይገለጽ አልፈው ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ።

  20. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢራን ሚሳዔል እንደተተኮሰባት አስታወቀች

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከቴህራን በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመውባታል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቴህራን በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመውባታል

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መከላከያ ሚኒስቴር ከኢራን የተወነጨፉ ሦስት ሚሳዔሎችን ማክሸፉን እና አራተኛው ባሕር ላይ መውደቁን አስታወቀ።

    መከላከያ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ እንዳሰፈረው፤ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ፍንዳታ የተሰማው በከሸፉት ሚሳዔሎች ምክንያት ነው።

    ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው፤ የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ባለሥልጣን ለተወነጨፉ ሚሳዔሎች ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ካስታወቀ በኋላ ነው። ባለሥልጣኑ፤ የአገሪቱ ዜጎች ደኅንነቱ የተጠበቀ ስፍራ ውስጥ እንዲቆዩ አሳስቦ ነበር።

    እስካሁን ኢራን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠችም። በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን፤ ኤምሬቶችን ጨምሮ የባሕረ ሰላጤው አገራትን በማጥቃት አጸፋ ስትሰጥ ቆይታለች።

    ከአሜሪካ ጋር ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ግን ጥቃቶቹ ረግበው ነበር። አሁን ኤምሬቶች ላይ ጥቃት የተፈጸመው አሜሪካ በኢራን በተዘጋው ሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚጓዙ መርከቦችን እንደምታጅብ ካስታወቀች በኋላ ነው።