የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት በመርዛማ ኬሚካል ልቀት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አወጀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት በመርዛማ ኬሚካል ልቀት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አወጀች። የካሊፎርኒያ ግዛት ገዢ ጋቨን ኒውሰም ኦሬንጅ ካውንቲ በተባለ አካባቢ በማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ አደገኛ የኬሚካል ፍሳሽ ከተከሰተ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል።

ከ26,500 ሊትር በላይ ከሚይዘው ታንከር ኬሚካል እየፈሰሰ መሆኑ ታውቋል። ይህ ኬሚካል በቀላሉ የሚተን እና በጣም የሚቀጣጠል፤ ፕላስቲክ ለማምረት የሚያገለግል ነው።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ለጥንቃቄ በሚል በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አሳስበዋል።

ቅዳሜ ዕለት ባለሥልጣናቱ ከዚህ ቀደም ይታሰብ ከነበረው በላይ ታንከሩ ውስጥ ያለው ሙቀት ከፍ እንዳለ እና ሙቀቱ መጨመሩ እንደቀጠለ አስታውቀዋል።

የኦሬንጅ ካውንቲ የእሳት አደጋ ባለሥልጣን ክሬግ ኮቪ እንደገለጹት ሁለት አማራጮች እየታሰቡ ነው። ይህም "ታንከሩ ተበትኖ ይፈስሳል? ወይስ ይፈነዳል?" የሚል መሆኑን ገልፀዋል።

ታንከሩ ለምን ሥራው እንደተስተጓጎለ ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን፤ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሙቀቱን ለመቆጣጠር ታንከሩንን በውሃ እየረጩ ነው።

ባለሥልጣናት አንድ "የማይሰራ ቫልቭ" ተጨማሪ ችግር እንደደቀነባቸው አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት የእሳት አደጋ ኃላፊ ኮቪ የተጎዳው ታንከር ሙቀት 32 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ የነበረ እና በየሰዓቱ በአንድ ዲግሪ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

አርብ ምሽት የሙቀት መጠኑ በድሮኖች ተለክቶ 16 ድግሪ ድረስ እንደቀነሰ ተነግሮ ነበር።

ሆኖም የአደጋ ሠራተኛ ቡድኖች ወደ ታንኩ ቀርበው መጠኑን ሲያነቡ ውስጣዊ ሙቀቱ ከፍ ብሎ እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል።

የታንኩን ሙቀት በመጨመር እና በታንኩ ግፊት እንዲጨምር ያደረገውን የኬሚካል መብላላት የአደጋ ሠራተኞች ቡድን ሊቀንሱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አሳይተዋል።

"ይህን ነገር እንዲፍነዳ መፍቀድ በፍጹም አይገባም" ሲሉ ኮቪ ተናግረዋል።

ባለሥልጣናት የታንከሩ መሠረት ቢፈርስ እና ኬሚካሉ ቢፈስ ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎች ጠንካራ ዕቅዶችን እየዘጋጁ ነው። ኬሚካሉ ቢፈስ ወደ ውሃ መስመር ወይም ወደ ባሕር እንዳይደርስ ለመከላከል ግንቦች እየተገነቡ ነው።

ትምህርት ቤቶች ለጥንቃቄ በሚል የተዘጉ ሲሆን፣ ወደ አካባቢው መግባት እንዳይቻል አንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል።

የኦሬንጅ ካውንቲ የሕክምና ባለሙያ ዶክተር ሬጂና ቺንሲዮ-ክዎንግ ማንኛውም ሰው "ጠንካራ ሽታ ያለው ፍራፍሬ የመሰለ" ፈሳሽ ከተመለከተ ለባለሥልጣናት እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።

ለደኅንነት ሲል ቤቱን ለቅቆ የወጣው ማርክ ኦልሰን በአደጋ ደወሎች ድምፅ እንደነቃ እና ስለ ኬሚካል ፍሰቱ ሳያውቅ በአካባቢው ወደ ሚገኝ የስፖርት ማዕከል እንደተጠለለ ተናግሯል።

የኬሚካል አደጋ ስጋት ያሳደረው ጣቢያ የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያ ሲሆን፤ ከአውሮፕላኖች ቁሳቁስ የሚያመርት ነው።

የኩባንያው ቃል አቀባይ ለደረሰው ስጋት ለአካባቢው ነዋሪዎች ይቅርታ ጠይቀዋል።