የቅርጫት ኳስ ተመልካቾች በጩኸት ትራምፕን ተቃወሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ ታሪክ የቅርጫት ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ በመመልከት የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በውድድሩ ታዳሚዎች ተቃውሞ ገጠማቸው። ታዳሚዎቹ በጩኸት ትራምፕን አሽሟጠዋል።

ማዲሰን ስኩዌር ጋርደን የተካሄደውን የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ለመመልከት ለረዥም ሰዓት የጠበቁ ተመልካቾች ትራምፕ ላይ በመጮህ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

በኒው ዮርክ ኒክስ እና በሳን አንቶኒዮ ስፐርስ መካከል የዋንጫ ጨዋታ ተካሂዷል።

የኒው ዮርክ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ ጨዋታውን ተመልክተዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት ትራምፕ በአዳራሹ ስክሪን ላይ ምሥላቸው ሲታይ ነበር ታዳሚዎቹ ተቃውሟቸውን ያስተጋቡት።

ትራምፕ ጨዋታውን የተመለከቱት ከልጅ ልጃቸው ካይ ትራምፕ እና ከኒክስ ክለብ ባለቤት ጄምስ ዶላን ጋር ነው።

የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትር እና የአገር ውስጥ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎችም ባለሥልጣኖች በአዳራሹ ተገኝተዋል።

ትራምፕ የተወለዱት ኒው ዮርክ ቢሆንም በአብላጫው ዴሞክራቶች በሚኖሩበት ትውልድ ከተማቸው ተቀባይነት አላገኙም።

ትራምፕ በኒው ጀርሲ ጎልፍ ሲጫወቱ ቆይተው ወደ ቅርጫት ኳስ ጨዋታው አምርተዋል። በዚህም ወቅት የማዲሰን ስኩዌር ጋርደን ጎዳናዎች ተዘግተዋል።

በአካባቢው የእግረኞች እና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም ተገድቧል።

አንድ የኒው ዮርክ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት በአካባቢው የነበረው ከፍተኛ የደኅንነት ጥበቃ የኒክስ ክለብን "የደስታ ስሜት ገድሏል"።

የኒክስ ደጋፊዎች በማንሀተን ተገኝተው በየጎዳናው ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

የ44 ዓመቱ የክለቡ ደጋፊ እንደተናገሩት ለመጨረሻ ጊዜ ኒክስ ለዋንጫ ግጥሚያ የደረሰው የ17 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር።

ሆኖም ግን ትራምፕ በጨዋታው ላይ መገኘታቸው "በጣም የሚረብሽ ነው" ብለዋል።

አንቶኒ ፑሊ የተባሉ የኒክስ ደጋፊ በበኩላቸው ትራምፕ ጨዋታቸውን መታደማቸውን ባይቃወሙም በአካባቢው የተፈጠረው መስተጓጎል እንደረበሻቸው ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ጨዋታውን እየተዝናኑ ለመመልከት የተዘጋጁ ድግሶች መቀዛቀዛቸውን ጠቅሰው ትራምፕ መገኘታቸው ግን እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የኒው ዮርክ ግዙፍ ሕንጻዎች በክለቡ አርማ ብርቱካናማ እና ሰማያዊ ደምቀው ታይተዋል።

አብዛኞቹ ተመልካቾች ትኬት መግዛት እንዳልቻሉ እና በበይነ መረብ የነበረው ርካሽ የትኬት ዋጋ ከ10,000 ዶላር በላይ እንደሆነ ተገልጿል።

የትኬት ዋጋን መወደድ በተመለከተ አስተያየት የሰጡት ትራምፕ "እንግዲህ ሕይወት እንዲህ ነው" ብለዋል።

ከንቲባው ማምዳኒ ትኬት የገዙት በ1,000 ዶላር መሆኑን ተናግረዋል።