ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር የተወዛገቡት ጠ/ሚኒስትር ኔታኒያሁ ኢራን “በእሳት እየተጫወተች ነው” አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በእሳት እየተጫወተች ነው ያሏት ኢራን ያላትን የዩራኒየም ክምችት ለማስወገድ እንዳልተስማማች ነገር ግን የሚደርስባት ጫና እየበረታ መሆኑን ተናገሩ።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር መወዛገባቸው የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትራምፕ ጋር በኢራን ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም እንዳቸላው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሲኤንቢሲ በሰጡት ቃለ ምለልስ ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ድርድር ካለስኬት ቢቋጭ ብዙም እንደማያሳስባቸው እና የኢራን ጉዳይ ያላበቃ ቢሆንም ግን በከፍተኛ ሁኔታ መዳከሟን ገልጸዋል።
ከኢራን ጋር ዳግም ወደ ሙሉ ጦርነት የመግባቱ ጉዳይ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚወሰን መሆኑን እና ”የአሜሪካ እና የእስራኤል ኃይሎች ዝግጁ ናቸው። ኢራንም ይህንን ማወቅ አለባት፤ እነሱም ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን በግልጽ እንደሚታየው በእሳት እየተጫወቱ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደችው ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለፉት ቀናት ሲዘገብ እንደነበረው በሁለቱ መሪዎች መካከል ጠንከር ለያ ንግግር መደረጉ ተገልጿል።
ፕሬዝዳን ትራምፕ “ፖድ ዋን ፎርስ” ከተባለ ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከኔታኒያሁ ጋር የጋለ ምልልስ ማድረቸጋውን አረጋግጠዋል።
“አዎ [ጠንካራ ውይይት] አድርገናል። በጣም ተናድጄ ነበር፤ ሊባኖስ ውስጥ [ኔታኒያሁ] እያካሄደው ባለው ያልተቋረጠ ጦርነት ተረብሼ ነበር” በማለት ውይይታቸው ጠንከር ያለበትን ምክንያት አስረድተዋል።
የኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ስለተደረገው የስልክ ምልልስ በይፋ ከመናገር ቢቆጠብም ጠቅላይ ሚኒስረሩ ግን “እንደ ጥሩ ቤተሰብ አንዳንድ ጊዜ ስልታዊ ልዩነቶች አሉን” በማለት ጉዳዩን በማጣጣል የጋራ ዘላቂ አላማ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ኔታኒያሁ ጨምረውም ከኢራን ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ዘወትር ስመምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
















